1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አበይት የስፖርት ክንውኖች በ2015

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 18 2008

የጎርጎሪዮሱ 2015 ሊሰናበት የቀሩት በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ቀናት ናቸው። ለመሆኑ በ2015 ምን አበይት የስፖርት ክንውኖች ተከሰቱ? ከፊፋ ፕሬዚዳንት የሙስና ቅሌት አንስቶ እስከ ቤጂንግ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን አስደማሚ ውጤት፤ ከካናዳው የሴቶች የዓለም ዋንጫ እስከ የሚሊዮን ዶላሩ የቡጢ ፍልሚያ በርካታ ነገሮች ተከናውነዋል።

https://p.dw.com/p/1HUmh
Schweiz Logo FIFA in Zürich Gebäude
ምስል Getty Images/AFP/F. Coffrini

አበይት የስፖርት ክንውኖች በ2015

በጎርጎሪዮሱ 2015 የስፖርቱ ዓለምን ካስደመሙ ዘገባዎች መካከል የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (FIFA) ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ የተዘፈቀበት የሙስና ቅሌት ዋነኛው ነበር። የፊፋው የሙስና ቅሌት ምርመራ ቀደም ብሎ በሌሎች ቦታዎች የጀመረ ቢሆንም፤ ወደ ጡዘቱ የደረሰው ግን ሐሙስ ግንቦት ወር 2015 ነበር። በዚያን ቀን የስዊስ ፖሊስ ዙሪክ ውስጥ የሚገኝ አንድ እጅግ ዘመናዊ ሆቴል ውስጥ ዘልቆ በመግባት የፊፋ የቀድሞ እና የወቅቱ 9 ባለሥልጣናትን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ መጀመሩ ብዙዎችን አስደንግጧል። ባለሥልጣናቱ በቁጥጥር ስር የዋሉት ዙሪክ ስዊትስዘርላንድ ውስጥ ፊፋ የሁለት ቀናት ዐቢይ ጉባዔ ሊያካሂድ በዝግጅት ላይ እንዳለ በዋዜማው ነበር። ቀደም ሲል ዩናይትድ ስቴትስም 14 ሰዎች በፍርድ ቤት እንዲመረመሩ ማዘዣ ማውጣቷ ተነግሮ ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ በወቅቱ ፤ የፊፋ ፕሬዚዳንት ሴፍ ብላተር ከ7 ዓመት የሥልጣን ዘመን በኋላ እንደገና ለ4 ዓመት መመረጣቸው ብዙዎችን ማስደመሙ አልቀረም።

በእርግጥ የፊፋ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሙስና ተዘፍቀዋል የሚለው ክስ ብዙዎችን ጣጣ ውስጥ ከቷቸዋል። ቅሌቱን ተከትሎ የፊፋው ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር እና የአውሮጳ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዚዳንት ሚሼል ፕላቲኒ ለስምንት ዓመታት ከእግር ኳስ ነክ ጉዳዮች ታግደዋል። የእገዳው ሰበብ ሴፕ ብላተር ለሚሼል ፕላቲኒ 1,8 ሚሊዮን ዩሮ ገንዘብ ሰጥተዋል የሚል ነው። በዚህ ድርጊታቸው ሁለቱም የቀድሞ ባለሥልጣናት የገንዘብ እገዳ ተጥሎባቸዋል። ፕላቲኒ ለፊፋ ፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር የነበረው ተስፋ ውኃ በልቶታል።

ይኽ የሙስና ቅሌት በፊፋ ብቻ አልተወሰነም። ይልቁንስ የክስ ሒደቱ የጀርመን የእግር ኳስ ፌዴሬሽንንም (DFB) አተራምሷል። ጀርመን በ2006 የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ዕድሉን ያገኘችው ገንዘብ ተከፍሎበት በጉቦ ነው የሚል ዜና የጀርመኑ ዴር ሽፒግል (der Spiegel) የተባለው መጽሔት ይፋ ማድረጉ በርካታ ነገር አስከትሏል። የጀርመን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን እጅ መንሻውን የሰጠው ለጄክ ዋርነር እንደሆነ መጽሔቱ ዘግቧል። ጄክ ዋርነር በወቅቱ የሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ እንዲሁም የካሪቢያን እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በምኅፃሩ ኮንካፋ ፕሬዝዳንት ነበሩ።
በጉቦ ቅሌቱ የጀርመን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዎልፍጋንግ ኒርስባኅ ስልጣናቸውን አስረክበዋል። እሳቸውን የተኩት ጊዜያዊው ፕሬዚዳንት ራይነር ኮኅ ደግሞ መግለጫ ለመስጠት ተገደዋል።

«ጉዳዩ በጀርመን በኩል ፍራንስ ቤከን ባወር፤ በኮንካፋ በኩል ደግሞ ጄክ ዋርነር ፈርመውበታል ስለተባለው የስምምነት ሠነድ የሚያጠይቅ ነው። ጉዳዩ የ2006 የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ማንነት ከሚወሰንበት አራት ቀናት አስቀድሞ ስለተከናወነ ስምምነት የሚወሳ ነው።»

እንደ መጽሔቱ ዘገባ ከሆነ የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጃክ ዋርነርን ድምጽ ለማግኘት ሲል ያልተገባ ድርጊት ፈጽሟል። የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፍራንስ ቤከን ባወር በኩል የተለያዩ ጥቅማጥሞችና 1,000 ውድ ትኬቶችን ለጃክ ዋርነር ለመስጠት ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ለፊፋ የባህል ፕሮጄክት በሚል ከጃክ ዋርነር ጋር የተፈረመው ስምምነት ወደ 6,7 ሚሊዮን የሚቆጠር ዩሮ ነበር ሲል ዴር ሽፒግል አጋልጧል። ጃክ ዋርነር ከሌሎች 14 የፊፋ ባለስልጣናት ጋር በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ተብለው ከእግር ኳስ እድሜ ልካቸውን ታግደዋል። ጥፋታቸው የማጭበርበር፤ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና እጅ መንሻ የመቀበል ድርጊት ነው ተብሏል።

በአትሌቲክሱ ዘርፍ የቻይና ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮን ውጤት እንዲሁም የኃይል ሰጪ መድሐኒትን በተመለከተ የጀርመን እና የእንግሊዝ መገናኛ አውታሮች ይፋ ያደረጉት ዘገባ ጎልቶ ይጠቀሳል።

በቻይና ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮን ውድድር አሜሪካዊው ድንቅ ውጤት ያስመዘገበውም በዚሁ 2015 ነው። ዩሲያን ቦልት በቻይናው ውድድር በ100 እና በ200 ሜትር የአጭር ርቀት የሩጫ ውድድር እንዲሁም በ100 ሜትር ዱላ ቅብብል ሦስት ወርቆችን በማግኘት ኃያልነቱን አስመስክሯል። እንደ ጎርጎሪዮስ በ2008 እዛው ቤጂንግ እና በ2012 ለንደን ላይ በተከናወኑ የኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ ያገኘውን ተመሳሳይ ድል በማስመዝገብ ብቃቱን ያሳየበት ዓመት ነበር 2015።

የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር በምኅፃሩ (IAAF) በመቶዎች የሚቆጠሩ አትሌቶችን የኃይል ሰጪ መድሐኒት ምርመራ ውጤት በአግባቡ አልተከታተለም በሚል ወቀሳ ቀርቦበት ነበር በ2015። የጀርመኑ ቴሌቪዥን ጣቢያ ARD እና የእንግሊዙ ጋዜጣ Sunday Times የምርመራ ውጤቱ መደበቁን በተመለከተ ማጋለጣቸው ማኅበሩን አጣብቂኝ ውስጥ ከትቶት ነበር። የኬንያ አትሌቶችን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ አትሌቶች ቅጣት ገጥሟቸዋል። አጋጣሚው የአንዳንድ አትሌቶች ውጤት ከዓመታት በኋላ እንዲቀየር አድርጓል።

ዘገባውን ተከትሎም በለንደን ማራቶን የሦስተኛ ደረጃን አግኝታ የነበረችው ኢትዮጵያዊት አትሌት ከዓመታት በኋላ አንደኛነቱ እንደሚገባት ተገልጧል። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሰለፈች መርጊያ ከአምስት ዓመት በፊት በተኪያሄደው የለንደን ማራቶን አሸናፊ መኾኗ የተነገራት በ2015 ነበር። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2010 የለንደን ማራቶን አሸናፊ የነበረችው ሩስያዊቷ አትሌት ሊሊያ ሾባኮቫ አንደኛ የወጣችው ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ አበረታች መድሃኒት ተጠቅማ ነው ተብሏል። ውሳኔውን ተከትሎ አትሌት አሰለፈች መርጊያ እንዲህ ብላ ነበር።

በአትሌቲክሱ ዘርፍ አሰለፈች መርጊያ የሚገባትን ክብር ከዓመታት በኋላም ቢሆን ስታገኝ ኢትዮጵያዊቷ ማሬ ዲባባ ደግሞ የ2015 ምርጥ አትሌት ተብላ የተመረጠችውም በዚሁ በ2015 ነበር። አትሌቷን የመረጣት የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ማህበር ነው።

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን ለሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት አመታት ከዋና ዋና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጭ የሆነውም በ2015 ነው። ይኽ የሆነውም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ባለመቻሉ ነው ተብሏል። የአፍሪቃ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በምኅፃሩ ካፍ ለፌዴሬሽኑ የላከውን የውድድር ተሳትፎ መጠየቂያ ቅፅ ሞልቶ ባለመላኩ ነበር ቡድኑ የታገደው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት ካወዳደራቸው ባለሙያዎች መካከል ብቃት ያላቸው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ናቸው በሚል ሥራ እንደሚጀምሩ በኢሜል መልእክቱ ይፋ ያደረገው በዚሁ 2015 ዓም ነበር።

ከሣምንታት በፊት በተጠናቀቀው የመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪቃ የእግር ኳስ ውድድር (ሴካፋ) አስተናጋጇ ኢትዮጵያ ዋንጫው ሳይቀናት ቀርቷል። በሴካፋ የእግር ኳስ ውድድር ዩጋንዳ ርዋንዳን አንድ ለምንም በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆናለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አቋም እና አቅም ከሌሎች ተሳታፊዎች ጋር ሲነፃጸር በደካማነቱ ተተችቷል። «ቡድኑ በአጠቃላይ ለደጋፊ የሚመች ቡድን አልነበረም፤ ውጤት የሚጠበቅበት አልነበረም፤ውህደት የጎደለው ነበር» ያለው የስፖርት ጋዜጠኛ እና ተንታኙ መንሱር አብዱልቀኒ የብሔራዊ ቡድኑ ዕቅድ ግልጽ እንዳልነበረ ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ለሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ከአልጄሪያ፤ሲሸልስና ሌሴቶ ጋር ተደልድላለች። እሳካሁን ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ሌሴቶን 2 ለ1 ስታሸንፍ ከሲሸልስ አቻ ተለያይታለች። በመጪው መጋቢት ከምድቡ ጠንካራ ቡድን ናይጄሪያ ጋር ተከታታይ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በአህጉራዊው ውድድር ተሳትፎዋ ላይ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል።

ሚያዝያ ወር 2015 በእለተ እሁድ በዓለም የቡጢ ፍልሚያ ውድድር ታሪክ ለተፋላሚዎች እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ፉክክር በዩናይትድ ስቴትስ ላስቬጋስ ተከናውኗል። በቡጢ ፍልሚያ ውድድሩ 400 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ ፍሎይድ ሜይዌዘር ለውድድሩ ከ140 እስከ 180 ሚሊዮን ዶላር ሳይከፈለው አልቀረም ተብሏል። የፊሊፒኑተፋላሚ ማኒ ፓኪያው ምንም እንኳን በዳኛ ውሳኔ የተሸነፈ ቢሆንም፤ በበኩሉ ከ100 እስከ 120 ሚሊዮን ዶላር በእጁ እንዳስገባ ተዘግቧል።

በዓለም አቀፍ የሜዳ ቴኒስ ውድድር ደግሞ አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ ከ56 ውድድሮች 53ቱን በማሸነፍ በ2015 ብቃቷን አስመስክራለች። ሴሬና የሜዳ ቴኒስ አራት የፍፃሜ ውድድሮችን ጠቅልላ ለመውሰድ ጥቂት ነበር የቀራት። ከአራቱ ታላላቅ ውድድሮች የሦስቱ አሸናፊ ናት። ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ደግሞ በወንዶች የሜዳ ቴኒስ ለአራት ተከታታይ ዓመታት አራት የሜዳ ቴኒስ የፍፃሜ ውድድሮችን በማሸነፍ በ2015 ኃያል ተወዳዳሪ እንደሆነ አስመስክሯል።

በ20015 ከታዩ አበይት የስፖርት ክንውኖች መካከል ካናዳ ውስጥ የተኪያሄደው የዓለም የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ይገኝበታል። ካናዳ ቫንኮቨር ከተማ ውስጥ በተከናወነው የሴቶች የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ የፍፃሜ ግጥሚያ አሸናፊ የሆነው የየዩናይትድ ስቴትስ ቡድን ነበር። ቡድኑ የጃፓን አቻውን 5:2 በመርታት የዓለም ዋንጫን ለሦስተኛ ጊዜ በእጁ ከማስገባቱም ባሻገር ከአራት ዓመታት በፊት ጀርመን ፍራንክፉርት ከተማ ላይ ጉድ ያደረገው የጃፓን ቡድንን ለመበቀል ችሏል። በዚሁ የካናዳው ውድድር የጀርመን ቡድን ለሦስተኛ ደረጃ ባደረገው ፍልሚያ በእንግሊዝ ቡድን 1 ለ0 መሸነፉም ይታወሳል።

የአውሮጳ ሃገራት የእግርኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ፉክክር ተጠናቆ ቡድኖቹ ለ2016ቱ ዋንጫ ተደልድለዋል። የ2016ቱ የአውሮጳ ዋንጫ ፈረንሣይ ከሩማንያ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ይጀምራል።

ፍሎይድ ሜይዌዘር
ፍሎይድ ሜይዌዘርምስል Getty Images
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ደጋፊዎች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ደጋፊዎችምስል DW
ዩሲያን ቦልት በቤጂንግ ውድድር
ዩሲያን ቦልት በቤጂንግ ውድድርምስል Reuters/D. Martinez
ዙሪክ ስዊትዘርላንድ የሚገኘው የፊፋ ዋና ጽ/ቤት
ዙሪክ ስዊትዘርላንድ የሚገኘው የፊፋ ዋና ጽ/ቤትምስል Reuters/A. Wiegmann
ጀርመናዊው ፍራንስ ቤከን ባወር
ጀርመናዊው ፍራንስ ቤከን ባወርምስል Getty Images/Bongarts/A. Hassenstein
የፊፋው ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር
የፊፋው ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተርምስል Reuters/R. Sprich

ስፔናዊው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በ2015 መገባደጃ ላይ ከባየር ሙኒክ የእግር ኳስ ክለብ ጋር ያላቸውን የሥራ ውል ሲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚለቁ ተረጋግጧል። በፔፕ ጋርዲዮላ እግር ተከትለው ጣሊያናዊው ካርሎ አንቺሎቲ የባየር ሙኒክን የአሰልጣኝነት መንበር በሚቀጥለው አመት ይረከባሉ ተብሏል።

ለተደጋጋሚ ሽንፈት የተዳረጉት የቸልሲው አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆን ከቡድናቸው የተባረሩትም ሊገባደድ ጥቂት ቀናት በቀረው በጎርጎሮሳዊው 2015 ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ