1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናይጀሪያና ፀረ የሕፃናት ሴት ልጆች ጋብቻው ትግል

ሰኞ፣ ነሐሴ 6 2005

በናይጀሪያ የምክር ቤት እንደራሴዎች ለአካለ መጠን ያለደረሱ ሕፃናት ሴቶች ሊዳሩ ይቸላሉ የሚለውን ሕግ ወደፊትም ሊሰራበት ይችላል ካሉ በኋላ በሀገሪቱ ሰፊ ክርክር ተነስቶዋል። ሰሞኑንም በኤኮኖሚ መናኸሪያ በሆነችው በሌጎስ ከተማ አደባባይ በመውጣት «ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት እንጂ ለሙሽራነት አልደረሱም » የሚል መፈክር አሰምተዋል።

https://p.dw.com/p/19NVM
ምስል picture alliance/AP Photo

በአሁኑ ጊዜ በናይጀሪያ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት የማሻሻል ስራ ተጀምሮዋል። በዚህም መሠረት ልጃገረዶች ከተዳሩ በኋላ ዕድሜአቸው ለአካለ መጠን ባይደርስም ለአካለ መጠን እንደደረሱ ይቆጠራል የሚለውን አንቀፅ ለማሻር ጥረት የተደርጎ፣ ከእንደራሴዎቹ መካከል ሁለት ሦስተኛው ደግፈውት ነበር፦ ግን፣ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት እንደራሴ አህመድ የሪማ ሕፃናት ሴቶች ለአካለ መጠን ሳይደርሱ መዳር የለባቸውም የሚለውን ሀሳብ የደገፉት እንደራሴዎች ይህንኑ ውሳኔአቸውን እንዲቀይሩ ለማግባባት ችለዋል። አስገራሚው ነገር የ 53 ዓመቱ እንደራሴ የሪማ ራሳቸው የ 13 ዓመት ግብፃዊት ማግባታቸው ነው። የሪማ የ13 ዓመት ሴት ሕፃን ናት ብለው አያምኑም።

A health worker (L) vaccinates a child at a public health centre where children are being vaccinated against polio in Kano, northern Nigerian, on February 13, 2013. Two Nigerian journalists and a cleric were granted bail today after being charged over a controversial radio programme on polio vaccines days before deadly attacks on polio clinics. Gunmen attacked two polio clinics in the northern city of Kano on February 8, killing at least 10 people, after Wazobia FM broadcast a story on claims of forced vaccinations. AFP PHOTO / BEN SIMON (Photo credit should read BEN SIMON/AFP/Getty Images)
ምስል AFP/Getty Images

« በእሥልምና ሕግ መሠረት፣ ማንኛዋም ትዳር የምትመሠርት ሴት ለአካለ መጠን ደርሳለች። ለአካለ መጠን አልደረሰችም ካላችሁ እሥላማዊውን ሕግ ትፃረራላችሁ። »

የናይጀሪያ ማዕከላይ መንግሥት ለሀገሪቱ ሕፃናት ከለላ የሚሰጥ ሕግ አውጥቶዋል። በሕጉ መሠረት፣ ከ 18 ዓመት በታች የሆነ ሁሉ እንደ ሕፃን ስለሚቆጠር ከለላ ሊደረግለት ይገባል። በዚህም የተነሳ ትዳር ሕጋዊ የሚሆነው የሚዳረው ልጅ ከ 18 ዓመት በላይ ሲሆን ብቻ ነው ይላል። ይሁንና፣ አንዳንድ የናይጀሪያ ፌዴራዊ ግዛቶች ሕጉን ተግባራዊ አላደረጉም። እንደራሴ የሪማ በብዛት ሙሥሊሞች በሚኖሩበት በሰሜናዊ ናይጀሪያ የሚገኙት ግዛቶች አሁንም የሸሪዓን ሕግ የሚከተሉበትን አሰራር እንደ መከራከሪያ ሀሳብ አቅርበዋል።

የመብት ተሟጋቿ ጆ ኦኬይ ኦዱማኪን ይህ ዓይነቱ ህሳብ እጅግ እንደሚያስቆጣቸው ይናገራሉ።

« ሀይማኖትን እኛን ለመከፋፈያ ሊጠቀሙበት የሚፈልጉትን በግልጽ መቃወም አለብን። ይኸው ጉዳይ በናይጀሪያ ድረ ገፆች ብዙ ክርክር አስነስቶዋል። አንዳንድ የየንተርኔት ተጠቃሚዎች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ሴቶችን መዳር በሀገሪቱ እየተስፋፋ መጥቶዋል ያሉትን ሴተኛ አዳሪነትን ለመቀነስ እንደሚያስችል ገልጸዋል። በናይጀሪያ የስራ አጥነቱ መጠን በጣም ከፍ በማለቱ ውጣት ሴቶችን ለዝሙት ይዳርጋል። በነዳጅ ዘይት ሀብት የታደለችው ናይጀሪያ መንግሥት ከዚሁ ተፈጥሮ ሀብት ሽያጭ የሚያገኘውን ገቢ ለስራ ቦታ ፈጠራ ቢጠቀምበትም፣ የስራ አጡ መጠን ከ50% በላይ ደርሶዋል።

ሴቶችን 18 ዓመት ሳይሞላቸው መዳር ሴተኛ አዳሪነትን ለመቀነስ ይረዳል የሚለውን ሀሳብ የመብት ተሟጋቿ ጆ ኦኬይ ኦዱማኪን የተሳሳተ ነው ይላሉ። #« እንደሚመስለኝ፣ የሕፃናት ጋብቻን የሚያራምዱት እነዚህ ግለሰቦች የራሳቸውን ልጆች ለአካለ መጠን ሳይደርሱ አይድሩም። »

ለሴቶች መብት የሚሟገቱት ኤኔ ኤዴም የኦዱማኪንን አባባል ይጋራሉ። አንድ ለአካለ መጠን ያልደረሰች ልጅ ለአንድ በዕድሜ ጠና ያለ ሰው የምትዳርበት ድርጊት ከለ አልባ ያደርጋታል ብለው ነው የሚያምኑት።

« አንዲት ለአካለ መጠን ያልደረሰች ልጅ ሥነ አዕምሮአዊው እና አካላዊው ዕድገት ከሌላት እንዴት ነው ከትዳር የሚጠበቀባትን ኃላፊነት ልትወጣው የምትችለው። ይህን ጉዳይ በጥሞና ልንመለከተው ይገባል ብዬ አስባለሁ። እና የእንደራሴ የሪማ ርምጃ ለአካለ መጠን ያለደረሰች ሴት በሕይወቷ ልትደርስበት የምትችለውን እንዳትደርስ ዕድሏን የሚነፍግ ሆኖ አየዋለሁ። »

"Photo Credit: Earth Day Network" Zulieferer: Sarah Steffen Kinder pflanzen eine Pflanze in Nigeria
ምስል Earth Day Network

ኤዴ ይህን ያሉት ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ነው። በ 11 ዓመታቸው ነበር በዕድሜ በሦስት እጥፍ ለሚበልጡዋቸው ሰው የተዳሩት። ትዳር በልጅነት አንዲትን ልጅ ሕይወቷን እንደፈለገችው መምራት የምትችልበትን መብቷን ይነፍጋል።

ጉዳዩ በናይጀሪያ ብርቱ ክርክር እና ተቃውሞ በማስነሳቱ የሀገሪቱ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የሴት ሕፃናት ጋብቻን ሕጋዊ ያደረገውን አንቀጽ ከሕገ መንግሥቱ እንዲሰረዝ የቀረበውን ጥያቄ እንደገና ለመመልከት ወስኖዋል።

አድሪያን ክሪሽ/አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ