1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻይና በጅቡቲ የጦር ሰፈር ለማቋቋም ማሰቧ

ሰኞ፣ ግንቦት 3 2007

ቻይና በጅቡቲ ዉስጥ የጦር ሰፈር ለመመስረት ማቀዷን ተዘገበ። የፈረንሳይ፤የጃፓን እና ዩ.ኤስ አሜሪካ በትንሺቱ የአፍሪቃ ቀንድ ሐገር የጦር ሰፈር ያላቸው ሲሆን የቻይና ከተረጋገጠ አራተኛዋ ሐገር ትሆናለች።የጂቡቲዉ ፕሬዝደንት እስማኤል ኡመር ጉሌሕ የቻይናን ፍላጎት በደስታ እንደሚያስተናግዱት አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/1FOI2
Dschibuti/ Soldaten/ US-Stützpunkt
ምስል picture-alliance/dpa

ቻይና በጅቡቲ ሰሜናዊ የወደብ ከተማ ኦቦክ የጦር ሰፈር ልትመሰርት ምክክር መጀመሩን የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌሕ ለአዣንስ ፍራን ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ሌሞኒየርን ጨምሮ የፈረንሳይ እና ጃፓን ጦር ሰፈሮች በጅቡቲ ይገኛሉ። የቀድሞዋ የጅቡቲ ቅኝ ገዢ የፈረንሳይ የጦር ሰፈር ከሁሉም ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ነዉ።የአሜሪካዉ ደግሞ በየመን እና ሶማሊያ ለሚደረገው የጸረ-ሽብር ዘመቻ መነሻ ሆኖ ያገለግላል።

የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ቻይና እንደቀደሙት ሶስት አገሮች ሁሉ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ማቀዷን ተናግረዋል። መቀመጫውን በለንደን ባደረገው ቻታም ሐዉስ አለም አቀፍ ጉዳዮች ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ጉዳዮች ረዳት ተመራማሪ አህመድ ሱለይማን ቻይና በሁለት ምክንያቶች በጅቡቲ መገኘት ፈልጋለች ይላሉ።

China Somalia Einsatz gegen Piraten
ምስል AFP/Getty Images/T. Aljibe

«ጅቡቲ አፍሪቃን ከመካከለኛው ምስራቅ ከሚለየው የባብ አል-ማንደብ የባህር ወሽመጥ ፊት ለፊት የምትገኝ አገር ናት። ቦታው በዓለም በርካታ መርከቦች የሚተላለፉበት መስመር ነው። የቻይና መርከቦችም በዚሁ ነው የሚተላለፉት። በጎርጎሮሳዊው 2008 ዓ.ም. በአካባቢው የተከሰተው የባህር ላይ ውንብድና ለአለም አቀፍ ማህበረሰብና የባህር ሃይል ቁልፍ ቦታ እንዲሆን አድርጎታል። ጅቡቲም ቀድሞ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ከሆኑት ከፈረንሳይና ጥቂት የአውሮጳ አገሮች ጋር ተወስኖ የቆየውን ግንኙነቷን ትፈልጋለች።»

ቻይና ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሚሰሩ የባቡር ትራንስፖርት፤አውሮፕላን ማረፊያ እና መኪና መንገድ ሥራን ለመደገፍ ከ9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች። በርካታ የቻይና ኩባንያዎችን የተቀበለችው ኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ በጅቡቲ ወደብ ላይ የተንጠለጠለ ነው።

በጎርጎሮሳዊው 2014 ቻይና እና ጅቡቲ፤ የቻይና የጦር መርከቦች የጅቡቲ ወደብን እንዲጠቀሙ የሚፈቅድ ውል ሲፈራረሙ ዩ.ኤስ. አሜሪካ ተቆጥታ ነበር።አሁን ቻይና ከሌሞኒየር የጦር ሰፈር በቅርብ ርቀት መገኘት የሚኖረው ፖለቲካዊ ትርጓሜ ገና አልታወቀም።ቢሆንም አገሪቱ ከአሁን ቀደም የንግድ መርከቦቿን ከአደጋ ለመጠበቅ ከዩ.ኤስ.አሜሪካ፣የአውሮጳ አገራትና ሩሲያ ጋር ስታደርግ የነበረው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚሉት አህመድ ሱለይማን ለአፍሪቃም ፋይዳ እንዳለው ይናገራሉ።

US-Luftsstützpunkt Hoedspruit Afrika Amerikanische Hubschrauber treffen in Mosambik ein
ምስል picture-alliance/dpa

«የቀጠና ትስስር በምስራቅ አፍሪቃ አገራትና በምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ይመስለኛል። ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው የላፕሴት የመንገድና (LAPSSET Corridor Projects) የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት እቅዶች ለዚህ ማሳያ ናቸው። የብዙዎቹ የሚገነቡት በቻይና ገንዘብ፤ጉልበትና ቴክኖሎጂ ነው።ይህ በቀጣናው የንግድ ግንነትን እና የሰዎችን እንቅስቃሴ ያሳድጋል።አሁን የምናያቸውን አለመረጋጋቶችና ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን ለማስወገድና ይረዳል።»

ከቀይ ባህር እና ከስዊዝ ካናል አቅራቢያ የምትገኘው ጅቡቲ ከቻይና የመጣውን ወዳጅነት አጥብቃ የምትሻው ትመስላለች። ባለፈው አመት የአገሪቱ ግዙፍ ወደብ የማስተዳደሩን ስራ ተረክቦ ከነበረው የዱባይ አለም አቀፍ ወደቦች ኩባንያ (Dubai Ports World) በመረከብ ለቻይናውያን ለመስጠት የጅቡቲ መንግስት መወሰኑ አይዘነጋም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሀመድ