1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻይና እና አፍሪቃ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 28 2000

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ያንግ ዢቺ የአራት የአፍሪቃ ሀገር ጉብኝታቸውን በዛሬው ዕለት ጀመሩ።

https://p.dw.com/p/E0Zx
የቻይናና የአፍሪቃ ግንኙነት ጥንካሬ ምልክት
የቻይናና የአፍሪቃ ግንኙነት ጥንካሬ ምልክትምስል AP
የቻይና ፕሬዚደንት ሁ ዢንታው ባለፈው አውሮጳዊ ዓመት በአፍሪቃ ካደረጉት ጉጉዞ በኋላ አሁን ቻይናዊው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደቡብ አፍሪቃን፡ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ፡ ቡሩንዲንና ግብጽን የሚጎበኙበት ድርጊት ቻይና የአህጉሩን ጥሬ አላባና የኃይል ምንጭን ለራስዋ ጥቅም ለማዋል ያላት ጽኑ ፍላጎት ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን ያሳያል። እአአ እስከ 2010 ዓም ድረስ ከአፍሪቃ ጋር የምታካሂደውን የንግድ ግንኙነት መጠን ወደ አንድ መቶ ሚልያርድ ዶላር በማሳደግ ትልቅዋ የአፍሪቃ የንግድ ተጓዳኝ የመሆን ፍላጎት አላት። ቻይና በአሁኑ ጊዜ ከዩኤስ አሜሪካና ከፈረንሳይ ቀጥላ ሶስተኛዋ የአፍሪቃ የንግድ ተጓዳኝ ናት። በአፍሪቃ በትልቅ ጥረት የተገኘው የሰብዓዊ መብት ይዞታ ደረጃ አሁን ቻይና ለአፍሪቃ በምትሰጠው ቅድመ ግዴታ ባላረፈበት የልማት ርዳታ እየተሸረሸረ ሄዶዋል በሚል ዋሽንግተን፡ ፓሪስና በርሊን ወቀሳ ሰንዝረዋል። እአአ ኅዳር 2006 ዓም በፔኪንግ በተካሄደው የቻይና አፍሪቃ ዓቢይ ጉባዔ ወቅት የቻይና አመራር ከተማይቱን የአፍሪቃን ገጽታ በሚያንጸባርቁ ቁሳቁሶች ያሸበረቁበትና ከአየር ማረፊያው እስከ መሀል ከተማ የሚወስዱትን መንገዶች በአፍሪቃውያቱ ሀገሮች ሰንደቃላማዎች ያስዋቡበትን ሁኔታ አፍሪቃውያኑ ፖለቲከኞች አሁንም በአድናቆት ያስታውሱታል። ያኔ ቻይና ላዘጋጀችው ጉባዔ ከአርባ ስምንት ያላነሱ አፍሪቃውያን መሪዎች ነበሩ ወደ ፔኪንግ የተጓዙት። ከዚያን ጊዜ ወዲህም ቻይና በአፍሪቃ ያካሄደችው የኤኮኖሚና የንግድ ግንኙነት መጠን እጅግ ነው የተስፋፋው። ቻይና ከአርባ አንድ ሀገሮች ጋር ልዩ አስተያየት የታከለበት የውጭ ንግድ ግንኙነት ስምምነት ተፈራርማለች። ቻይናዊው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዢቺ ዛሬ የከሚጎበኙዋት ደቡብ አፍሪቃም ጋር ነጻ የንግድ ስምምነት ለመፈራረም ድርድር ጀምራለች። እአአ ከ 1993 ዓም ወዲህ ብቻ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በንግድ ወደ ሀገርዋ ማስገባት የጀመረችው ቻይና በወቅቱ ለሀገርዋ ከሚያስፈልጋት የኃይል ምንጭ መካከል አንድ ሶስተኛውን የምትገዛው ከአፍሪቃ ሲሆን፡ ይህ ለአፍሪቃ አስራ ሶስት ሚልያርድ ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል። በአፍሪቃ ከርሰ ምድር የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት ለመቆጣጠር የሚደረገው የመጨራመት መፎካከር ተግባር ከተጀመረ ሰንበት ብሎዋል። ቅኝ ገዢዎች አፍሪቃን በመካከላቸው የተከፋፈሉበት የበርሊን ጉባዔ ከተካሄደ ከአንድ መቶ ሀያ ዓመታት ወዲህ፡ በወቅቱ ከብሪታንያና ከፈረንሳይ ጎን፡ ቻይናና ዩኤስ አሜሪካም በአህጉሩ ለማንሰራራት ከፍተኛ ጥረት ሲያካሂዱ ይታያል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ርዳታ ተቀባይ የነበረችው ቻይና አሁን ርዳታ ሰጪ ሀገር በመሆን፡ ለአፍሪቃ ቅድመ ግዴታ ያላረፈበት ግዙፍ ብድር ማቅረብ የያዘችበት ሁኔታ አውሮጳውያኑን አሳስቦዋል። ቻይና ከአንጎላ ጎን በሰብዓዊ መብት ይዞታቸው የሚወቀሱትን ሱዳንና ዚምባብዌንም እንደ ዋነኞችዋ ተጓዳኞችዋ የምትመለከትበት አሰራርዋ አውሮጳውያኑን አስቆጥቶዋል። በሀምበርግ የሚገኘው የአፍሪቃ ጥናት ተቋም አስተንታኝ እንደ ዶክተር ማትያስ ባዜዳው አባባል፡ በአህጉሩ የሰብዓዊ መብት ይዞታ እንዳይሸረሸር አውሮጳውያኑ የሚያሰሙት ማስጠንቀቂያ ውጤት ማስገኘቱ አጠራጣሪ ብቻ ሳይሆን ለይስሙላ የሚሰነዘር አስመስሎታል።
« ዴሞክራሲያውን ሂደት ለማጠናከር የሚደረገው ጥረት አማራጭ ተጓዳኝ ካለና በተለይም ይኸው ተጓዳኝ ይህንን ጥያቄ የማያቀርብ ከሆነ፡ ጥረቱ አዳጋች እንደሚሆን ግልጽ ነው። በሌላ በኩል ግን፡ ባለፉት ጊዚያት፡ በተለይ ጥሬ አላባን በተመለከተ፡ አፍሪቃውያኑ መንግስታት ሙስናን እንዲተውና ዴሞክራሲያዊ አሰራርን እንዲከተሉ የቀረበው ግፊት ከምዕራቡ ዓለምም በኩል ቢሆን ጠንካራ አልነበረም፤ በዚህ ነጥብ ላይ ግለ ወቀሳ አስፈላጊ ይሆናል። »

አፍሪቃውያን ፖለቲከኞች ቻይና የምትከተለውን በእኩልነት ላይ የተመሰረተውን ጉድኝት በማሞገስ የፓሪስና የበርሊንን አሰራር ይወቅሳሉ። ይኸው የቻይና የግንባታና የመሰረተ ልማት ዘርፍ፡ እንዲሁም የምትሰጠውን አማላዩን ብድር የሚመለከተው ሞገስ ግን የአፍሪቃውያኑን ገበያዎች ጥራቱ ያን ያህል ባልሆነው የቻይና የፍጆታ እና የጨርቃ ጨርቅ ምርት ብቻ ነው ያጥለቀለቀው።
በታንዛንያ ለምሳሌ OK Plast የተባለው ፕላስቲክ አምራች ኩባንያ በቻይና ግፊት የተነሳ የሰራተኞቹን ቁጥር ከሶስት ሺህ ወደ አንድ ሺህ ዝቅ ማድረግ ተገዶዋል።
ያንግ ዛሬ ውይይት በሚያካሂዱባት ደቡብ አፍሪቃም ውስጥ ባለፉት አሰርተ ዓመታት እንዲሁ በጫይና ግፊት ሰበብ ሰባ አምስት የስራ ቦታዎጭ መዘጋታቸውን ደቡብ አፍሪቃውያኑ አሁንም አልረሱትም። በሰበቡም ተቋማት፡ የሙያ ማህበራትና የመገናኛ ብዙኃን ተገቢውንና የተሳካውን የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውን በጆሀንስበርግ ከተማ የቻይና ጥናት ኤኮኖሚ ጠቢብ ሃና ኤዲንገር ያስታውሳሉ።
« የደቡብ አፍሪቃ ምሳሌ ቻይና ገላጋይ ሀሳብ ለመድረስ ዝግጁ መሆንዋን ያሳያል። ደቡብ አፍሪቃ ከቻይና ለምትገዛው ልብስና ጨርቃጨርቅ በምላሹ ቻይናን ሰላሳ አንድ ግዴታዎችን እንድታሟላ አድርጋለች። በዚህም ደቡብ አፍሪቃ ከቻይና ለሚደቀንባትን ፉክክር ራስዋን ቀስ በቀስ ማዘጋጀት ያስችላታል። በመሆኑም፡ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ከቻይና ጋር ለመደራደር ይቻላል ብዮ አምናለሁ። »
ይሁን እንጂ፡ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ታቦ ምቤኪ ቻይና የቅኝ አገዛዝ ፖሊሲ እንዳትከተል ከማስጠንቀቅ ወደ ኋላ አላሉም። እንደ ዶክተር ማትያስ ባዜዳው አባባል፡ ቻቅና በአፍሪቃ የጀመረችው ታታሪነት አህጉሩን የሚጠቅምበት ወይም የሚጎዳበት ሁኔታ በያንዳንድዋ አፍሪቃዊት ሀገር ፖለቲከኞች ላይ ጥገኛ ይሆናል።
« የቻይና ታታሪነት ለአፍሪቃ ቡራኬ ወይም ርግማን መሆን አለመሆኑ በያንዳንዱ መንግስት አሰራር ላይ ጥገኛ ይሆናል። የጋራ ብልጽግና ማስገኘት የሚሰኘውን ሀሳብ የሚያስቀድም መንግስት ከቻይና ጋር የሚደረገውን ግንኙነት ጠቃሚ ሊያደርገው ይችላል። ይህን አስተሳሰብ የማያስቀድም ግን በህዝቡ ላይ ጉዳት ያስከትላል። »
ሃና ኤዲንገርም ተመሳሳዩን አስተያየት ነው የሰጡት።
« ከቻይና ጋር ከሚደረገው የንግድ ግንኙነት የሚገኘውን ትርፍ ወደ ባለስልጣናቱ የባንክ የቁጠባ ደብትእ እንዳይገባ እና ለሰፊው ህዝብ ትቅም እንዲውል ማድረጉ የአፍሪቃውያኑ መሪዎች ኃላፊነት ነው። »