1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳዛኙ የስደተኞች እልቂት

ረቡዕ፣ የካቲት 4 2007

ባለፈው ሰኞ በሜዲትራንያን ባህር በኩል ወደ ኢጣልያ በጀልባ በመጓዝ ላያ የነበሩ የ27 አፍሪቃውያን ስደተኞች አሳዛኝ እሟሟት አነጋግሮ ሳያበቃ ዛሬ ደግሞ ከ300 በላይ ስደተኞች የተሳፈሩባቸው ጀልባዎች ሰጥመው እዚያው ሜዲትራንያን ባህር ውስጥ ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተዘግቧል ።

https://p.dw.com/p/1EZjn
Italien Flüchtlinge im Hafen von Lampedusa
ምስል picture-alliance/epa/Italian Coast Guard Press Office

ባለፈው ሰኞ ከሞቱት ስደተኞቹ አብዛኛዎቹ ሊታደጓቸው በተላኩ የኢጣልያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ጀልባዎች ውስጥ ብርድ መቋቋም አቅቷቸው መሞታቸው ነው የተነገረው ። የእርዳታ ድርጅቶች ፣ የአውሮፓ የባህር በር ተቆጣጣሪዎች ሰዎችን የመታደግ አቅም ያላቸውን መርከቦች እስካላሰማሩ ድረስ በአደገኛው የባህር ላይ ጉዞ የሚሞቱ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ እንደማይቀር አስጠንቅቀዋል ።የተባባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ መርጃ ድርጅት UNHCR ዛሬ እንዳስታወቀው ከሊቢያ በሜዴቴራንያን ባህር በኩል ወደ ኢጣልያ በመጓዝ ላይ ከነበሩ ስደተኞች ወደ 300 የሚሆኑት ጀልባቸው ሰጥሞ ደብዛቸው ጠፍቷል ። ሟቾቹ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በ4 ትናንሽ ጀልባዎችከሊቢያ ወደ ኢጣልያ ሲጓዙ ከነበሩ ስደተኞች መካከል እንደሆኑ በህይወት የተረፉ 9 ስደተኞች ተናግረዋል ። ባለፈው እሁድ ደግሞ በአነስተኛ ጀልባ ተሣፍረው በሜዲቴራንያን ባህር በኩል ከሊቢያ ወደ ኢጣልያ ጉዞ የጀመሩት 105 ስደተኞች ነበሩ ። ሆኖም ኢጣልያ የባህር ክልል እንኳን ሳይደርሱ እስከ 8 ሜትር በሚደርስ ወጀብ ጀልባቸው ተናወፀ ።

ስደተኞቹ ሰኞ ማለዳ ላይ የኢጣልያ የባህር ጠረፍ ጠባቂ የድረሱልን ጥሪ ቢያቀርቡም የደረሰላቸው ግን ዘግይቶ ነበር ። የባህር ድንበር ጠባቂዎቹ 160 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ ከሰዓት በኋላ ስደተኞቹ ጋ ሲደርሱ ከስደተኞቹ 7ቱ ኃይለኛውን ቅዝቃዜ መቋቋም አቅቷቸው ህይወታቸው አልፎ ነበር ። ወደ ኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ ሲወስዷቸውም ረዥም ጊዜ በመፍጀቱ መንገድ ላይ የ20 ው ህይወት አልፏል ። ምንም እንኳን ስደተኞቹ ከኢጣልያ የባህር ጠባቂዎች ጋር ግንኙነት ከመፍጠራቸው በፊትም ለአደጋ የተጋለጡ ቢሆንም እንዲታደጓቸው ከመጡላቸው አነስተኛዎቹ ጀልባዎች ይልቅ አስፈላጊ መሣሪያዎች ያሉት መርከብ ተልኮ ቢሆን ኖሮ የሰዎቹን ህይወት ማትረፍ ይቻል እንደነበር ሰዎቹን ይረዱ የነበሩ ሃኪሞች ተናግረዋል ። የእርዳታ ድርጅቶች ይህን መሰሉ ችግር ወደፊት ተባብሶ መቀጠሉ እንደማይቀር ከወዲሁ እያስጠነቀቁ ነው ። ለአሁኑ አሳዛኝ አደጋ አንድ ምክንያት ተደርጎ የተወሰደው ማሬ ኖስትሩም የተባለው የኢጣልያው የፍለጋና የመድን ተልዕኮ ሥራ ማቆሙ ነው ። ይህን ከሚሉት ውስጥ ጋንዲ የተባለው ስደተኞችንና ለተለያየ አደጋ የተጋለጡ ሰዎችን የሚረዳው በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ሃላፊ ዶክተር አልጋነሽ ፍስሃ ናቸው ።

Verstorbene Flüchtlinge im Hafen von Lampedusa
ምስል Reuters/Vista via Reuters TV

«የኢጣልያ መንግሥት ትልቁ ጥፋት ማሬኖ ስቶርምን ማቆሙ ነው ። ማሬኖ ስትሮም ቢያንስ የ135 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት አድኗል ።ባለፈው ሳምንት 37 ስደተኞች ሞቱ ፤በዚህ ሳምንት ደግሞ 29 ። ስደተኞችን ያሰፈሩ ሁለት ጀልባዎች የደረሱበት አልታወቀም ።»

Verstorbene Flüchtlinge im Hafen von Lampedusa
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Buccarello

እጎአ በ2013 ፣ ከ366 በላይ ስደተኞች ላምፔዱዛ አቅራቢያ ከሞቱ በኋላ ሥራ የጀመረውን የኢጣልያው ማሬ ኖስትሮምን ወጪ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት አንጋራም በማለታቸው ኢጣልያ ወጪ በዛብኝ ብላ ባለፈው ጥቅምት ሥራውን አቁሟል። ኢጣልያ እንደምትለው ተልዕኮው በመጀመሪያው ዓመት ብቻ 114 ሚሊዮን ዩሮ አስወጥቷታል ። አሁን በሜዲቴራንያን ባህር የተሰማራው ፍሮንቴክስ በተባለው የአውሮፓ ህብረት ድንበር ጠባቂ ድርጅት ስር የሚገኘው ትሪቶን ሲሆን ቁጥጥሩም በህብረቱ አባል ሃገራት የውሃ ድንበር ላይ ብቻ የተወሰነ ነው ። በኢጣልያዋ ሲሲሊና በማልታ የሚገኙት የዚህ ድርጅት ሁለት ትላላቅ ጀልባዎች በዓለም ዓቀፍ የውሐ ክልል ውስጥ የደረሰውን የሰኞውን አሳዛኝ አደጋ መታደግ አልቻሉም ። አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች ለአውሮፓ ድንበር ጥበቃ ሲባል ሰዎች በቅዝቃዜና እንዲሞቱ መደረጉን በጥብቅ ተቃውመዋል ። ህይወት አድኑ ማሬ ኖስትሮምን እንደገና ሥራውን እንዲጀምርም ጠይቀዋል ። ዶክተር አልጋነሽ ደግሞ የአውሮፓ ህብረት አሠራሩን ይመርምር ይላሉ ።

« የአውሮፓ ማህበረሰብ አቋሙን እንደገና መፈተሽ ይኖርባታል ። ስደተኞችን መታደግ ያልቻሉትን ማሬ ኖስትሮምን ወይም ፍሮንቴክስን ትተው ሌላ አዲስ አሠራር መቀየስ አለባቸው ።»

Italien Flüchtlingsdrama vor Lampedusa
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Buccarello

ምንም እንኳን በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓም ከሰሜን አፍሪቃ ወደ ኢጣልያ በጀልባ ሲጓዙ የኢጣልያ ባህር ኃይል የታደጋቸው ከ170ሺህ በላይ ስደተኞች ኢጣልያ ቢገቡም 3200 ሰዎች ደግሞ በጉዞ ላይ ህይወታቸው አልፏል ። ይህ ማብቂያ ያጣው የባህር ላይ አደጋ እንዲገታ ዶክተር አልጋነሽ ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግለት ያሳስባሉ ። በርሳቸው አስተያየት ማሬ ኖስትሮም እንደገና ሥራ መጀመሩ ችግሩን በዘላቂነት አያስወግድም ።

«የተሻለው መንገድ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች መተላለፊያ መስመር መክፈት ነው ። ያ ማለት አፍሪቃ ውስጥ 2 ሃገራት መርጦ ስደተኞች እዚያ ሆነው እንዲያመለክቱ ማድረግ ነው ። ይህን ተግባር የሚያከናውኑ ኤምባሲዎች ወይም ድርጅቶች ስደተኞቹን እያነጋገሩ ተገን የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ይመርጣሉ ። ይህ ሲሆን የሰዎችን ህይወት እናድናለን፤ ደላላዎችንም እናስቆማለን ። በኔ አመለካከት ሌላ ማሬ ኖስትሮምን ያሰማሩም መፍትሄ ሊሆን አይችልም ። »

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ