1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ነፃ ገበያ እና የትራምፕ መንገድ

ረቡዕ፣ ጥር 24 2009

ዋይት ሐውስ ከገቡ ወር ያልሞላቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነፃ የንግድ ውሎችን ወደ ጎን ገፍተው የገበያ ውድድርን ሊዘጉ ዝግጅት ላይ ናቸው። ፕሬዝዳንቱ አገራቸውን ከትራንስ ፓሲፊክ የንግድ ውል ለማስወጣት ትዕዛዝ ያስተላለፉ ሲሆን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገቡ የሜክሲኮ ምርቶች ላይ ቀረጥ ለመጨመር እየዛቱ ነው።

https://p.dw.com/p/2WoHu
Kolumbien Containerhafen Cartagena Archiv 2012
ምስል Manuel Pedraza/AFP/GettyImages

ነፃ ገበያ እና የትራምፕ መንገድ

የአውሮጳ ኅብረት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ ለ27ቱ አባል አገራት መሪዎች በፃፉት ደብዳቤ የዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር ከቻይና፤ሩሲያ፤ ከጽንፈኛ ሙስሊሞች እንዲሁም ከጦርነት እና ሽብር እኩል ለሕብረቱ ውጫዊ ሥጋት ብለውታል። ፕሬዝዳንቱ የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር መግለጫዎችንም «መፃኢ እጣፈንታችንን ለመገመት አስቸጋሪ አድርገውታል» ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጠዋል። «በተለይ» አሉ ቱስክ «በተለይ በዋሽንግተን ያለፉት 70 ዓመታት የዩናይትድ ስቴትስን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጥያቄ ውስጥ በመጣል የተደረገው ለውጥ አውሮጳን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አስቀምጧታል።» ሲሉ ደመደሙ።  

ገና በጠዋቱ ውዝግብ የጫሩት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔዎቻቸዉ ያሰጉት አውሮጳውያኑን ብቻ አይደለም። የዩናይትድ ስቴትስ የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ትራምፕ እና ሚሥጢረኞቻቸው ከሜክሲኮ ጋር በደቂቃ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያከሥር የንግድ ጦርነት ሊከፍቱ ይችላሉ የሚል ፍራቻ አላቸው።ቀረጥ በመጨመር፤ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የድንበር ግብር በማስከፈል እስከ 580 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ግብይት ባላቸው አገራት መካከል ውጥረት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ሰውየው ግንብ ገንብተው ሜክሲኮን ሊያስከፍሉ ምለው ሲገዘቱ ተደምጠዋል። ከምረጡኝ ዘመቻቸው ጀምሮ የሰሜን አሜሪካ የነፃ ንግድ ሥምምነትን (NAFTA) አብዝተው ተራግመዋል። ለዩናይትድ ስቴትስ የሞተር ተሽከርካሪ አምራቾች የደም ሥር የሆነውን ሥምምነት መሰረዝ ለሜክሲኮ ኤኮኖሚ መርዶ ነው። በጀርመን ውጭ ግንኙነት ካውንስል የጥናት ምርምር እና የአውሮጳ ዘርፍ ኃላፊዋ ዳንዬላ ሽቫርዘር በአዲሱ ፕሬዝዳንት እርምጃዎች እንደ ዶናልድ ቱስክ ሁሉ ግራ ተጋብተዋል። «እቅዳቸው በእርግጠኝነት ምን እንደሆነ አናውቅም። የዩናይትድ ስቴትስን ከንግድ ውድድር ለይቶ የመጠበቅ ኃሳባቸውን በተደጋጋሚ ሰምተናል። የተወሰኑ የንግድ ሥምምነቶችን ለመሰረዝ ያላቸውንም ፍላጎት እናውቃለን። በተጨባጭ የምናውቀው ከትራንስ ፓስፊክ የንግድ ሥምምነት ለመውጣት መወሰናቸውን ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ የተወሰኑ ኩባንያዎች ማምረቻቸውን ከዩናይትድ ስቴትስ እንዳያወጡ የወጡትም ወደ አገሪቱ መልሰው እንዲያመጡ ጫና ሲያሳድሩ ተመልክተናል። ነገር ግን አሁንም ሙሉ በሙሉ ዩናይትድ ስቴትስን ከንግድ ውድድር ለይቶ የሚጠብቅ የንግድ ጦርነት ሥልት በዘላቂነት ለመከተላቸው የምናውቀው ነገር የለም።» ትራንስ ፓሲፊክ የንግድ ውል (TPP) በእስያ እያደገ የመጣውን የቻይና ኤኮኖሚያዊ የበላይነት ለመገዳደር የተጠነሰሰ ነበር። ዶናልድ ትራምፕ ቻይና የዩናይትድ ስቴትስን የሥራ እድልን ትዘርፋለች፤ የውጭ ንግዷን ለማሳደግ የመገበያያ ገንዘቧን ምንዛሪ ትቀንሳለች ሲሉ ይወነጅላሉ። 

Präsident Trump unterschreibt Dekret im Oval Office Weißes Haus
ምስል picture-alliance/CNP/A. Harrer

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና አማካሪዎቻቸው «አሜሪካ ትቅደም» በሚል መፈክራቸው ዩናይትድ ስቴትስን ከውሉ አስወጥተዋል። አውስትራሊያ፤ብሩኔይ፤ካናዳ፤ማሌዥያ፤ሜክሲኮ፤ኒውዚላንድ፤ ፔሩ፤ሲንጋፖር ዩናይትድ ስቴትስ እና ቪየትናም የፈረሙት ግን ደግሞ ጃፓን ብቻ ያጸደቀችው ሥምምነት ፋይዳ በፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን በኤኮኖሚ ባለሙያዎች ዘንድም አከራካሪ ነበር። በዓለም 40 በመቶ ኤኮኖሚያዊ ድርሻ ያላቸው እኒህ አገራት ሥምምነቱን ሲፈርሙ ኤኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር፤በየርስ በርስ ግብይት ቀረጥ ለመቀነስ እና እድገትን ለማበረታታት አቅደው ነበር። አገራቱ ከዚህ መለስ ያለ ሥምምነት ማዘጋጀት ቢችሉም ያለ ዩናይትድ ስቴትስ የትራንስ አትላንቲክ የንግድ ውል ኅልውና የሚታሰብ አይመስልም። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስን ከስምምነቱ ለማስወጣት ያስተላለፉት ትዕዛዝ ለቻይና ሌላ እድል ይዞ ከተፍ ያለ ይመስላል። ትራምፕ ውሳኔያቸውን ባስተላለፉ ማግሥት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ባልደረባ ሑ ቹንይንግ አገራቸው በቀጠናው የንግድ ልውውጥ የሚፈጠር ማንኛውንም ክፈተት ለመሙላት ዝግጁ መሆኗን ጠቁመዋል።«የእስያ ፓስፊክ ቀጣና የዓለም ኤኮኖሚ የደም ሥር መሆኑን እና ለዓለም እድገት አስተዋፅዖ ማበርከቱን ይቀጥላል። ሁሉንም አካታች እና ዘላቂ በሆነው የእድገት ጎዳና መዝለቅ ይኖርብናል። ትብብር እና እኩል ተጠቃሚነት ያሻናል።»

Xi Rede im australischen Parlament 17.11.2014
ምስል Reuters/D. Gray

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እርምጃ በአገራቸው የመኪና አምራቾች ዘንድ ውዳሴ ቢበረከትለትም ወቀሳም አላጣውም። የትራምፕ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ከሚያሰጋቸው የዩናይትድ ስቴትስ ባለሙያዎች በተጨማሪ ሥምምነቱን የፈረሙ አገራት መሪዎች እና ኩባንያዎች መከፋታቸውን አልደበቁም። በቅርቡ ከጀርመን የኤኮኖሚ ሚኒሥትርነት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተሸጋገሩት ሲግማር ጋብሬል ከምሥራቃውያኑ ጋር በንግድ የመተባበር ፍላጎት አገራቸው እንዳላት ጥቆማ ሰጥተዋል። 

«የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በዚያ የንግድ ግጭት መቀስቀስ ከፈለጉ እኛ ለእስያ አገሮች፤ ለቻይና እና ለሕንድ በመሰል ተግባር ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለን ልንናገር ይገባል። በሌላ በኩል ፍትሐዊ አጋር መሆን ይኖርብናል። ከቻይናም እንደዚያው ፍትሐዊነት እንጠብቃለን።» 
ዶናልድ ትራምፕ ሊከተሉት ሳያቅዱ አይቀርም የሚባልለት ዩናይትድ ስቴትስን ለይቶ የመጠበቅ ተግባር አገራት ከውጭ ኢንዱስሪዎች የሚገጥማቸውን ፍትኃዊ ያልሆነ ውድድር ለመግታት የሚከተሉት ሥልት ነው። ሥልቱ ከፖለቲካ የነቃ የመከላከል ተግባር እንደሆነ ይነገርለታል። ሥልቱን የሚከተሉ አገራትን ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት እና ዓለም አቀፍ ግብይት በረጅም ጊዜ ስለሚያዳክም አፍራሽ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አገራቱ ከውጭ በሚያስገቧቸው ሸቀጦች ላይ ቀረጥ በመጫን የውጭ ኩባንያዎችን ውድድር ለማዳከም የሚደረግ እርምጃ የዋጋ ንረት ስለሚያስከትል ሥጋት አብሮ ይጦ መምጣቱ አይቀርም። ኢፎ በተሰኘው የዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ጥናት ማዕከል ተንታኝ የሆኑት ጋብሪየል ፌልበርማየር ይኸው ንግድን ከውድድር የመከላከል ሥልት እንደገና እያንሰራራ እንደሆነ እምነታቸው ነው።

«ባለፉት አስር አመታት እንዲህ ውድድርን የመከላከል ሥልት ያን ያክል በዓለም ላይ አልታየም። አሁን ሲያንሰራራ እየተመለከትን ነው። በተለይ እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ያለ ግዙፍ አገር ከነፃ ገበያ መሸሽ  እንዲሁም በመላው ዓለም ለሸቀጦች፤ አገልግሎቶች እና ኃሳቦች ነፃ ዝውውር ዋስትና ለሚሰጠው የዓለም የንግድ ድርጅት የምታደርገውን ድጋፍ ማቀብ ሁነኛ ማሳያ ነው።» 
የዩናይትድ ስቴትስን እርምጃዎች ለሚከታተሉ ተንታኞችም ይሁን ፖለቲከኞች ዶናልድ ትራምፕ በበዓለሲመታቸው ያሰሙት ንግግር ውድድርን ለመከላከል የመሻታቸው ማረጋገጫ ነው። «አሜሪካ ትቅደም» ያሉት ዶናልድ ትራምፕ «ምርቶቻችንን፤ኩባንያዎቻችንን ከሚሰርቁ የሥራ እድሎችን ከሚያኮላሹ አገሮች ድንበሮቻችንን መጠበቅ ይኖርብናል። ነበር ያሉት። 

«እጅጉን አስገራሚ ነው። ይኸ ዩናይትድ ስቴትስ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ስትከተለው ከነበረው አካሔድ ማፈንገጥ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ እንደ ዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ናት። እነዚህ ተቋማት አገራት ከአፈሙዝ ይልቅ በህግጋት  በጋራ እንዲሰሩ ፤ እንዲገበያዩ እና ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ የሚሹ ናቸው። ከዚህ መርኅ ማፈግፈግ እጅጉን አስገራሚ ነው። ይኸ አሁን የምንመለከተው ወደ ተግባር አይሸጋገርም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።»

USA Trump-Unterstützer | Make America's Military great again
ምስል Getty Images/AFP/B. Wechter

እንደ ቻይና ሁሉ በዓለም ኤኮኖሚ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው አገራት የዶናልድ ትራምፕን እርምጃዎች በአንክሮ እየተከታተሉ ነው። ደፍረው የተቿቸው አማራጭ ማማተር የያዙም አልጠፉም። ጀርመናውያን ባለስልጣናት የአውሮጳ ኅብረት እንደ ጃፓን፤ኢንዶኔዥያ፤ማሌዥያ፤ሕንድ፤ቻይና እና ኒውዚላንድን ከመሳሰሉ አገራት ጋር የንግድ ሥምምነቶች እንዲያመቻች ጥሪ አቅርበዋል። የአውሮጳ የፋይናንስ ሚኒሥትሮች ጉባኤን የሚመሩት ሆላንዳዊው ይሩን ዳይጄስብሉም ቆፍጠን ብለው አህጉሯቸው በነፃ ገበያ ላይ ልትሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።«ልብ በሉ እኛ ውድድርን የምንከላከል አይደለንም። እኛ አውሮጳውያን በነፃ ገበያ ላይ መሥራታችንን መቀጠል ይኖርብናል። የሰራተኞች መብት እና የከባቢ አየር ጥበቃን የመሳሰሉ ሌሎች አውሮጳዊ የጥራት ደረጃዎቻችን እንዳሉ ሆነው ማለት ነው። የአውሮጳ ኮሚሽን በርካታ የነፃ ንግድ ሥምምነቶችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመፈጸም እየሰራ ነው። እስያ እና ላቲን አሜሪካን ጨምሮ ማለት ነው።»

Symbolbild EU USA Freihandelszone Gespräche
ምስል Georges Gobet/AFP/Getty Images

አፍሪቃ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የገባችው የእድገት እና ንግድ ውል በምሕፃሩ አጎዋ አገሮች በርካታ ሸቀጦችን ከቀረጥ ነፃ ወደ ዶናልድ ትራምፕ አገር እንድትልክ ይፈቅድላታል። በጎርጎሮሳዊው 2025 ዓ.ም.  ውሉ መታደስ አሊያም መሰረዝ ይኖርበታል። የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ውሉን ይሰርዘዋል የሚል ጭምጭምታ ቢሰማም እስካሁን በግልጽ የተባለ ነገር የለም። ከነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ውጪ አፍሪቃ በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ግብይት ውስጥ ያላት ድርሻ 2 በመቶ ብቻ ነው። ትራምፕ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ግብይቱን ካልፈለጉት ውሉ ለአገራቸው የሚፈይደው ስለመኖሩ በርካቶች ጥርጣሬ አላቸው።


እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ