1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

"ኑ በኢትዮጵያ ሥሩ" የተባለበት መድረክ

ረቡዕ፣ ግንቦት 23 2009

የኢትዮ-ጀርመን የንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ ውይይት ትናንት ግንቦት 21 ቀን 2009  በሐኖቨር ከተማ ተደርጓል። በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም.  177 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ሸቀጥ ለጀርመን የሸጠችው እና የ350 ሚሊዮን ዩሮ የሸመተችው ኢትዮጵያ ክራሞት ግን ለንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ ፈታኝ ነበር።

https://p.dw.com/p/2dwKx
3. Deutsch-äthiopischer Wirtschaftstag Mebrahtu Meles und Kuma Demeksa Tokon
ምስል DW/E. B. Tekle

"ኑ በኢትዮጵያ ሥሩ" የተባለበት መድረክ

ከ100 ሚሊዮን በላይ ሸማች ያለው ገበያ ፤ 88 ሚሊዮን ገበሬ የሚያሳትፍ ሰፊ የግብርና ዘርፍ እና የእርሻ መሬት ፤ በዓለም ገበያ ተቀባይነት ያላቸው የቡና ፤ የጤፍ ፤ የሰሊጥ ፤ የጥራጥሬ እና የአበባ ምርቶች የኢትዮጵያ ሹማምንት በሐኖቨር ከተማ የጀርመን ባለወረቶችን እና ኩባንያዎችን ቀልብ ለመሳብ የሚጠቃቅሷቸው መረጃዎች ናቸው። ባለሥልጣናቱ እና የልዑካን ቡድኑ አባላት የጀርመናውያንኑን ቀልብ ይገዙልናል ያሏቸውን መረጃዎች በቁጥሮች የፎቶግራፍ ማስረጃዎች እያስደገፉ "ኑ-በኢትዮጵያ ሥሩ" ሲሉ ተደምጠዋል።

"የአገሪቱ የማምረቻ ዘርፍ ማሽነሪዎች በውጭ ምንዛሪ እየሸመተ መቀጠል አይችልም" የሚሉት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሚኒሥትር ድኤታ ዶ/ር መብራሕቱ መለስ የመንግሥታቸው ቀልብ በጀርመናውያኑ ላይ እንዳረፈ ይናገራሉ። የፌድራል እና የክልል መንግሥታት በፍጥነት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየገነቡ መሆኑን የሚናገሩት ሚኒሥትር ድኤታው "ማሸጊያ ኃይል እና ማሽነሪ የሚያቀርቡ ኩባንያዎች እንፈልጋለን" ሲሉ ይናገራሉ። ዶ/ር መብራሕቱ  እንደሚሉት በመድረኩ መንግሥታቸው ወደ ሚገነባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገቡ ጀርመናውያን ኩባንያዎች እና ግብዓት አምራቾች ማፈላለግ ቀዳሚ ዓላማቸው ነው።

3. Deutsch-äthiopischer Wirtschaftstag Karsten Grimm
ካርሰን ግሪምምስል DW/E. B. Tekle

የድንች ዘር እያባዛ የሚሸጠው ሶላና ኩባንያ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ አይኑን ጥሏል። የድንች ዘሮቹን ከ50 በላይ ለሚሆኑ አገራት የሚያከፋፍለው ሶላና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሲወጥን የምሥራቅ አፍሪቃን ገበያ ታሳቢ አድርጎ ነው። ኩባንያውን ወክለው በበጀርመን-ኢትዮጵያ የንግድ እና መዋዕለ ንዋይ የውይይት መድረክ (German-Ethiopian Business Day) ላይ የተገኙት ካርሰን ግሪም በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት የድንች ዘር የሚያራቡበትን የእርሻ ሥራ እንደሚጀምሩ ተስፋ አድርገዋል።

"ለአገራቸው የውጭ መዋዕለ-ንዋይ ይፈልጋሉ። እኛንም በኢትዮጵያ የድንች ዘር እንድናመርት ጠይቀውናል። ችግሩ ጥብቅ የንጽሕና አጠባበቅ ሕግ አላቸው። ይህ ደግሞ ሥራውን እጅግ ውድ ያደርገዋል። ዓላማው ለአገሬው ገበሬ ጥሩ የድንች ዘር በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መሆን አለበት። ይኸ (ሕግጋቱ) በኢትዮጵያ ለሚኖረን መዋዕለ-ንዋይ ቁልፉ ጉዳይ ነው። እኛ ደግሞ ለአገሩ ገበያ በአገር ውስጥ ዘር ማምረት እንድንችል ቀለል ያለ የአሰራር ዘይቤ እንፈልጋለን።"

ካርሰን ግሪም ከኢትዮጵያውያኑ የልዑካን ቡድን መካከል ጥያቄያቸውን የሚመልስ፤አብሯቸውም የሚሰራ አጋር ሲያፈላልጉ ነው የዋሉት። የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ካርሰን ግሪም ያሉ ጀርመናውያንን ቀልብ ለመሳብ ጥረት ሲያደርግ ይኸ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ ቀደም  በሙኒክ እና በሐምቡርግ ከተሞች ተመሳሳይ መሰናዶዎች ነበሩ። በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ ጥረቶቹ ፍሬ ማፍራታቸውን ይናገራሉ። መስከረም አካባቢ "ከባቫሪያ 20 ኩባንያዎች ኢትዮጵያን አይተው ተመልሰዋል። ቀስ በቀስም ወደ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጁ ነው" የሚሉት አምባሳደሩ ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት ከርዳታ የማሻገር እቅድ እያሳየች እንደሆነ ያምናሉ። "የግል ባለሐብቶችን በማንቀሳቀስ፤ ሥራ በመፍጠር አውሮጳን እያስቸገረ ያለውን ስደት እዛው ማስቀረት ይቻላል የሚል እምነት አላቸው" ሲሉ ያክላሉ።  

በመድረኩ የኢትዮጵያን የመዋዕለ-ንዋይ እና ንግድ እድሎች ካስተዋወቁ ግለሰቦች መካከል የሕግ ባለሙያው ሉትዝ ሐርትማን አንዱ ናቸው። ሐርትማን የጀርመን ባለወረቶችን ቀልብ መግዛት ለኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን ፈታኝ እንደሆነ ይናገራሉ። ፈጣን እና በቅጡ የተደራጀ የማጓጓዣ አገልግሎት፤ የኃይል አቅርቦት እና አስፈላጊ መሰረተ-ልማቶች በተሟሉለት የጀርመን ኤኮኖሚ ውስጥ መሥራት የለመዱት ኩባንያዎች እና ባለወረቶች ፈታኝ የሥራ ከባቢን ለመሞከር ግን ችላ እንደማይሉ ሉትዝ ሐርትማን እምነታቸው ነው።

3. Deutsch-äthiopischer Wirtschaftstag Lutz Hartmann
ሉትዝ ሐርትማንምስል DW/E. B. Tekle

"ጀርመናውያን ምርቶቻቸውን ለሌሎች ሃገራት የመሸጥ ልምድ አላቸው። መዋዕለ-ንዋያቸውን በሌሎች ሃገራት በማፈሰስ ግን ትልቅ የሚባሉ አይደሉም። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ጀርመናውያን ምርቶቻቸውን እንዲሸጡ ብቻ ሳይሆን መጥተው እሴት የተጨመሩባቸው ምርቶች እንዲያመርቱ ማሳመን ይጠበቅበታል። ይህ ደግሞ በውጭ የሚገኙ ጀርመናውያን ዋና እንቅስቃሴ አይደለም። ቢሆንም ይኸንን ለማድረግ ዝግጁ የሆኑ ጀርመናውያን አሉ። በኢትዮጵያ ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው የዘር አምራቾች መኖራቸው ተሰምቷል። ይኸ መልካም እድል ነው። ጀርመናውያን በቅጡ ያልተደራጁ አሰራሮችን አይፈሩም። በዚህ በጀርመንም በርካታ ችግሮች አሉ። ነገር ግን ይኸ የሥራ ፈጣሪ (ኢንተርፕርነር) ሕይወት ነው። ወደዚያ የሚያመሩት ችግርን ለመፍታት ነው። ያንን በኢትዮጵያም ልናደርገው እንችላለን።»

ሉትዝ ሐርትማን ራሳቸው 300 ሔክታር መሬት በሊዝ ተከራይተው ለጊዜው በ30 ሔክታር መሬት ላይ አትክልት እና ፍራፍሬ ያመርታሉ።በመጪዎቹ ሁለት ወራት የእርሻ ሥራቸው ወደ 60 አሊያም 70 ሔክታር ይሰፋል ብለው ይጠብቃሉ። በጎርጎሮሳዊው ጥር 2016 ዓ.ም. የእርሻ ላይ ሥራቸውን የጀመሩት ሐርትማን በኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎች መኖራቸውን አላጡትም። በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አጭር ጊዜ የስራ ፈቃድ ማግኘታቸውን እየጠቀሱ አሰራሩ ለዘለቄታው እንደ አጀማመሩ እንዲሆን ይመኛሉ።

3. Deutsch-äthiopischer Wirtschaftstag Teilnehmer
ምስል DW/E. B. Tekle

ሉትዝ ሐርትማን ሥራቸውን የጀመሩበት ጊዜ ታዲያ ኢትዮጵያ ለአንድ አመት ግድም ከናጣት የፖለቲካ ቀውስ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገቢራዊ ያደረገችበት ነበር።  አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መተዳደር ከመጀመሯ በፊት በኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ የመንግሥት እና የባለወረቶች ንብረት ወድሟል። ሐርትማን የፖለቲካ እና ተቃውሞው ወላፈን በእርሻ ሥራቸው ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ባይኖርም ጉዳዩ ግን አሳሳቢ መሆኑን አይሸሽጉም።

"በእርግጠኝነት ይህ ወደ ሥራ በገቡ እቅዶች ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋል። በምንገኝበት አካባቢ ምክንያት በዚያ ወቅት የደረሰብን ችግር የለም። ምን አልባትም አትክልት እና ፍራፍሬ አምርተን ለአገሬው ገበያ የምናቀርብ በመሆናችንም ሊሆን ይችላል። በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ያለን አቀባበልም መልካም ነው። ለማኅበረሰቡ ቅርብ ለመሆን እንሞክራለን። ነገር ግን ኩነቱ ለውጭ መዋዕለ-ንዋይ ተስማሚ አይደለም። ሁኔታው አሁን ተረጋግቷል። ይሁንና የሚቀጥል ይሁን አይሁን አሊያም በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ትክክለኛ ፖለቲካዊ ውይይት ስለመደረጉ፤ በዚያም ፖለቲካዊ መረጋጋት እና ሰላም ስለመፈጠሩ ገና የምናየው ይሆናል።

ዶ/ር መብራሕቱ መለስ በተቃውሞው ጉዳት የደረሰባቸውን ኩባንያዎች በመለየት የቀረጥ ማበረታቻዎች በመስጠት፤ የባንክ ብድር ያለባቸው የመክፈያ ጊዜያቸውን በማራዘም እና የካሳ ክፍያ ለሚያስፈልጋቸው ካሳ በመክፈል ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደረጉን ገልጠዋል። "የተፈጠረው ነገር በጣም አሳዛኝ ነው። የሰው ሕይወት አልፏል፤ንብረት ወድሟል፤ በኤኮኖሚው እድገት ላይም የራሱን ተፅዕኖ አሳድሯል" የሚሉት ዶ/ር መብራሕቱ መለስ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎችን የናጠውን ተቃውሞ የማይደገም 'ክስተት' አድርገው ያቀርቡታል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ