ቻርልስ ቴይለርና የእሥራቱ ቅጣት
ሐሙስ፣ ግንቦት 23 2004
ፍርድ ቤቱ ባለፈው ወር ነበር ቴይለርን በዘጠነኛዎቹ ዓመታት የሲየራ ልዮን የተባበረው ዓብዮታዊ ግንባር ዓማፅያንን ረድተዋል በሚል ጥፋተኛ ናቸው ሲል ብይን ያሳለፈው። ጥፋተኛ እንዳልሆኑ ያስታወቁት የስድሳ አራት ዓመቱ ቻርልስ ቴይለር በብይኑ አንጻር ይግባኝ ሳይሉ እንደማይቀሩ ይጠበቃል።
« ሚስተር ቴይለር፡ በሚቀጥሉት ምክንያቶች ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙባችው ወንጀሎች በሀምሣ ዓመት እሥራት እንዲቀጡ በአንድ ድምፅ በይኖዋል። ብይኑ ተይዘው ከታሰሩበት እአአ ከመጋቢት 2006 ዓም ጀምሮ የፀና ይሆናል። »
ዳኛው ሪቻርድ ሉሲክ የእሥራቱን ቅጣት ይፋ ባደረጉበትና ያጠፋ ሁሉ በሕግ እንደሚጠየቅ ባስታወቁበት ጊዜ ያሰሙትን ብይን ነበር ያዳመጣችሁት።
ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ በናዚ ባለሥልጣናት አንጻር ከተካሄደው ችሎት በኋላ አንድ የሀገር መሪ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ብይን ሲተላለፍበት የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለር የመጀመሪያው ናቸው። ቴይለር እአአ በ 2002 ዓም ባበቃው የሲየራ ልዮን የርስ በርስ ጦርነት ወቅት እጅና እግር በመቁረጥ የጭካኔ ተግባራቸው ይታወቁ የነበሩትን የተባበረው ዓብዮታዊ ግንባር ዓማፅያንን ረድተዋል በሚል ተከሰው እአአ በ 2006 ዓም በስደት ይኖሩባት ከነበረችው ናይጀሪያ ተይዘው በሲየራ ልዮን ወደተቋቋመው የተመድ ጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ተወሰዱ፤ የርሳቸው የፍርድ ሂደት በሲየራ ልዮን የሚካሄድበት ድርጊት ግን ያካባባውን መረጋጋት ያደፈርሳል በሚል ስጋት ችሎታቸው ወደ ዴን ኻግ ከተዛወረ በኋላ ፍርድ ቤቱ ባለፈው ወር ቴይለርን በአሥራ አንድ የክስ ወንጀልዎች ጥፋተኛ ሆነ አግኝቶዋቸዋል። በዛሬው ዕለትም የሀምሳ ዓመት እሥራት በይኖባቸዋል። በዘጠነኛዎቹ ዓመታት ከነበሩት ጨካኝ የጦር ባላባቶች መካከል አንዱ የሚባሉት የስድሳ አራት ዓመቱ ቻርልስ ቴይለርን ችሎት ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ሲከታተሉ የቆዩት ኦፕን ሶሳይቲ ጃስቲስ ኢኒሺየቲቭ የተባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን መሪ ጠበቃው የሲየራ ልዮኑ ተወላጅ አልፋ ሴሴይ ብይኑ አስደሳችና ለሌሎችም መቀጣጫ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል።
« ወሳኝ ወቅት ነው፤ ብይኑ ቅር የሚያሰኝ አይደለም፤ ብዙዎቹ የሲየራ ልዮን የጦር ወንጀል ሰለባዎች ቻርልስ ቴይለር ዕድሜ ይፍታህ እንዲፈረዱ ነበር የጠበቁትና ይህ ደግሞ የዕድሜ ልክ እሥራት ነው። እርግጥ ይህ በሲየራ ልዮን የርስ በርስ ጦርነት ወቅት የተፈጸመውን የጦር ወንጀል ሁሉ ያበቃል ማለት አይደለም። ግን የሕግ የበላይነት እንደሚከበር፡ በተለይም ዳኛው እንዳስታወቁት፡ እንደ ቴይለር ትልቅ ሥልጣን ያላቸው ሰዎችም ሳይቀሩ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ያሳያ ወሳኝ ምልክት አስተላልፎዋል። »
በሲየራ ልዮን የተቋቋመው የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ቃል አቀባይ ፒተር አንደርስም የፍርድ ቤቱን ብይን እንደ ትልቅ ስኬት ነው የተመለከቱት።»
« በዚህና በሌሎች አካባቢዎች ትልቅ ሥልጣን ያለህ ሰው ከሆንክ በፍርድ ፊት የማትጠየቅበት ጊዜ ነበር። እና ልዩው ፍርድ ቤት በፍፁም አይነኩም ተብለው ይታሰቡ የነበሩ ሰዎችን በከሰሰበት ድርጊቱ ማንም በሕግ ሊቀጣ እንደሚችል ዋነኛ ርምጃ ወስዶዋል።
እአአ ከ 1991 እስከ 2002 ዓም በቆየው የርስበርስ ጦርነት ወደአንድ መቶ ሀያ ሺህ ሰው ሲገደል፡ በዚሁ ጊዜ የተባበረው ዓብዮታዊ ግንባር ዓማፅያን በፈፀሙት ዘግናኙ የእጅና እግር መቁረጥወንጀል ከአምስት ሺህ የሚበልጥ ሰው ሰላባ ሲሆኑ፡ ብዙ ሴቶችም ባማፅያኑ መደፈራቸው ይታወቃል።
የዛሬውን የፍርድ ቤት ብይን በሲየራ ልዮን መዲና ሊብረቪል በቀጥታ በቴሌቪዥን ከተከታተሉት ሰለባዎች አንዱ የቀኝ እጁ የተቆረጠው አሊማሚ ካኑ በብይኑ እጅግ መደሰቱን፡ የግራ እግሯን ያጡት ሲያህ ሊቢ ደግሞ የዛሬው ብይን መጥፎ ስራ ለመስራት ለተዘጋጁ ሁሉ ጥሩ ማስጠንቀቂያ እንደሚሆን ገልጸዋል።
እርግጥ ፍርድ ቤቱ በቴይለርና ረዱዋቸው በተባሉት የዓብዮታዊ ግንባር ዓማፅያን መሪዎች ላይ የቅጣት ብይን ማስተላለፉ የመጀመሪያ ርምጃ ቢሆንም፡ አሁንም ብዙዎቹ የጦር ወንጀለኞች በሲየራ ልዮን ክስ ሳይመሰረትባቸው በነፃ በመዘዋወር ላይ መገኘታቸው ፡ ምንም እንኳን ጦርነቱ ቢያበቃም አሁንም ኑሮዋቸውን የመግፋት ችግር ያልተለያቸውን ያማፅያኑ ወንጀል ሰለባዎችን ቅር ማሰኘቱ አልቀረም።
አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ