1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሸባብ አራት የስለላ ሰራተኞችን ረሸነ መባሉ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 30 2007

የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ለአሜሪካን፤ ኢትዮጵያና የሶማልያ ደህንነት ተቋም ሲሰልሉ ነበር ያላቸውን አራት ሰዎች መግደሉ ተዘገበ። ታጣቂ ቡድኑ ባርድሬ በተባለችው የሶማልያ ከተማ በአደባባይ አይናቸውን በማሰር መረሸኑን የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1EGgg
al-Shabaab Kämpfer in Somalia
ምስል picture alliance / AP Photo

በሶማልያ በደቡብ ምዕራብ በምትገኘው የባርድሬ ከተማ ያስቻለውን የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ፍርድ ቤት የመሩት ዳኛ ማንነት አልታወቀም። ይሁንና ዳኛው ለአሜሪካኑ ማዕከላዊ የስለላ ተቋም ሲ.አይ.ኤ ይሰልሉ ነበር ያሏቸውን አራት ሰዎች በአደባባይ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ውሳኔ አስተላልፈዋል።በሶማልያ የሚገኘው የዶይቼ ቬሌ ዘጋቢ መሃመድ ኡመር ሁሴን አራቱም በአደባባይ መረሸናቸውን ተናግሯል።

«የአሸባብ ዳኛ አራቱ ሰዎች የአሜሪካን፤ ኢትዮጵያና የሶማልያ ደህንነት ተቋም ሰላዮች ናቸው ብለዋል። ዳኛው የሞት ውሳኔ ካስተላለፉባቸው ሰዎች መካከል የ29 ዓመቱ ኡመር መሃመድ ኻሊድ የሰሃብ ኢስኩዱን ግድያ አመቻችቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል። ሰሃብ ኢስኩዱ የአልሸባብ አመራር የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ጅሊብ ነበር የተገደለው። ከኡመር መሃመድ በተጨማሪ እድሜያቸው 21፤40 እና 49 የሆኑ ሶስት ወንዶች ሞት ተፈርዶባቸው በአደባባይ በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል።»

የአሸባብ ታጣቂ ቡድን አራቱ ሰዎች በመሪው መሐመድ አብዲ ጎዳኔ እና የስለላ ሃላፊው ታህሊል አብዲ ሽኩር በአሜሪካን ሰዉ ዓልባ አዉሮፕላን ጥቃት ሲገደሉ እጃቸው አለበት ብሎ እንደከሰሳቸው ኤ.ኤፍ.ፒ የዜና ወኪል ዘግቧል። ታጣቂ ቡድኑ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ በሶማልያ የነበረውን ጠንካራ ይዞታ በሽንፈት ለአፍሪቃ ሕብረት ሰላም አስከባሪ አስረክቧል ቢባልም አሁንም በሚፈጽማቸው የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች አደገኛ ሆኖ ዘልቋል። መሃመድ ኡመር ሁሴን ታጣቂ ቡድኑ በስለላ የሚጠረጥራቸውን ሰዎች በአደባባይ የመረሸን ልምድ እንዳለው ይናገራል።

«አሸባብ እንዲህ በስለላ የሚጠረጥራቸውን ሰዎች ሲገድል የአካባቢው ሰዎች ወጥተው እንዲመለከቱ ያስገድዳል። ሞት ለፈረዱበት ሰው ወንጀል አመርቂ ምክንያት ላይኖራቸውም ይችላል። ግልጽ አሰራር እና ምርመራም የለም። የከሰሱትን ሰው አይን በማሰር ወደ አደባባይ ወስደው ይገድላሉ። ዋንኛ ዓላማቸው የአካባቢውን ሰው በማስፈራራት እንዲተባበራቸው ማድረግ ነው።»

ሶማልያ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ ውድቀት በኋላ ማዕከላዊ መንግስቱን ለመቆጣጠር በሚፈልጉ ቡድኖች ትንቅንቅ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሰላም ርቋታል። የአፍሪቃ ሕብረት ሰላም አስከባሪዎች እና የቀጣናው ሃገራት ሶማልያን ለማረጋጋት እና እስላማዊ መንግስት ለመመስረት የሚታገለውን የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ለማጥፋት ያደረጓቸው ዘመቻዎች እስካሁን ግባቸውን አለመምታታቸዉ ይታወቃል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ