1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማርኛ መናገር የሚያስቀጣባቸው ት/ቤቶች

ሐሙስ፣ ሰኔ 28 2004

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቅፅር ግቢዎቻቸው በስህተት የአማርኛ ቃላትን የተናገሩ ተማሪዎች ላይ ቅጣት የሚጥሉ በቁጥር ከአንድ እስከ አራት የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ይነገራል። ብዙዎች ድርጊቱን እንደ እድገት እና መሻሻል ሲቆጥሩት በዛው መጠን ደግሞ ትውልድን መግደል ነው የሚሉ አይታጡም። ለመሆኑ ባህል ያድጋል ሲባል ምን ማለት ነው?

https://p.dw.com/p/15Rpp
ምስል Solomon Mengist

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቅፅር ግቢዎቻቸው በስህተት የአማርኛ ቃላትን የተናገሩ ተማሪዎች ላይ ቅጣት የሚጥሉ በቁጥር ከአንድ እስከ አራት የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ይነገራል። ብዙዎች ድርጊቱን እንደ እድገት እና መሻሻል ሲቆጥሩት በዛው መጠን ደግሞ ትውልድን መግደል ነው የሚሉ አይታጡም። ለመሆኑ ባህል ያድጋል ሲባል ምን ማለት ነው? ባህል በራሱስ ምን ፅንሰ-ሀሳብ ይዟል?

«አንድ ት/ ቤት ውስጥ አንድ ህፃን አማርኛ ከተናገረ I am stupid, I am stupid እኔ ደደብ ነኝ፣ እኔ ደደብ ነኝ» እያለ ሰሌዳው ላይ 100 ጊዜ እንዲፅፍ ይደረጋል።

በእርግጥም ነገሩ እጅግ አሳሳቢ ነው፤ አንድ ህፃንን አማርኛ ለምን ተናገርክ ብሎ በጓደኞቹ ፊት ደደብ ነኝ እያለ 100 ጊዜ ሰሌዳው ላይ እንዲፅፍ ማስገደድ። ትምህርት ቤቶች የእውቀት ምንጮች እና የማንነት መቀረጪያ ቦታዎች ከመሆናቸው አንፃር የድርጊቱን አደገኛነት ሳይገነዘቡት ቀርተው ነው ለማለት ያዳግታል። ህፃናቱ 100 ጊዜ ራሳቸውን ኮንነው እንደፃፉበት ሰሌዳው መሆናቸው ለማንም እሙን ነውና። እናም ይህ ድርጊት ለእነዚህ ህፃናት አማርኛ ቋንቋን መናገራቸው ብቻ ሳይሆን ደደብ እንደሆኑ እንዲሰማቸው የሚያደርገው፤ ቋንቋውን መገለጫው ያደረገውን ባህል እና ማንነትም ወደፊት እንዲያናንቁት መሰረት መሆኑ አይቀርም። ህፃናት የሰጧቸውን ነገሮች ሁሉ ትክክል ነው ብለው የሚወስዱ ከመሆናቸው አንፃር ማለት ነው። በዚህ መልኩ ሲታይ ነው ታዲያ የነገሩ አደገኛነት ግዝፈቱ የሚታየው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህር ቤት መምህሩ ተስፋዬ እሸቱ የባህል ጥናትን በድኅረ ምረቃ ደረጃ አከናውነዋል። ቋንቋ የባህል እንጂ የስልጣኔ መገለጫ አይደለም ይላሉ።

ሙዚቃ፥

ቀደም ሲል እንዳደመጥነው ከሀገር ውስጥ ይልቅ የውጭ ሀገር ባህል ማንፀባረቂያ የሆነውን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ብቻ ልጆቻቸው እንዲማሩላቸው የሚያስገድዱ ሰዎች በኢትዮጵያ ቁጥራቸው እየተበራከተ እንደሆነ ይነገራል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች በሐገራቸው የባህል ውቅያኖስ መሀከል ለብቻው ተነጥሎ የተንሳፈፈ ደሴት ላይ የተተወ ትውልድ ለመቅረፅ የሚጣደፉ መሆናቸውን ያስተዋሉት አይመስልም። ያ ትውልድ እውቅያኖስ ባህሉ ውስጥ ገብቶ የሚቀዝፍበት ሀገርኛ ታንኳ አልተበጀለትምና እስከወዲያኛው ከውቅያኖሱ ተነጥሎ መዝለቁ አይቀርም። ቋንቋ የባህል ውቅያኖሱ መቅዘፊያ ታንኳ ነውና። እንግዲህ እስካሁን ለመዳሰስ የሞከርነው የባህል አንዱ መገለጫ የሆነው ቋንቋን ነው። ለመሆኑ ግን ባህል በራሱ ምንድን ነው? መምህር አበረ አዳሙ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ምሁር እና የዲማ ጊዮርጊስ የቅኔ ምሩቅ ናቸው። የጥንታዊ ፅሁፎች እና ቋንቋዎችንም በማጥናት ላይ ይገኛሉ፤ እንዲህ ያብራራሉ።

ባህል ለሚለው ቃል በእርግጥም አንድ አቻ ትርጓሜው ለማግኘት ይከብዳል። በዓለም ላይ ካሉ በጣም አስቸጋሪ ነገሮች አንዱ ባህል ማለት እንዲህ ነው ብሎ መበየኑ እንደሆነ ግን በተለያየ መልኩ መግለፅ እንደሚቻል መምህር ተስፋዬ ያብራራሉ።

ተማሪዎች እንደሚፃፍበት ሰሌዳዎች ናቸው
ተማሪዎች እንደሚፃፍበት ሰሌዳዎች ናቸውምስል picture-alliance/ dpa

ባህል ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ አንፃራዊ በሆነ መልኩ የሚታይ ነገር ነው ሲሉም መምህር ተስፋዬ ያክላሉ። ለአብነት ያህልም በእድሜ የገፉ አዛውንቶች በሰሜን ንፍቀ ክበብ እና በሀገራችን የሚኖራቸው ተቀባይነት የተለያየ ነው። በሰሜን ንፍቀ ክበብ የተፈጥሮ ሀብቶች የተመናመኑ ከመሆናቸውም ባሻገር የሚሞተው ሰው ቁጥር አነስተኛ ነው። ያም በመሆኑ በዚያ አካባቢ የሚገኘው ማኅበረሰቡ በእድሜ የገፉ ሰዎች እንዲሞቱ ማድረግን ከባህል አንፃር በመጥፎ ድርጊት አይመለከተውም። በአንፃራዊነት በሀገራችን እድሜ የጠገቡ አንጋፋዎች የበለጠ በህይወት እንዲቆዩ ማኅበረሰቡ አጥብቆ ሲሻና ሲንከባከባቸው ይስተዋላል። ይህ እንግዲህ የባህል አንፃራዊነት አንዱ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል። መምህር ተስፋዬ ይቀጥላሉ።

አንድ ኅብረተሰብ ባህሉን መረዳት እና መጠበቅ ካልቻለ መጨረሻው መልስ የማይገኝለት የማንነት ጥያቄ ውዥምብር ውስጥ መውደቅ ይሆናል። ለዚያ ደግሞ ኅብረተሰቡ በተለይ የባህል መገለጫ የሆነው ቋንቋ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ያስፈልጋል ሲል መምህር ተስፋዬ ያስረዳል።

አድማጮች ባህል ያድጋል ሲባል እንደቋንቋ ያሉ የማንነት መገለጫ የሆኑ እሴቶችን በማስቀረት እንዳልሆነ ለማሳየት ሞክረናል። ለሰጡን ሙያዊ ትንታኔ የዩኒቨርሲቲ ምሁራኑን እያመሰገንን በዚሁ እንሰናበት።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ