1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናይጄሪያ ቸል ያለችው የአፍሪቃ ነጻ የንግድ ቀጠና ምሥረታ

ቅዳሜ፣ የካቲት 2 2011

አዲስ አበባ በሽር ጉድ እንግዶቿን እየተቀበለች ትገኛለች። የከተማይቱ ዋና ዋና መንገዶች በተለይ የአፍሪቃ መሪዎች እና ከፍተኛ ፖለቲከኞች የሚዘዋወሩባቸው ጸድተዋል። ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥርም በከተማዋ ይታያል። በሒደት ላይ የሚገኘው የአፍሪቃነፃ የንግድ ቀጠና ምሥረታ በ32ኛው የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ቁልፍ ቦታ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/3D3je
Äthiopien AU-Gipfel in Addis Adeba
ምስል Getty Images/AFP/M. Tewelde

የአፍሪቃ ነጻ የንግድ ቀጠና ምሥረታ ሒደት ላይ ነው

የአፍሪቃ መሪዎች ወደ አዲስ አበባ ከመትመማቸው በፊት ሐሙስ እና አርብ የአፍሪቃ ኅብረት ሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ተሰብስቦ ነበር። በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሕማት "መሪዎቻችን በተደጋጋሚ የአፍሪቃን አኅጉር ለማዋሐድ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ እየገለጹ ነው። የቃል ኪዳኖቻችንን ተግባራዊነት ማፋጠን አለብን። የኅብረቶች መጠናከር አማራጭ ያሳጣናል። ጠንክረን በአንድነት ልንቆም ይገባል" ሲሉ ተደምጠዋል።

አዲስ አበባ ላይ የሚደረገው 32ኛው የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በዋናነት ከሚመክርባቸው ጉዳዮች ባሻገር የአፍሪቃ የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ቁልፍ ቦታ እንደሚኖረው ይጠበቃል። የአፍሪቃ ኅብረት ላለፉት ስምንት አመታት ገደማ ግዙፉን ነፃ አኅጉራዊ የንግድ ቀጠና ለመመሥረት ሲያልም ቆይቷል። ከዓመታት ድርድር በኋላ እውን የሆነው የአፍሪቃ የነፃ ንግድ ሥምምነት ቀጠናውን ለመመሥረት መንገድ ጠርጓል። ባለፈው መጋቢት በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ 44 አገሮች የፈረሙት ሥምምነት ተግባራዊ ለመሆን ግን በ22ቱ ሊጸድቅ ይገባል። እስካሁን ድረስ 17 አገሮች ስምምነቱን አፅድቀዋል።

የአኅጉራዊው የነፃ ንግድ ሥምምነት እስከ ዛሬ ድረስ ደካማ ሆኖ የቆየውን የአፍሪቃ አገሮች የርስ በርስ የንግድ ልውውጥ የማሳደግ የረዥም ጊዜ ውጥን አለው። በሥምምነቱ መሰረት ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥ ቀላል እና ርካሽ ሊሆን ይገባል። ከአኅጉሪቱ ሕዝብ ባሻገር ጥቃቅን እና አነስተኛ የንግድ ድርጅቶች በተለይ ተጠቃሚ መሆን ያሻቸዋል።

የአፍሪቃ ኅብረት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነሩ አልበርት ሙቻንጋ እንደሚሉት ስምምነቱን ገቢራዊ ማድረግ ላቅ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል።

ኃላፊው "ዕድሎች እየፈጠርን ነው። ግዙፍ ገበያ ሲፈጠር ለግዙፍ መዋዕለ-ንዋይ በር ይከፍታል። እዚህ ካንተ ጋር እያወራሁ ከአፍሪቃ ውጭ የሚኖሩ የአኅጉሪቱ ዜጎች ለወጣቶች በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጥር ስራ ለመጀመር ወደ እኛ መጥተው እያነጋገሩን ነበር። ምርታማነትን ካሳደግን ይኸ ለልጆቻችን የሥራ ዕድል ይፈጥራል" ሲሉ ተስፋቸውን አስረድተዋል።

የናይጄሪያ ማፈግፈግ

አጠቃላይ ዓመታዊ የምርት መጠኗ 3.4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርሰው አፍሪቃ በዓለም ምጣኔ-ሐብት ውስጥ ያላት ሚና እጅግ የተዳከመ ነው። የአፍሪቃ ኅብረት በአኅጉራዊ የንግድ ቀጠና አማካኝነት ሊቀይር የሚታትረውም ይኸንንው ውስን ሚና ነው። ስምምነቱ የኅብረቱን 55 አባል አገራት ወደ አንድ ካሰባሰበ 1.2 ቢሊዮን ሸማቾች ያሉት ገበያ ለመፍጠር ይቻለዋል። በተሳታፊ አገሮች ብዛት ረገድ የአፍሪቃ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ከዓለም የንግድ ድርጅት መመስረት በኋላ ከፍተኛው ይሆናል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሽን የንግድ ስምምነቱ የገቢ ግብርን በማስቀረት የአባል አገራቱን የርስ በርስ የንግድ ልውውጥ የማሳደቅ አቅም እንዳለው ተስፋውን ገልጿል። ለዚህ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ኹነኛ ያሉት እርምጃ ከአምስት አመታት በፊት በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. ተወስዷል። የምሥራቅ አፍሪቃ አገራት ማኅበረሰብ(EAC)፤ የደቡብ አፍሪቃ አገራት የልማት ማኅበረሰብ (SADC) እና የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪቃ አገራት የጋራ ገበያ (Comesa) በመካከላቸው የነበሩ የንግድ መሰናክሎችን ለማስቀረት ከስምምነት ደርሰዋል።

Infografik wichtige Handelsabkommen weltweit EN

ይሁንና በአኅጉራዊው የንግድ ቀጠና መመስረት ሁሉም የአፍሪቃ አገሮች ዕኩል ባለ ተስፋ አይደሉም። እስከ ዛሬ ድረስ የንግድ ሥምምነቱን ያጸደቁበትን ሰነድ ለአፍሪቃ ኅብረት ያስረከቡት ዘጠኝ አገሮች ብቻ ናቸው። ዘጠኙ አገሮች ጋና፣ ኬንያ፣ ርዋንዳ፣ ኒጀር፣ ቻድ፣ ጊኒ፣ ኢ-ስዋቲኒ (የቀድሞዋ ስዋዚላንድ)፣ ዩጋንዳ እና አይቮሪ ኮስት ናቸው።

ደቡብ አፍሪቃ፣ ሴራ ሊዮን፣ ማሊ፣ ናሚቢያ፣ ሴኔጋል፣ ኮንጎ፣ ቶጎ እና ሞሪታኒያ በየአገሮቻቸው ምክር ቤቶች ስምምነቱን መርምረው አፅድቀዋል። ይኸም ስምምነቱን አፅድቀው ለአፍሪቃ ኅብረት ያቀረቡ እና ለማቅረብ በዝግጅት ላይ የሚገኙ አገሮችን ቁጥር 17 ያደርሰዋል።

በኤኮኖሚዋ ግዝፈት አፍሪቃን ከፊት የምትመራው ናይጄሪያ ግን ወደ ስምምነቱ ለመቀላቀል ዛሬም ዝግጁ አይደለችም። ናይጄሪያ ስምምነቱን ለመፈረም አሁንም ፈቃደኛ አልሆነችም። የአገሪቱ መንግሥት ስምምነቱ የናይጄሪያን ገበያ በርካሽ ምርቶች አጠለቅልቆ የአገሪቱን ሥራ ፈጣሪዎች እና ባለወረቶች ይጎዳል የሚል ሥጋት እንዳለው ገልጿል።

በአፍሪቃ የንግድ ፖሊሲ ማዕከል የንግድ ፖሊሲ ትንታኔ ባለሙያው ዤሚ ማክሌዎድ የናይጄሪያ ማፈግፈግ የከፋ ጉዳት ያስከትላል የሚል ሥጋት የላቸውም።

ዤሚ ማክሌዎድ "ለምሳሌ ያክል የናይጄሪያ ተንታኞችን ከሚያሳስባቸው መካከል በስምምነቱ ስም እንደ ቻይና ካሉ ሶስተኛ አገሮች ሸቀጦች ወደ አገራችን ገበያ ሊገቡ ይችላሉ የሚለው ይገኝበታል። ይኸ የሸቀጦችን መነሻ በሚለዩ ድንጋጌዎች እና ስምምነቶች መፍትሔ ሊያገኝ ይችላል። እንዲህ አይነት ምርቶች ከአገር ወደ አገር ሲዘዋወሩ ከተገኙ በስምምነቱ መሠረት ማገድ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በስምምነቱ ውስጥ የየአገሮቹን ኢንዱስትሪ የሚጎዱ ምርቶች ግብይቶች ከተፈጠሩ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ድንጋጌዎች ተዘጋጅተዋል። ድንጋጌዎቹ አገሮች በእነዚያ ምርቶች ላይ የሚጣሉ ታሪፎችን ከፍ እንዲያደርጉ ይፈቅዳሉ። ይኸ በራሱ ጉድለት ይኖረዋል። አሰራሩ አገሮች ገበያቸውን ከውድድር እንዲዘጉ በር ይከፍታል" ሲሉ የናይጄሪያውያኑ ሥጋት በስምምነቱ ሊቀረፍ እንደሚችል ያስረዳሉ።  

አፍሪቃ በዓለም ገበያ ያላት ድርሻ ሶስት በመቶ ብቻ ነው። ስለዚህ ማክሌዎድ ናይጄሪያን ጨምሮ በመላው አፍሪቃ በውጭ ምርቶች ሊጎዳ የሚችል ገበያ የለም የሚል ዕምነት አላቸው።

ድንበር የለሽ አፍሪቃ

አልበርት ሙቻንጋ አብዛኞቹ የአፍሪቃ አገሮች የነፃ የንግድ ሥምምነቱን የሚያጸድቁበትን ሰነድ በቅርቡ ያስረክባሉ የሚል ዕምነት አላቸው።

"ጥሩ ግስጋሴ በማድረግ ላይ እንገኛለን" የሚሉት አልበርት ሙቻንጋ "በመጪው የካቲት ሁለተኛ ሳምንት ላይ በምናደርገው ጉባኤ ሁሉም ፈራሚ አገሮች አስፈላጊውን ሰነድ ያቀርባሉ። በዚህም የጋራ ገበያውን ለመመስረት የሚያስፈልገን አነስተኛ ቁጥር ይሟላል። ስለዚህ በትክክለኛው ሒደት ላይ እንገኛለን" ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።  

ሒደት እና ፈተና

Ruanda Kigali Unterzeichnung Afrikanisches Freihandelsabkommen
ምስል Getty Images/AFP/STR

ዤሚ ማክሌዎድ ናይጄሪያ የንግድ ቀጣና ምሥረታውን እንደምትቀላቀል ባለሙሉ ተስፋ ናቸው። ዤሚ ማክሌዎድ "ከፊታቸው ፖለቲካዊ ጋሬጣ ጭምር አለ። በመጪዎቹ ሰባት ሳምንታት ምርጫ ያካሒዳሉ። ጉዳዩ ከምርጫ ጋር ሊያያዝ አይገባም የሚል ሐሳብ ነበራቸው። ለመፈረም ባሰቡበት ወቅት ፕሬዝዳንታቸው በአገራቸው በቂ ምክክር አልተደረገበትም በማለት በመጀመሪያ ጉዳዩን ወደ ውይይት ለመውሰድ ወሰኑ። ነገር ግን እስካሁን ከወደ ናይጄሪያ የምንሰማው በአንፃራዊነት አዎንታዊ ሐሳብ ነው። በእኔ አተያይ ናይጄሪያውያን ወደ ነፃ የንግድ ቀጣናው ይመጣሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

አልበርት ሙቻንጋ ዋናው ፈተና ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነቱ ተግባራዊ ሲሆን እንደሚበረታ ያስጠነቅቃሉ። "ሕይወት እንዲህ ነው። አንዱን ፈተና ስትሻገር ከሚቀጥለው ጋር ትፋጠጣለህ። ለዚህም ነው ነፃ የንግድ ቀጣና የመመስረቱ ጅማሪ ሒደት ብቻ የሚሆነው። ትልቁ ፈተና ደግሞ ብዙ ሰዎች ስኬታማ አትሆኑም የሚል ዕምነት መያዛቸው ነው። ነገር ግን የአፍሪቃ ምጣኔ-ሐብት ባደገ ቁጥር በመላው ዓለም ላይ ላቅ ያለ ተፅዕኖ ይኖረዋል። የአፍሪቃ ኅብረት የካቲት 3 እና 4 በቂ አገሮችን ማሳመን ከቻለ በመጪው መጋቢት አኅጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጣና እውን ይሆናል" ባይ ናቸው።

እሁድ እና ሰኞ በአዲስ አበባ የሚደረገው የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ በአንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ከመምከር ባሻገር ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ አገሮችን የማሳመን ስራ ይጠበቃል።

ሲሊያ ካትሪና ፍሮሕሊሽ/እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ