1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሜሪካና ኩባ የ56 ዘመኑ ፍጥጫ ፍፃሜ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 5 2007

ምክትል ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን «ትከለኛ» ያሉትን «አቅጣጫ ለማስያዝ» ያደረጉት ሙከራ አንደከሸፈ ሁሉ፤ በፕሬዝዳንት አይዘናወር ዕቅድ መሠረት ፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ኩባዎች «ቅጥረኞች» ባሏቸዉ ተዋጊዎች አማካይነት ኩባን ከኮሚንስቶች አላቀዉ «ትክክለኛዉን አቅጣጫ ለማስያዝ» ያዘዙት ወረራም ከሸፈ።

https://p.dw.com/p/1F7Hp
ምስል Reuters/Jonathan Ernst

የቀድሞዉ የኩባ መሪ ፊደል አሌሐንድሮ ካስትሮ ሩዝ እንደ ሐገር መሪ መጀመሪያ ከጎበኙት ሐገራት አንዷ ዩናይትድ ስቴትስ ነበረች።ካስትሮ ሥልጣን በያዙ በአራተኛዉ ወር ዋሽግተን ገቡ።የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጄኔራል ድዋይት ዴቪድ አይዘናወር ግን ካስትሮን ላለማነጋገር ጎልፍ ሊጫወቱ ከዋሽግተን ወጡ ።ከሐቫናዎች-በሐቫናዎች በኩል ከሞስኮዎች ጋርም ጨዋታዉ የጠመንጃ-ሚሳዬል ዉጊያ፤ የኑክሌር ፍጥጫ፤ የግድያ-ሙከራ፤ የሴራ ሻጥር ማዕቀብ ሆነ።በ56 ዓመቱ በቀደም ግን አጋዳዩ ሥልት ተለወጠ።ወይም የተለወጠ መሠለ። ሠላም።የሠላሙን ጅምር አስታከን የሐምሳ-ስድስት ዘመኑን ጠላትነት፤ባጭሩ እንቃኛለን አብራችሁኝ ቆዩ።

ፊደል ካስትሮ በወላጆቻቸዉ ሐብት፤ በሕግ ዶክተርነት እዉቀታቸዉ ገቢ ተንደላቀዉ መኖር እየቻሉ ለድሆች የመሟገታቸዉ ቁርጠኝነት፤ የጄኔራል ፉልሔንቺዎ ባቲስታ ሳልዲነርን አምገነናዊ አገዛዝን የሚቃወሙ ሐይላትን የማስተባበራቸዉ ብቃት፤ለጠመንጃ ዉጊያ ጫካ የመግባታቸዉ ፅናት፤ የአንደበታቸዉ ትባት፤ እንደ አብዛኛዉ የዚያ ዘመን የዓለም ወጣት ሁሉ የአሜሪካ ወጣቶችን ለመማረክ በቂ ነበር።

ኮት፤ ከራቫት ከሚያዘወትሩት፤ የአንጋች ጋጋታ ከማይለያቸዉ፤ የተጠኑ ቃላት ከሚወረዉሩት የሐገራቸዉ ፖለቲከኞች ፊት መቅረቡ የሰለቻቸዉ የአሜሪካ ጋዜጠኞች ደግሞ ፂም ባርኔጣ፤ የጦር ሜዳ ልብስና መለዮ፤ መለያዉ ያደረገ መሪ ለማየት ሳይጓጉ አልቀሩም።ካስትሮን።ጋዜጠኞቹ ለጉጉት ፍላጎታቸዉ ርካታ የአሜሪካ ጋዜጣ አዘጋጆች ማሕበረሰብ-በተባለዉ ማሕበራቸዉ አማካይነት ካስትሮ ዋሽግተንን እንዲጎበኙ ጋበዟቸዉ።ሚያዚያ 15 1959 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ዋሽግተን ገቡ።ካስትሮ የመሩት የኩባ ኮሚንስቶች የመልዕክተኞች ቡድን ዩናይትድ ስቴትስን ለአስር ቀናት ሲጎበኝ ፓሬዝዳንት አይዘናወር ለአንድ ሰዓት እንኳን ለማነጋገር አልፈቀዱም ነበር።

US-Präsident Obama und Präsident Raul Castro beim Amerika-Gipfel in Panama
ምስል Reuters/Jonathan Ernst

ምክትል ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ግን ለካስትሮ የሐገር መሪነት ክብር ላለመስጠት «በግል» ከሚል ማራቂያ ጋር ላጭር ጊዜ አነጋገሯቸዉ።የንግግሩ ዉጤት ግን ወትሮም የተንጠረዘዘዉን የጠብ ደመና እንደ ዶፍ ዝናብ የሚዘረግፍ ነበር።አብዮታዊዉ መሪ ኒክሰንን ከማነጋገራቸዉ በፊት ለአሜሪካ ጋዜጠኞች፤ዲፕሎማቶችና የቀድሞ ባለሥልጣናት ያሉትን ለኒክሰን ደገሙላቸዉ።«ዩናይትድ ስቴትስ ለኩባ የምጣኔ ሐብት ርዳታ እንድትሰጥ ተንበርክከን አንለምናትም።» እያሉ።

ኒክሰን ባንፃሩ ከንግግሩ በኋላ «ሰዉዬዉ አንድም ኮሚንዝም በጣም ተሞኝተዋል፤ አለያም የኮሚንዝም ዲስፕሊን ተገዢ ናቸዉ።የእኔ ግምት የመጀመሪያዉ ነዉ» አሉ ለጋዜጠኞች።«ትክክለኛዉን አቅጣጫ እንዲይዙ ለመግፋት ሞክሬ ነበር።» ቀጠሉ የያኔዉ የአሜሪካዉ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን።

የካስትሮ ጉብኝት ከተጠናቀቀ በኋላ ፕሬዝዳንት አይዘናወር የሐቫና ኮሚንቶች የሚስወገዱበትን ብልሐት ያዉጠነጥኑ ገቡ።ዓመት በማይሞላ ጊዜ ዉስጥ የአሜሪካዉ የማዕከላዊ የሥለላ ድርጅት CIA ኩባን በዋሽግተኖቹ «ትክክለኛ አቅጣጫ» እንዲያስገባ ፕሬዝዳንቱ አዘዙ።CIA የሐቫና ኮሚንስቶችን የሚቃወሙ የኩባ ስደተኞችን ለዉጊያ ያደራጅ፤ ያሰለጥን፤ ያስታጥቅ ገባ።የካስትሮዋ ኩባ ባንፃሩ ኩባ የሚገኙ የአሜሪካ እና ከአሜሪካ ጋር የሚሰሩ ኩባንዮችን ዘጋች።ሌሎቹን ወረሰች።በሁለተኛ ዓመቱ በአሜሪካ የታጠቁና የተደራጁት ሐይላት ኩባ ላይ ግልፅ ጦርነት ከፈቱ።

«እዚሕ በምወክለዉ መንግሥት ስም በይፋ ማስታወቅ አለብኝ።ይኸዉም የኩባ ሪፐብሊክ፤ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ባደራጃቸዉ፤ በሚከፍላቸዉና ባስታጠቃቸዉ ቅጥረኞ ተወራለች።ቅጥረኞቹ የሚነሱት ከጓቲማላና ከፍሎሪዳ ነዉ»

Kuba Fidel Castro mit Zigarre
ምስል picture-alliance/AP Photo

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኩባዉ አምባሳደር ካርሎስ ሌቹንግ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንደነገሩት።ሚያዚያ 17 1961።የአሳማዎች ሠርጥ ወረራ ተብሎ በሚታወቀዉ በዚሕ ጦርነት የኩባ መንግሥት ጦርና ብርጌድ 2506 በተባለዉ ሐይል መካከል በተደረገዉ ዉጊያ ከሁለቱም ወገን ከአምስት ሺሕ በላይ ሰዉ ተገድሏል።ከአንድ ሺሕ በላይ ቆስሏል።ዩዩናይትድ ስቴትስ -26 የተባሉትን ሥምንት የጦር ጄቶች ጭምር አስታጣቅ ካዘመተቻቸዉ ተዋጊዎች መካካል ከአንድ ሺሕ ሁለት መቶ በላይ ተማርከዋል።

ምክትል ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን «ትከለኛ» ያሉትን «አቅጣጫ ለማስያዝ» ያደረጉት ሙከራ አንደከሸፈ ሁሉ፤ በፕሬዝዳንት አይዘናወር ዕቅድ መሠረት ፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ኩባዎች «ቅጥረኞች» ባሏቸዉ ተዋጊዎች አማካይነት ኩባን ከኮሚንስቶች አላቀዉ «ትክክለኛዉን አቅጣጫ ለማስያዝ» ያዘዙት ወረራም ከሸፈ።

ሶቬት ሕብረትን የከተተዉ የቃላት እስጥ አገባ፤ የዲፕሎሳዊ ዉዝግብ፤ቀጥተኛና ተዘዋዋሪዉ ወረራ፤ ጦርነቱም አንዳቸዉ ሌላቸዉን «ትክክለኛ» ወደሚሉት ሊያመጣ አለመቻሉን በጥሞና ለመገምገም አልፈለጉም።እንዲያዉም ተደጋጋሚዉ ዉዝግብ፤ አስጥ አገባ ጠብ-ቁርቁስን ከማስከተል ባለፍ ለሁሉም ምናልባትም ለተቀረዉ ዓለምም «ትክክል» ወደ ሆነዉ ሰላማዊ ግንኙነት እንዳያመራ የሚፈልጉ ይመስሉ ነበር።

ሰወስቱ ሐገራት የገጠሙት እስጥ አገባ ንሮ የአሳሞቹ ሠርጥ ወረራ-በኩባ አብዮተኞች ድል በተጠናቀቀ ባመቱ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በቅጡ ያላገገመችዉን ዓለም ከሰወስተኛዉ ምናልባትም አይታዉ ከማታዉቀዉ የኑክሌር ጦርነት ከሚዶልበት አፋፍ ላይ ደረሰ።

Bildergalerie Kuba
ምስል picture-alliance/dpa

የሶቭየት ሕብረት ኑክሌር አወንጫፊ ሚሳዬሎች ቀስታቸዉን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ደግነዉ ኩባ ምድር ተጠመዱ።በጃፓኖቹ ከተሞች ሔሮሺማና ናጋሳኪ ዘር-ማንዘር አጥፊዉን ቦምብ በማፈንዳት የታወቁት የሜሪካ ኑክሌር ጣይ ጄቶች ለበረራ ተዘጋጁ።የሁለቱ ሐገራት ዘመናይ የጦር መርከቦች ያንዱ ወደ ተቃራኒዉ ይቀዝፉ ገቡ።

ጥቅምት 22 1962።ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ አስጠነቀቁ።«የሚከተሉት እርምጃዎች ባስቸኳይ እንዲወሰዱ አዝዢያለሁ።የጥቃት ዝግጅቱን ለመከላከል ማንኛዉም ወታደራዊ መሳሪያ ወደ ኩባ ደሴት እንዳይገባ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል።ከማንኛዉም ሐገር ወይም ወደብ ወደ ኩባ የሚጓዙ መርከቦች በሙሉ የጦር መሳሪያ ጭነዉ ከተገኙ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ይገደዳሉ። በማንኛዉም የምዕራብ ንፍቀ-ክበብ ሐገር ላይ ከኩባ የኑክሌር ጥቃት ከተከፈተ ሶቭየት ሕብረት በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ጥቃት እንደተከፈተች ይቆጠራል።በሶቭየት ሕብረት ላይ አስቸኳይ የብቀላ እርምጃ ይወሰዳል።»

የሞስኮ-ዋሽግተን ጠላቶች በጦር በመጣጠናቸዉ መፈራራታቸዉ፤ የሁለቱ ሐገራት መሪዎች ብልጠት ታክሎበት የተፈራዉ የኑክሌር ጦርነት በርግጥ አልተጫረም።ሶቬት ሕብረት የምትመራዉ የኮሚንስቱ ዓለም ከአሜሪካ መራሹ የካፒታሊስት ባላንጣዉ ጋር የገጠመዉ ግጭት፤ ቁርቁስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪቃ እስከ ደቡብ አሜሪካ፤ ከአዉሮጳ እስከ እስያ የሚገኙ አያሌ ሐገራትን ማተራመሱ ግን ቀጠለ።

ዛሬ ከአፍቃኒስታን እስከ ሶሪያ፤ ከፍልስጤም እስራኤል እስከ ዩክሬን፤ ከኮሪያ ልሳነ ምድር እስከ ኮንጎ ያሉ ግጭት ጦርነቶች የያኔ ቅሪቶች ናቸዉ።ትንሺቱ ደሴት ኩባ ከዓለም ሐብታም፤ ሐያል ጎረቤትዋ ጋር የገጠመችዉ ጠላትነትም እንዲሁ።

Nixon macht Victoryzeichen nach Rücktritt 1974
ምስል picture-alliance/dpa

ዩናይትድ ስቴትስ እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ድረስ የፊደል ካስትሮን መንግሥት ለማስወገድ ያልሞከረችዉ የለም።አንዳድ ዘገቦች እንደጠቆሙት ዩናይትድ ስቴትስ 368 ጊዜ ካስትሮን ለማስገደል ሞክራለች።የሚያጤሴቱን ሲጋር ከመመረዝ፤ ቦምብ የተቀበረበት ደብዳቤ እስከ መላክ፤ በሚናገሩበት ማይክሮፎን ቦምብ ከማጥመድ፤ቆንጆዎችን እስከ ማዝመት የደረሰዉ የግድያ ሙከራ ሁሉም ከሽፏል።ሰዉዬም 1959 ዩናይትድ ስቴትስ አፍንጫ ሥር የተከሉት ሥርዓታቸዉም አሉ።

የጦርነት፤ ግጭት፤ ፍጥጫ፤ የምጣኔ ሐብት ማዕቀብ፤ ነብስ የማስጠፋቱ ሙከራ መክሸፍ ኒክሰን ላንድ ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ «ትክክለኛ አቅጣጫ» ያሉት ትክክል እንዳልነበር ለመረዳት ሐምሳ-ስድት ዓመት መፍጀቱ በርግጥ አሳዛኝ ነዉ።የፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን ለዩናይትድ ስቴትስ፤ ለኩባ፤ ለዓለምም ሠላም ትክክል የሚባለዉን እርምጃ መጀመሩ ግን ያፅናናል።የኩባ አቻቸዉ የራዑል ካስትሮ ተመሳሳይ አፀፋ ያበረታታል።

የኦባማና የካስትሮ (ትንሹ) መንግሥታት በሚስጥር የጀመሩት ግንኙነትን የማሻሻል እርምጃ ሲያዘግም ከርሞ ባለፈዉ ቅዳሜ ሁለቱን መሪዎች አጨባበጠ።አግባባም።

«ቀዝቃዛዉ ጦርነት ከተወገደ ረጅም ጊዜ ሆነዉ።እዉነቱን ለመናገር እኔ ከመወለዴ በፊት የተጀመረዉ ሽኩቻ እንዲቀጥል አልፈልግም።እኔ የምፈልገዉ ችግርን ማስወገድ ነዉ።ከናንተ ጋር መሥራት ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ የምትፈልገዉ ይሕንን ነዉ።ለዚሕም ነዉ የጋራ ግንኙነታችንን ለማሻሻል ይሕን ያክል የጣርነዉ።ለዚሕም ነዉ የጋራ ጥቅምን ለማስከበር፤የእኩልነትና የመከባበር መንፈስን ለማዳበር ይሕን ያክል ያወጣነዉ።ይሕ ደግሞ መሻሻልን ያስከትላል ብዬ አምናለሁ።»

ራዑል ካስትሮ የግንኙነቱን መሻሻል በደስታ ተቀብለዉታል።መሻሻሉ ግን «ፍቅሬ፤ ፍቅሬ በዛ እንዳይሆን አደራ ብለዋል።

«በሁሉም ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ዝግጁ ነን።ይሁንና መታገሥ አለብን።በጣም መታገስ።በአንዳድ ጉዳዮች ላይ እንስማማለን። በሌሎች አንስማማም።በዘመናችን የሕይወት እርምጃ በጣም ፈጣን ነዉ።ዛሬ በማንስማማባቸዉ ጉዳዮች ነገ ልንስማማ እንችላለን።»

ሶቭየት ሕብረት የለችም።ኩባም የአሜሪካ የሥልታዊ ጥናት ተቋም የፖለቲካ አጥኚ ካርል ሜአኬም እንደሚሉት የዛሬዋ ኩባ በቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን የነበረችዉ ዓይነት አይደለችም።

« ኩባ ዛሬ በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት የነበረችዉ ኩባ አይደለችም።ከሶቭየት ሕብረት ጋር የነበረን ግንኙነት እና ኩባ የሶቭየት ሕብረት ተቀፅላ በመሆንዋና ከዚያ ጋር የመጣዉ ጣጣ በሙሉ አሁን የለም።»

Bildergalerie Kuba Fidel Castro Raul Castro
ምስል picture-alliance/AP Photo/Cristobal Herrera

የፕሬዝዳንት ፑቲኗ ሩሲያ ግን እንደ የልሲኗ ሩሲያ ለዩናይትድ ስቴትስ የምታድር ሳትሆን እንደ ክሪስቾቯ ሶቭየት ሕብረት እንቢኝ ባይ ሆናለች።ዋሽግተኖች ሐቫና ዳግም ከሞስኮ እቅፍ ትገባለች ብለዉ አለመስጋት አይችሉም።ትልቁ ሥጋት ያለዉ ግን ከሞስኮ ይልቅ ከቤጂንግ ነዉ።

ቤጂንጎች ዋሽግተን-ሞስኮዎች ብዙ ተጫዉተዉበት ብዙ የሰለቸዉን የጠመንጃ-የፖለቲካ ድጋፍ ችላ ብለዉ ካዲስ ሐብት ጋር አዲስ ስልት ይዘዉ ነዉ ብቅ ያሉት።ገንዘብ ወይም ሸቀጥ።ቤጂንግ በጥቅም ለመቆራኘት የምትፈልገዉን ሐገር የፖለቲካዉ ሥርዓት ምን ይሁን ምን መዋዕለ ነዋይዋን ታፈሳለች።ገበያ ታጋኛለች።

ቻይኖች እንደ አፍሪቃ ሁሉ ደቡብ አሜሪካን ዉስጥም ሥር እየሰደዱ ነዉ።ይሕ አሜሪካኖችን ያሰጋል።ከሞስኮ፤ ቤጂንጎች ጋር ብሪክስ የሚለዉ ማሕበር የሚያስተሳስራት ብራዚልም እንደቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን በዋሽግተን በሚታዘዙ ጀኔራሎች ወይም ቱጃሮች የሚትገዛ ደኸ ሐገር አይደለችም።የዋሽግተንን ገበያ ተሻሚ እንጂ።

ይሕም ለዋሽግተኖች ተጨማሪ ስጋት፤ ለሽሚያም የሚያጣድፍ ነዉ።ሌላዉ ምክንያት አሜሪካዊዉ የምጣኔ ሐብትና የፖሊሲ እጥኚ ማርክ ዋይስብሮት የሚሉት ነዉ።የኩባ ኮሚንስትዊ ሥርዓትን ለመጣል ከጠላትነት ይልቅ በወዳጅነት መቅረብ-የሚል የአሜሪካኖች አዲስ ሥልት።

«መንግሥትን ጨምሮ በዉጪ ጉዳይ መርሕ አዉጪዎች ዘንድ አንድ መግባባት ያለ ይመስለኛል።እዉነት ይሁን ዉሸት ሌላ ጉዳይ ነዉ።እነሱ ግን ይሕ (ግንኙነትን ማሻሻሉ) የኩባን መንግሥት ለማስወገድ ዉጤታማዉ መንገድ ነዉ ብለዉ ያስባሉ።»

ራዑል ካስትሮ ጥድፊያዉን የጠሉትም ለዚሕ ነዉ።ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን ሁለቱ ሐገራት ከግማሽ ምዕተ-ዓመት የበለጠዉን የጠላትነት ግንኙነት ማሻሻላቸዉ ለሠላም ጠቃሚ ነዉ።የሁለቱ መሪዎች ዉሳኔ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ሙን እንዳሉት ብልሕነታቸዉን መስካሪ።ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ