1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሥር ዓመት የኤውሮ ዘመን

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 25 2004

የኤውሮ ምንዛሪ የሕዝብ መገልገያ ገንዘብ ሆኖ በይፋ በሥራ ላይ ከዋለ ወዲህ ባለፈው ዕሑድ የጎርጎሮሣውያኑ የዘመን መለወጫ ዕለት አሥር ዓመት አለፈው።

https://p.dw.com/p/13dQc
ምስል picture-alliance/chromorange

በጊዜው የምንዛሪው ሕብረት ዓባል የነበሩት 12 ሃገራት ነዋሪዎች በመጀመሪያ በታሕሣስ ወር አጋማሽ 2001 ዓ.ም. ገንዘቡን በዕጃቸው እንዲጨብጡ ይደረጋል። የዚሁም ዓላማ ሕዝቡ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ይፋ መገበያያ የሚሆኑትን የኤውሮ ሣንቲሞች ገጽታ እንዲላመድ ማድረግ ነበር።
ኤውሮ በዚህ ሁኔታ እ.ጎ.አ. ከጥር 1 ቀን. 2002 ዓ.ም. አንስቶ ይፋ መገልገያ ገንዘብ ሲሆን ይሄው ኡን አንድ አሠርተ-ዓመት አስቆጥሯል። የጋራ ምንዛሪው መስፈን ታሪካዊ የአውሮፓ ትስስር ውጤት በመባል ሲወደስ ነው የቆየው። የምንዛሪው ሕብረት ዓባል ሃገራት ቁጥርም ወደ 17 ከፍ ሊል በቅቷል። ይሁን እንጂ ዛሬ አውሮፓ በበጀት ቀውስ በተወጠረችበት ወቅት የኤውሮ ሕልውና ስኬታማ መባሉ፤ የወደፊት ዕጣውም እንዲሁ ማጠያየቁ አልቀረም። ታዲያ ኤውሮ የስኬት ታሪክ ወይስ የተዛባ ተሃንጾ ውጤት? በወቅቱ በሰፊው እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው።

ወደ ኤውሮ አመጣጥ ታሪክ መለስ እንበልና የአውሮፓን የጋራ ምንዛሪ የማስፈኑ ሃሣብና ውጥን ገና ከ 60ኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አንስቶ ያለ ነገር ነበር። ይሁን እንጂ ዕቅዱን ተግባራዊ የማድረጉ ግፊት የመጣው ከውጭ ነው። ምክንያቱም የጊዜው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሪቻርድ ኒክሰን ነሐሴ 15 ቀን. 1971 ዓ.ም. የአሜሪካን የሕትመት ባንክ ዶላርን እስከዚያው ቋሚ ሆኖ በቆየው ተመን በወርቅ ከመለወጥ ግዴታ ነጻ ማድረጋቸው ነበር። የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ሄልሙት ሽሚት መለስ ብለው እንደሚያስታውሱት አውሮፓ ደግሞ ይህን የአሜሪካን ግፊት ለመቋቋም አልቻለችም።

“ዕርምጃው የቪየትናም ጦርነትና የዚሁ ወጪ ያስከተለው ነበር። የኒክሰን መስተዳድር የዶላርን በተወሰነ መጠን በወርቅ የመለወጥ ግዴታ ብቻ አልነበረም ያነሣው። ከዚሁ ባሻገር በ 1972 እና 1973 በምንዛሪዎች መካከል ቋሚ የነበረውን መለዋወጫ ደምብም ይተዋል። የጊዜው የፈረንሣይና የጀርመን የፊናንስ ሚኒስትሮች ከ 1945 ዓ.ም. የብሬቶን-ዉድስ ስምምነት በኋላ በጥሩ ሁኔታ ሲሰራበት የቆየው መለዋወጫ ደምብ ያላንዳች መተኪያ መፍረሱን ያኔ ተቃውመናል። ነገር ግን ከአሜሪካ የኤኮኖሚ ልዕልና አንጻር ሂደቱን ለመግታት አልቻልንም”

ሄልሙት ሽሚት በጊዜው የጀርመን የፊናንስ ሚኒስትር ነበሩ። እንግዲህ በመጀመሪያ ስድሥት ከዚያም ዘጠኝ የጊዜው የአውሮፓ ማሕበረሰብ ዓባል መንግሥታት የምንዛሪ ልውውጥን የሚወስን ማሕበር የፈጠሩት ግፊቱን በጋራ ለመከላከል እንዲችሉ ነበር። እነዚሁ መንግሥታት በምንዛሪዎቻቸው መካከል ሰፊ ውዥቀት እንዳይኖር ለማድረግ ሲስማሙ የዚህ ደምብ ዓላማም በአውሮፓው ማሕበረሰብ ዓባል ሃገራት መካከል ያለውን የምርትና አገልግሎት ልውውጥ እንዲሁም የካፒታል እንቅስቃሴ ሂደት ማቃቀልና ማዳበር ነበር። ለዚህም የመንግሥታቱ ማዕከላዊ ባንኮች ምንዛሪያቸውን ከውድቀት ለመጠበቅ ጣልቃ የመግባት ግዴታ ይጣልባቸዋል። መንግሥታቱ የሚተሳሰቡት ደግሞ Europian Currency Unit ወይም በአሕጽሮት ECU በተሰኘ የምንዛሪ መስፈርት መጠን ነበር።

“በጊዜው አይወራለት እንጂ ኤኩን ዘግየት ብሎ ወደ አንድ የጋራ ምንዛሪ የመለወጥ ዓላማ መያዛችንም አልቀረም። እርግጥ ምንዛሪው የመጨረሻው ይሁን አይሁን ገና ግልጽ አልነበረም። ከየብሄራዊው ምንዛሪ ጎን የሚቆም የጋራ ምንዛሪ ሊሆንም በቻለ ነበር። ለማንኛውም ዓላማውን በዋናነት ወደፊት ያራመደው ዣክ ዴሎር ነበር”

ሄልሙት ሽሚት! የጊዜው የአውሮፓ ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ዣክ ዴሎር በዕውነትም በ 1988 ዓ.ም. ለአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ መቋቋም ጥርጊያ ለከፈተው ለአውሮፓ የኤኮኖሚና የምንዛሪ ሕብረት መሠረት የጣሉት ባለሥልጣን ናቸው። ማዕከላዊው ባንክ የኤውሮን ምንዛሪ ቢቀር እስከ ቅርቡ ከማንኛውም ውዥቀት ጠብቆ አቆይቷል። ግን በሌላ በኩል ደግሞ ኤውሮ ገና ከጅምሩ ፈተናም አላጣውም። ምንዛሪው የሕዝብ መገለገያ ከመሆኑ በፊት ጥር 4 ቀን. 1999 ዓ.ም. በ 11 ሃገራት ውስጥ የባንክ መለዋወጫ መሣሪያ ሲሆን የኤውሮ ዋጋ አንድ ዶላር ከ 18 ሣንቲም ነበር። ግን ብዙ ሳይቆይ ሂደቱ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ባለሥልጣናትን ድንጋጤ ላይ ይጥላል። ለዚህም ምክንያቱ ኤውሮ ያለማቋረጥ ዋጋውን እያጣ መሄዱ ነበር። እና እንዲያም ሲል በጥቅምት ወር 2000 ዓ.ም. እስካሁን ባልታየ መጠን ያቆለቁላል። የአንድ ኤውሮ ዋጋ 82 የአሜሪካ ሣንቲም ብቻ ይሆናል።

ታዲያ የጋራ ምንዛሪውን በማጠናከሩ ረገድ ትክክለኛው መንገድ ይያዝ አይያዝ በዚያን ወቅት ብዙ ማነጋገሩ አልቀረም። የአውሮፓ ፖለቲከኞች በጊዜው የሚወስዱት ዕርምጃ የምንዛሪ ገበዮችን የሚያረካ አልነበረም። ለምሳሌ የምንዛሪውን ሕብረት መረጋጊያ ደምብ በሚጻረር መልክ ኢጣሊያ ዕዳዋን ከፍ እንድታደርግ ይፈቅዳሉ። ግሪክን በ 12ኛ ዓባልነት ሲቀበሉም የሕብረቱን መስፈርት የማታሟላ በመሆኗ ዓይናቸውን ጨፍነው እንደነበር ግልጽ ነው። እንግዲህ ከዚህ አንጻር የምንዛሪ ገበዮች በኤውሮ ላይ ዓመኔታ ለማዳበር አለመቻላቸው አያስደንቅም። ይህ የጊዜው ክስተት ከዛሬው ሁኔታ ጋርም እጅጉን የሚጣጣም ነው።

“ችግሩ ያለው ግሪክ ውስጥ ነው። አነሱ ከኤኮኖሚና ከምንዛሪው ሕብረት ውስጥ መግባት አልነበረባቸውም። አየርላንድም ጥሩ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ታድርግ እንጂ እምብዛም ያልጠበቀ የባንኮቿ መዋቅር ብዙ ወጪን የሚጠይቅ ነበር። ፖርቱጋል ደግሞ የምጣኔ-ሐብት ሞዴሏን መቀየር ይኖርባታል። እንግዲህ እነዚህ ናቸው ችግሮቹ። እርግጥ የአንዳንዶቹ በንጽጽር ትናንሽ የሆኑት ሃገራት! ችግሩ የተረጋጉት የታላላቆቹ የአውሮፓ ሃገራት አይደለም”

ይህን ከግማሽ ዓመት ገደማ በፊት የተናገሩት በዘጠናኛዎቹ ዓመታት የጀርመን የፊናንስ ሚኒስትር የነበሩትና ኤውሮን ለማስፈን በተደረገው ድርድር በቀጥታ የተሳተፉት የቀድሞ ባለሥልጣን ቴኦ ቫይግል ናቸው። እርግጥ ዛሬ ችግሩ የተረጋጉ የተባሉትን ታላላቅ ሃገራትም አዳርሷል። ሆኖም ልዩነት መኖሩን ነው ቫይገል የሚያስረግጡት።

“በአንዳንድ አገሮች ያለው ባለፉት 80 ዓመታት ውስጥ ታላቁ የሆነው ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ የቀሰቀሰው የፊናንስ ችግር ነው። እርግጥ በአንዳንድ ሃገራት ስህተቶች ጭምር! ግን የምንዛሪው ችግር አይደለም፤ የተወሰኑት ሃገራት እንጂ!”

በሌላ አነጋገር የኤውሮ ምንዛሪ ቀውስ የለም ማለት ነው። ምንም እንኳ ብዙዎቹ የኤውሮ-ዞን ሃገራት ሰፊ የዕዳ ችግር ቢኖርባቸውም ኤውሮ እንደ ምንዛሪ ፍቱንነቱን ያስመሰከረ ነው። የምንዛሪው አንድ-ወጥነት ኩባንያዎች በሚሊያርዶች የሚቆጠር የገንዘብ ሽግግር ወጪን እንዲቆጥቡ ረድቷል። ለጀርመን ታላቅ የውጭ ንግድ ስኬት ሲያስከትል በምንዛሪው ሃገራት ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎችም ለረጅም ጊዜ ወለድ ዝቅተኛ እንዲሆን በማድረግ ጠቅሟል። ዛሬ በዓለም ላይ ከዶላር ቀጥሎ ሁለተኛው የምንዛሪ ክምችት ኤውሮ ነው። ያለፉት ዓመታት ብዙ የፊናንስ ውዥቀት ቢታይባቸውም ኤውሮ ከዶላር አንጻር እርጋታውን መጠበቁ ተሳክቶለታል።

እርግጥ ዶላር ግልጋሎት ላይ ወደሚውልባቸው አካባቢዎች ምርቶችን የማይሸጥ ወይም ወደነዚህ አካባቢዎች በቱሪስትነት የማይጓዝ የጋራ ምንዛሪው ኤውሮ በዚያ ያለው የውጭ ዋጋ ያን ያህል አያሳስበውም። ይልቁንም ስለራሱ ምንዛሪ ውስጣዊ እርጋታ ነው ይበልጡን የሚጨነቀው። ይህ ደግሞ ከሁሉም በላይ በዚህ በጀርመን ጎልቶ የታየ ጉዳይ ነበር። በሕብረተሰቡ ውስጥ ብሄራዊው የቀድሞ ምንዛሪ ዴ-ማርክ ባለበት እንዲቀጥል የተመኙትና የተከራከሩት ጥቂቶች አልነበሩም። ለምሳሌ ኤውሮ በስራ ላይ ሲውል ገና ከጅምሩ “ቶይሮ” ማለት ውድ የሚል ቅጽል መጠሪያን ነበር ያተረፈው። ዛሬም ቢሆን ይሄው ስሜት በማይናቅ መጠን እንዳለ ነው።
እርግጥ መረጃ ሰንጠረዦችን ከተመለከትን የሚቀርቡት አሃዞች ይህን አልለዝብ ያለ የሕዝብ ግምት የሚያስተባብሉ ናቸው። እንደ መረጃዎቹ ከሆነ ኤውሮ ሕጋዊ የክፍያ መሣሪያ ከሆነ ወዲህ ያሉት አሥር ዓመታት ከዴ-ማርክ የመጨረሻ አሠርተ-ዓመት ሲነጻጸሩ በኤውሮ ክልል ውስጥ የኑሮ ውድነት ዝቅተኛ ነበር። እንግዲህ ከኑሮ ውድነትና ከመለዋወጫ መጠኑ አንጻር የኤውሮ ታሪክ ዛሬ ከአሥር ዓመት ጊዜ በኋላም የስኬት ታሪክ ሆኖ ሊታይ ይችላል። በሌላ በኩል እርግጥ በአንዳንድ ሃገራት ውስጥ ሰፊ የበጀት ኪሣራን የፈጠረውም ኤውሮ ነበር። የደቡባዊው አውሮፓ የኤውሮ ሃገራት የፊናንስ ችግሮች በተለይም የግሪክና የፖርቱጋል ቤት-ሰራሽ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ምርምር ኢንስቲቲዩት እንደሚያስረዳው በመሠረቱ የኤውሮ ገሃድ መሆን ለነዚህ ዛሬ ቀውስ ላይ ለወደቁት ሃገራት ትልቅ የዕድገት ዕድል ነበር የፈጠረው። ገና ቀደም ብሎ በ 1995 ዓ.ም. የአዲሱ ምንዛሪ ሃሣብ መነሣት ለደቡቡ ሃገራት የብድር ወለድ በሰፊው ዝቅ እንዲል ነበር ያደረገው። ክፋቱ ግሪክም ሆነች ፖርቱጋል በዚህ ዕድል ተጠቅመው ለዕድገት የሚበጅ መዋዕለ-ነዋይ አለማድረጋቸው ነው። በአንጻሩ ማሕበራዊ ወጪያቸውን በማስፋት ገንዘቡን በዚሁ ይፈጃሉ። ግሪክ ውስጥ በ 1995 ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት አንጻር 19 ከመቶ የነበረው ማሕበራዊ ወጪ በ 2007 ወደ 25 ከመቶ ከፍ ይላል። በፖርቱጋልም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር።

ኤውሮ ለማንኛውም ችግሩንና ስጋቱን እንደያዘ ባለፈው ዕሑድ ወደ ሁለተኛ አሠርተ-ዓመቱ ተሸጋግሯል። አዲሱ ዓመት ለአውሮፓው ምንዛሪ ክልል ፈታኝና ወሣኝ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። ሕብረቱ ለጋራ ምንዛሪው ሕልውና አደገኛ የሆነውን የዓባል ሃገራቱን የበጀት ቀውስ ለማስወገድ የሚቀረው ምርጫ እርግጥ አንድ ብቻ ነው። የበጀት ኪሣራ ገደቡን ዓባላቱ እንዲያከብሩ ማድረግና በቀውሱ በተጠመዱት ሃገራት ፍቱን መዋቅራዊ ለውጦችን ማካሄድ! ሃሣቡ በተገባደደው ዓመት መነሣቱ ባይቀርም ገቢርነቱ ግን ገና የሕብረቱን የአቋም አንድነትና ቁርጠኝነት አጥብቆ ይጠይቃል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ







ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ