1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ንጆያ ኢብራሂም

Henri Fotso
ዓርብ፣ ሰኔ 4 2013

የሱልጣን ንጆያ ኢብራሂም የግዛት ዘመን ጀርመኖች ካሜሩንን በቅኝ ለመግዛት ከደረሱበት ጊዜ ጋር የተገጣጠመ ነበር። የቅኝ ግዛቱ ኃይል የሌሎችን ኃይላት አቅም መገደብ ሲችል ንጆያ ግን በአፍሪቃዊ ማንነታቸው ተስፋ ሳይቆርጡ ነፃነታቸውን ማስጠበቅ የቻሉ ሰው እንደሆኑ ይነገራል

https://p.dw.com/p/3u4Lp
African Roots | Sultan Njoya Ibrahim | Porträt

ንጆያ ኢብራሂም መቼ ይኖሩ ነበር?
ሱልጣን ንጆያ ኢብራሂም የተወለዱት በጎርጎሮሳያዊው 1876 ዓ ም ገደማ ሳይሆን አይቀርም። አባታቸው ንሳንጉ በጦር ሜዳ ሲሞቱ ንጂያ ሦስት ዓመታቸው ነበር። ገና ሕፃን ስለነበሩም ከ1879 እስከ 1887 ባለው ጊዜ እናታቸው እና ንጃፕድኑንኬ ከክቡር አገልጋይ ከግቤትንኮም ንዶምቡ ጋር  አገዛዙን አረጋግጠዋል። ንጆያ ዙፋኑን ሲቀበሉ ገና 11 አመታቸው ነበር። እሳቸውም  የንቻሬ የን ሥርወ መንግሥት 17ኛው ንጉሥ ነበሩ። ሥልጣናቸው ለ 46 ዓመታት ከዘለቀ በኋላ  በፈረንሳዮች ወደ ያውንዴ ተገደው ተወስደው እና እዛም በግዞት ቆይተው ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።   
ንጆያ ኢብራሂም ምን አይነት ንጉሥ ነበሩ?
የባሙን ንጉሥ የነበሩት ንጆያ ከቀድሞዎቹ በተለየ መልኩ ጠበኛ አልነበሩም። ገና ልጅ ሳሉም ተገደው ነው ጦርነት ውስጥ የገቡት። በ 1892 የክቡር አገልጋያቸው ግቤትንኮም ንዶምቡ ግን ሥልጣኑን ወደውት ስለነበር አዲሱን ንጉሥ ለመገልበጥ ጦር አቋቋሙ። ውጤቱም እስከ 1895 ድረስ ለሦስት ዓመታት የዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ነበር። ጦርነቱ ሊያበቃ የቻለው ከሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ከባንዩ ፉላ ንጉሥ ሱልጣን ኦማሩ ባገኙት ድጋፍ ነው። 

ንጆያ ኢብራሂም

የንጆያን ሥርወ መንግሥት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?
ሱልጣን ንጆያ ማራኪ እና ሰላማዊ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የፈጠራ ባለሙያም ነበሩ። በ 1915 በእስልምና ፣ በክርስትና እና በባህላዊ እምነቶች ተመስጠው የራሳቸው ሃይማኖትን ፈጥረዋል።  የሃይማኖታቸውም መርሆዎች  ‹Nkuet Kwate› ላይ ተፅፏል።  ይህ የንጉሡ መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎም ይጠራል። ይህ መጽሐፍ የተፃፈው በራሳቸው በሱልጣን ንጆያ በተፈለሰፈው የጽሑፍ ፊደል በአ-ካ-ዩ-ኩ ነው። ከዚህም ሌላ ሱልጣን ንጆያ (የፍቅር ልብ ወለዶችን ጨምሮ) 15 ገደማ መጽሐፎችን እና አንድ በባህላዊ መድኃኒት ላይ የሚያተኩር ኢንሳይክሎፔዲያ ጽፈዋል። ከዚህም ባሻገር የበቆሎ መፍጫ ማሽን ፈጥረዋል።  የባሙን ህዝብ ባህላዊ  የኪነ-ጥበባት እድገት ከፍ እንዳደረጉም ይነገራል። ዋና ከተማዋ ፉምባን ዛሬ የጥበብ ከተማ ናት። የከተማዋ እምብርት ላይም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ አካል ሆኖ የተመዘገበው ሱልጣን ንጆያ ያስገነቡት ቤተመንግሥት ይገኛል።
ንጆያ ኢብራሂም ከቅኝ ገዥዎች ጋር የነበራቸው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር?
ንጆያ ኢብራሂም እንደ ሩዶልፍ ዱዋላ ማንጋ ቤል ቅኝ ገዥዎችን አልተዋጉም። ይልቁንስ ከጀርመኖች ጋር ሆነው ከባንሶ ጋር በተደረገ ጦርነት አባታቸውን ገድለው የራስ ቅላቸውን እንደ ዋንጫ ካስቀመጡት ታጋዮች በ 1906 ለማስመለስ ችለዋል። ይህ ጥምረት በጀርመን ቅኝ ገዥዎች እና በባሙን ህዝብ መካከል የተደረገ የመልካም ግንኙነት ጅማሬ ተደርጎ ይወሰዳል። ንጆያ በ1908 ለጀርመኑ ንጉሠ ነገሥት ዊሊያም II ልደት  ስጦታ ያበረከቱላቸው ዙፋናቸውን ነበር። ዛሬ ይህ ዙፋን በርሊን ከተማ በሚገኝ አንድ ሙዚየም ውስጥ ይገኛል። ከዚህም ሌላ  ከሚስቶቻቸው አንደኛዋን (ድንግል የነበሩ) ለአንድ የጀርመን ገዢ ሰጥተዋል። 
በአጠቃላይ በጀርመኖች እና በባሙኖች መካከል የነበረው ግንኙነት ለስላሳ የሚባል አይነት የነበሩ ቢሆንም ፈረንሳዮች የአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ ካሜሩን ሲደርሱ ግን ነገሮች ተለዋውጠዋል። የፈረንሣይ አስተዳደር ሱልጣን ንጆያን ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ወደ ያውንዴ በመላክ ከሥልጣናቸው አባሯቸዋል። በዚህ በጣም እንደተቆጩ የሚነገረው ንጆያም ለሦስት ዓመታት በግዞት እና በቤት የቁም እስረኛ ሆነው ከቆዩ በኋላ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የንጆያ ኢብራሂም ታዋቂ አባባሎች የትኞቹ ናቸው?
«በሀፍረት ከመኖር መሞት ይሻላል» ይህ አባባል ንጆያ ኢብራሂም የቀድሞ እስረኛ ተብለው ወደ ሥርወ መንግሥታቸው ከሚመለሱ ይልቅ በያውንዴ ግዞት ላይ ሳሉ መሞቱን እንደሚመርጡ የገለፁበት ነው።
« አንድ ሰው ከቀደምዎ ቦርሳዎን ይዘው መከተሉን አይዘንጉ» ይህ አባባል ከመጀመሪያዎቹ የጀርመን ሰፋሪዎች ጋር ለመቻቻል የተጠቀሙበት ነው።
«ሌሎች ሰዎች እርሶን መስለው እንዲሰሩ አይፍቀዱ» ።  የሹ-ሞም ቋንቋ መምህር የሆኑት ኦማሩ ንሳንጉ እንደሚሉት ይህ አባባል በግል ለማሰብ ያደዳፍሩ የነበሩትን ፈላስፋ አማኑኤል ካንት ያስታውሳል።  

African Roots | Sultan Njoya Ibrahim

ንጆያ ኢብራሂም: የካሜሮን የፈጠራ ባለሙያው ንጉሥ

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው።