1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢዉ የኮሌራ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ

ዓርብ፣ ሰኔ 7 2011

በኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው የኮሌራ ወረርሽኝ እስካሁን 16 ሰዎች መሞታቸውን የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቀ። በኮሌራ ከሞቱት 16 ሰዎች መካከል 14 ቱ በአማራ ክልል ነው። ሌሎች ሁለት ሰዎች በዚሁ በኮሌራ ወረርሽኝ ሳቢያ በኦሮሚያ ክልል ሕይወታቸው አልፏል።

https://p.dw.com/p/3KTx5
Hepatitis-B-Virus
ምስል picture-alliance/dpa

አሳሳቢዉ የኮሌራ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ

የኮሌራ ወረርሽኝ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መከሰቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ተቋም አስታወቀ። በሽታው እንዳይሰፋ እየተሰራ መሆንንም አመልክቷል። ሰሞኑን የኮሌራ በሽታ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የተለያዩ የመከላከል ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አስታወቋል። የተቋሙ ምክትል ዋና ዳሬክተር ዶ/ር በየነ ሞገስ በስልክ ለዶቼ ቬለ «DW » እንደገለፁት በሽታው በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ከሁለት ወር በፊት ጀምሮ ወረርሽኙ መከሰቱን ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት፣ በየዳና ቋራ ወረዳዎች፣ በዋግህምራ ዞን አበርገሌ ወረዳ፣ በአዊ ዞን ጓንጓ ወራዳ በአጠቃላይ በአማራ ክልል 198 ሰዎች፣ በትግራ ክልል በክለተ አውላሎ፣አዲግራትና መቀሌ 17 ሰዎች፣በአሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ዞን በኡላ ቡልቱ፣ጭሮና  ዴዴሳ ወረዳዎች፣ 256 ሰዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከየካ ክፍለ ከተማ በስተቀር በሁሉም ክፍለ ሀተሞች 56 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል ብለዋል። እንደዚሁም 33 ሰዎች በሶማሌ ክልል በበሽታው ተይዘዋል የሚል መረጃ ቢኖርም በህክምና እንዳልተረጋገጠ ዶ/ር በየነ አስረድተዋል፡፡
እስካሁን በበሽታው 2 በኦሮሚያ 14 ደግሞ በአማራ ክልል ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል። በአማራ ክልል ሕወታቸው ካለፈው መካከል 6ቱ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ላይ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በያሉበት ህይወታቸው ማለፉን ነው ዶ/ር በየነ አስረድተዋል። በሽታውን ለመከላከልም የፈጣን ምላሽ የህክምና ቡድን ተቋቁሞ የመከላከል ስራ በመላው አገሪቱ እየተደረገና በሽታ ሊከሰትባቸው ይችላሉ በተባሉ ቦታዎች የአሰሳ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።  ባለሙያዎች እንደሚሉት የኮሌራ በሽታ በዓይን በማይታይ ባክቴሪያ የሚመጣ ሲሆን ከሰውነት ከገባ በኋላ በሚያመነጫቸው መርዛማ ነገሮች ከፍተኛ ውኃ በተቅማጥና በተውኪያ ከሰውነታችን እንዲወጣ በማድረግ  ለአጭር ጊዜ ለሞት የሚያደርስ በሽታ ነው። መነሻውም የተበከለ ውኃ፣ የተበከለ ምግብና የአካባቢ ንፅህና ጉድለቶች በመሆናቸው ኅብረተሰቡ የራሱን ንፅህን እንዲጠብቅና የበሽታው ምልክቶች ሲታዩ ወደ ጤና ተቋማት በፍጥነት እንሄድ ዶ/ር በየነ አሳስበዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ