1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

  አሌፖ፤ ድልና ዉዝግብ

ነጋሽ መሐመድ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 6 2009

ፍርስራሽ፤ ፍርክስካሽ፤ አዋራ፤ አሸዋ የተሞሉባቸዉ ከረጢቶች ክምር፤ የደረቀ ደም የተጣበቀበት ግርግዳ፤ የመኪና፤ የቁሳቁስ ጭርምትምት፤ የቀለሕ ቁልል፤ የጨርቃጨርቅ ብጥቅጣቂ፤---ይሕ ነዉ የዚያች ጥንታዊ፤ ታሪካዊ፤ ሥልታዊ፤ ከተማ የዛሬ ገፅታ። ሐላብ።

https://p.dw.com/p/2ULzF
Syrien Krieg - Evakuierungen in Aleppo
ምስል Reuters/A. Ismail

Syrien krieg-Aleppo fällt - MP3-Stereo

የሶሪያ መንግሥት ጦር የሐገሪቱን ትልቅ ከተማ አሌፖን ሙሉ በሙሉ ከአማፂያን እጅ አስለቅቆ መቆጣጠሩን አስታዉቋል። የጦሩ አዛዦች እንዳስታወቁት ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ የሚደግፏቸዉ አማፂያን ላለፉት ሰዎስት ዓመታት የመሸጉበትን ምሥራቃዊ አሌፖን ከትናንት ጀምረዉ ጥለዉ ሸሽተዋል። አለያም ተደምስሰዋል። ምዕራባዉያን መንግሥታት እና ተቃዋሚዎች ግን የመንግሥት ጦር የከተማይቱ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ገድሏል፤ ምግብና መድሐኒት እንዳይደርሳቸዉ አግዷል በማለት እያወገዙት ነዉ። ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

Syrien Krieg - Evakuierungen in Aleppo
ምስል Getty Images/AFP/K. Al-Masri

በመሳጂድ፤ ቤተ-መቅደስ፤ ቤተ-ክርስቲያን፤ አብያተ-መንግሥታት ሕንፃ፤ ግንቦች፤ በፍርስራሽ መሰዊ-ሥፍራዎች፤ በንግድ-መደብሮች፤ በዛፍ-አበቦች ያሸበረቀዉ ጥንታዊም-ዘመናዊ ዉበትዋ ረግፏል። ፍርስራሽ፤ ፍርክስካሽ፤ አዋራ፤ አሸዋ የተሞሉባቸዉ ከረጢቶች ክምር፤ የደረቀ ደም የተጣበቀበት ግርግዳ፤ የመኪና፤ የቁሳቁስ ጭርምትምት፤ የቀለሕ ቁልል፤ የጨርቃጨርቅ ብጥቅጣቂ፤---ይሕ ነዉ የዚያች ጥንታዊ፤ ታሪካዊ፤ ሥልታዊ፤ ከተማ የዛሬ ገፅታ። ሐላብ።
የገጠጠች፤ የተንጨፈረረች፤ ኦና ምድር ።«ሁሉንም እንደገና እንገነባዋለን።» ይላል ሼኽ ሰይድ የተባለዉ መንደር ነዋሪ። ወጣት ነዉ።
                      
«ሁሉንም ዳግም እንገነባዋለን። ከሰዉ ሕይወት ጋር ሲነፃፀር በንብረት ላይ የደረሰዉ ጥፋት ምንም አይደለም። ቤቶቹ እንደገና ይሠራሉ። ወጣት ከሌለ ግን ሐገር አትኖርም።»
የሶሪያዉ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ከ2,3 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ነበራት። አማፂያን-ምሥራቃዊ፤ የመንግሥት ጦር ምዕራባዊ ግዛትዋን እሁለት ከተቃረጡበት ከ2012 ጀምሮ ሚሊዮኖች ከተማይቱን ጥለዉ ሸሽተዋል።
በሩሲያ የጦር ጄቶች የሚታገዘዉ የሶሪያ መንግሥት ጦር በአማፂያኑ ላይ ጥቃት ከከፈተበት ካለፈዉ ኅዳር መጀመሪያ ጀምሮ ደግሞ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ከከተማይቱ በተለይም ከምሥራቅ ክፍሏ ተሰድዷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ በዉጊያዉ ከ550 በላይ ሰላማዊ ሰላማዊ ሰዉ ተገድሏል።
ከእንግዲህ ግን ግድያ፤ ስደት፤ ጥፋቱ ቆሟል ይላሉ - የአሌፖ የፀጥታ ጉዳይ ኃላፊ መቶ አለቃ ዛይድ አል ሳሌሕ፤ ዉጊያዉ በመንግሥት ጦር ድል አድራጊነት ቆሟልና።
              
«ከዚሕ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛዉ ዉጊያ ቆሟል።»
የሶሪያ የሠብአዊ መብት ታዛቢ የተባለዉ የተቃዋሚዎች ድርጅት የበላይ ኃላፊ ራሚ አብድረሕማንም የመቶ አለቃዉን መግለጫ አረጋግጠዋል። ዉጊያዉ ከመጨረሻዉ-መጨረሻ ላይ ነዉ ብለዉ። የመንግሥት ጦር ትናንት ጧት ድረስ ከ730 በላይ አማፂያን መማረኩን፤ በርካታ መግደሉን፤ የተረፉት ከተማይቱን ጥለዉ መሸሻቸዉን ራሚ አብድረሕማን አስታዉቀዋል።
አማፂያኑ ይሚቆጣጠሩት የነበረዉ ምሥራቃዊ አሌፖ ነዋሪዎች ዉጊያዉ በመቆሙ ደስታቸዉን እየገለጡ ነዉ። ጦርነቱ ባየለበት ወቅት የመንግሥት ጦር ይዞታ ወደነበረዉ ምዕራባዊ አሌፖ ሸሽቶ የነበረው ሕዝብም ቀስበቀስ ወደየቀዬዉ እየተመለሰ ነዉ። 
እሳቸዉ እጃቸዉን ሽቅብ ሰቅለዉ ፈጣሪያቸዉን ያመሰግናሉ። በሽር አል አሰድን ያወድሳሉ። 
                               
ጦርነቱ በርግጥ በመንግሥት ጦር አሸናፊነት ተደምድሟል። ዉዝግቡ ግን እንደቀጠለ ነዉ። አማፂያንን የሚረዱ፤ የሚያስታጥቁና የሚደግፉት ምዕራባዉያን መንግሥታትና የአረብ ተከታዮቻቸዉ የመንግሥት ጦር ሰላማዊ ሰዎችን ፈጅቷል በማለት መንግሥትና መንግሥትን የምትረዳዉን ሩሲያን እያወገዟቸዉ ነዉ። አንድ ሶሪያ የጦር ጄኔራል ግን ዉግዘቱን «ሽንፈት» ያስከተለዉ ሐፍረት ዉጤት አሉት።

Syrien Verletzte werden aus Aleppo evakuiert
ምስል Reuters/A. Ismail
Syrien Krieg - Evakuierungen in Aleppo
ምስል Reuters/A. Ismail

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ