1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ግንቦት 30 2011

«ህወሀት በ1983 የተከለው የጎሳ ፖለቲካ የመጨረሻው ውጤት አሁን እየተቃረበ ነው። በወጣቱ እና በህብረተሰቡ እሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው። የዚህች ሀገር ፖለቲከኞች ነን ለሚሉት አዝናለሁ» ይላል የሳሙኤል ገብረ ሥላሴ መልዕክት። 

https://p.dw.com/p/3K2ZZ
Äthiopien Axum-Universität in der Region Tigray
ምስል DW/M. Hailesilassie

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ቶቶ የተባለው አስጎብኚ ድርጅት ለተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች ወይንም ለግብረ ሰዶማውያን ደንበኞቹ በኢትዮጵያ ያቀደው የጉብኝት መርኃ ግብር ብዙዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሐሳብ የተለዋወጡበት ርዕሰ ጉዳይ ነው። በአክሱም ዩኒቨርስቲ በተነሳ ኹከት የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉ ሌላው የሰሞኑ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። 

ግንቦት 27፣ 2011 ዓ.ም በአክሱም ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ኹከት ዮሐንስ ማስረሻ የተባለ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የ2ተኛ ዓመት የመካኒካል ኢንጅነሪንግ ተማሪ ሕይወት ማለፉ እና ሌሎች 7 ተማሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ልዩ ልዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። ብሔርን መሠረት ያደረገ ያለውን የተማሪውን ግድያ ዩኒቨርስቲው የሚገኝበት የትግራይ ክልል አውግዟል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል አስነዋሪ ባሉት በዚህ ግድያ  የተጠረጠሩ እንደተያዙ ሌሎችም እየታደኑ መሆኑን በግድያው ማግስት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ይህን መግለጫ መነሻ ያደረጉ ከተቃውሞ እስከ ቁጣ፣ ከምክር እስከ ልመና የደረሱ ልዩ ልዩ አስተያየቶች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተንሸራሽረዋል። 

ቲጂ በለጠ በፌስቡክ በአጭሩ «ምን ይፈይዳል የሐዘን መግለጫ ነብስ አይመልስም» ሲሉ፤ ልዩነት አለ በሚል የፌስ ቡክ አድራሻ ተጠቃሚ አስተያየት ሰጭም፦ «አዴፓ እና ህወሓት ግን በየሳምንቱ መግለጫ እያወጣቹ ስትነቋቆሩ ትከርሙና ምስኪን የደሀ ልጆችን ለመስዋእት ታቀርባላችሁ። ከዚያም መልሳችሁ እንደገና መግለጫ። ልጄ ተምሮ ተለውጦ ነገ ይጦረኛል ይደርስልኛል ብሎ በተስፋ እየጠበቀ ልጁን ላጣ ወላጅ የናንተ የአዞ እምባ አይነት መግለጫ ምን ይጠቅመዋል? »ሲሉ ይጠይቁና «በልቶ ማደር ፈተና የሆነበት ህዝብ እየመራችሁ እናንተ ግን በሴራ ፖለቲካ ተጠምዳችኋል። እውነት ግን ለስልጣን እድሜአችሁ የምትጨነቁትን ያህል ለዚህ ህዝብ ትጨነቃላችሁ? እንኳን እየተባላን ይቅርና አንድ ሆነንም መከራችን ብዙ ነው። እባካችሁ የምትመሩትን ህዝብ በደንብ እወቁት» ሲሉ ትችታቸውን በምክር ደምድመዋል። 

Bildergalerie Axum
ምስል DW/G. Tedla

«ህወሀት በ1983 የተከለው የጎሳ ፖለቲካ የመጨረሻው ውጤት አሁን እየተቃረበ ነው። በወጣቱ እና በህብረተሰቡ እሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው። የዚህች ሀገር ፖለቲከኞች ነን ለሚሉት አዝናለሁ» ይላል የሳሙኤል ገብረ ሥላሴ መልዕክት። 
የአክሱም ዮኒቨርስቲ ለተማሪው ሞት ምክንያት የሆነው ኹከት መነሻ ባለፈው ሳምንት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ መንገድ ከተፈጸመው የተማሪ ግድያ ጋር የተያያዘ ነው ተብሎ ሊገመት እንደሚችል ጠቁሟል። ያሬድ አስፋው «እንዲያው በየዩኒቨርሲቲዎቹ የሚማሩት መጋደል ነው እንዴ? ከዛ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ደግሞ "ምሁራን" ይባላሉ። ድንቄም ምሁራን። እንዴት ያሳዝናል» ሲሉ «የተዘራውን የማንነት መርዝ ኮሌጆች እያጨዱት ይገኛሉ። ይህ የሚወስደን ወደ ሩዋንዳ ሁቱ ቱትሲ ትልቅልቅ መሆኑን ሁሉም ልብ ይበል። የኳስ ሜዳና ዩኒቨርስቲዎች በመከላከያ ሠራዊት ስር ይሁኑ አልያም ይዘጉ» ሲሉ  የድርጊቱ መጨረሻ እንደማያምር ገልጸው መፍትሄ ያሉትንም የጠቆሙት ደግሞ ተድላ አስፋው ናቸው። ጠና ደስታ «በጣም ያሳዝናል ሰው በሀገሩ ላይ በሀገሩ ሰው መገደሉ የሚያሳዝን ነገር ነው:: እግዚአብሔር ነፍሱን ይማረው» ሲሉ ሚኪ ብር የተባሉ አስተያየት ሰጭ ደግሞ ለዩንቨርስቲ ተማሪዎች ወንድማዊ ያሉትን የሚከተለውን ልመና አዘል ምክር አስተላፈዋል። 

«እባካችሁ ስለ እግዚያብሔር፣ ስለ አላህ ብላችሁ፤ መማር ማለት ትዕግስት፣ እግዚአብሔርን መፍራት፣ የሰውን ልጅ በሰውነቱ ማክበር፣ ለሀገር እድገት መጣር መሆኑን አውቃችሁ በትእግስት ይህን ጊዜ ለማለፍ ሞክሩ። ጥላቻ ቤት አይሰራም፤ ፍቅር ተራራን አፍርሶ የተለያየን የተራራቀን ያገናኛል። አንድ ደብረ ማርቆስ አንድ አክሱም…….ከዚያስ በቀል በቀልን እየወለደ ሌላ እልቂት እንዳይመጣ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ያሉ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ተማሪዎችን ደህንነት ሊያስጠብቅ ይገባል» የሚለውን መልዕክት እዮብ ደበበ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።

Bet Giyorgi Felsenkirche von Lalibela in Äthiopien
ምስል picture alliance/Robert Harding World Imagery

ናርዶስ አበበ እንዲሁ በትዊተር ጽሑፉቸው፦ «በአክሱም ዩኒቨርስቲ ተማሪ ላይ የተፈጸመው ግድያ እጅግ ያሳዝናል ይህ በመንጋ ፍርድ መግደል በሀገራችን እየተለመደ መጥቷል። መፍትሄው አንድ እና አንድ ብቻ ነው የጎሳ ፖለቲካን በሕግ ማገድ» ብለዋል። አማር ቢን ያሲር «ልጇን ዩኒቨርስቲ የላከች እናት ዳግም አስከሬን እንዳትቀበል ከተፈለገ መንግሥት ሕግ ማስከበር እስከሚችል የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት ይዘጉ» ሲሉ መፍትሄ ያሉትን አካፍለዋል። 

በዚህ ሳምንት ሌላው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲያነጋግር የከረመው መቀመጫውን ቺካጎ አሜሪካን ያደረገው ቶቶ የተባለው አስጎብኚ ድርጅት ለተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች ወይንም ግብረ-ሰዶማውያን  በኢትዮጵያ ያቀደው የጉብኝት መርሃ ግብር ነበር። ቶቶ በኢትዮጵያ ከአራት ወራት በኋላ ለ16 ቀናት የሚዘልቅ የጉብኝት መርሃ ግብር ማዘጋጀቱን በድረ ገጹ ባወጣው ማስታወቂያ ላይ አስፍሯል። ጉብኝቱም አርባ ምንጭን የጫሞ ሀይቅን ኮንሶን ሀመርን የጣና ገዳማትን ጎንደር ላሊበላ አክሱም ውቅሮ እና ሌሎች ታሪካዊ ቤተ እምነቶችን ያካትታል። 
ይህ የጉብኝት መርሃ ግብር ከተለያዩ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ማህበራት እና የማህበረሰብ ክፍሎች ተቃውሞ እና ውግዘት ደርሶበታል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ላሊበላ ደብር ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በቶቶ እቅድ ላይ ተቃውሞአቸውን በቅድሚያ ካሰሙት መካከል አንዱ ነው። ጽሕፈት ቤቱ ግንቦት 26 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ባወጣው እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተሰራጨው መግለጫ፦ «ነውረኛ» ያለው አስጎብኝው ድርጅት፣ «በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የላሊበላ ውቅር ዐብያተ-ክርስቲያን ለማስጎብኘት ማሰቡ ከአማኞች አልፎ ህዝቡንም ያስቆጣ «ድፍረት» ብሎታል። ጽሕፈት ቤቱ ቢቻል ጎብኚዎቹ ወደ አገር እንዳይገቡ ቢደረግ ሲል ጠይቆ የሚመጡ ከሆነ ግን ለመግባት እንደማይፈቀድላቸው አስጠንቅቋል። ለሚፈጠረውም ችግር ኃላፊነቱን እንደማይወስድ አሳስቧል። 
ተመሳሳይ ተቃውሞ ካሰሙት ውስጥ የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ጉባኤ አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ 7 የእስልም እና የክርስትና ሃይማኖቶች የተወከሉበት ይኽው ጉባኤ ግብረሰዶማዊነት እንደሚያወግዝ አስታውቆ የሀገር ቅርስ እና ታሪካዊ ቦታዎችን ዒላማ ያደረገ የግብረ ሰዶማውያንን እንገናኝ መልዕክቶችን እና ቀጠሮዎችን እንዲያስቆም መንግሥትን ጠይቋል። መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣም የጉባኤው ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሊቀ- ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።  

Bildergalerie Axum
ምስል DW/G. Tedla

ከ120 በላይ የኦርቶዶክስ ማኅበራት ስብስብ የሆነው «ሰልስቱ ምእት የማህበራት ህብረት» የቶቶን የጉብኝት መርሃ ግብር እቅድ ተቃውመው ድምጻቸውን ካሰሙት መካከል ይገኝበታል። የቶቶ የጉብኝት መርሃግብር በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍልም ቁጣ፣ ውግዘት እና ማስጠንቀቂያ ደርሶበታል። ፀጋዬ አበበ በትዊተር ገጹ፦ «አሁን ገና የመጥፋት ጊዜውን አፋጠነ። ቶቶ ሳይሆን እረ ተው ተው ሊባል የሚገባ ተግባር ነው። ወገኔ ጠላት አይኑን አፍጥጦ ጥርሱን አግጥጦ ታሪክህን ሊያበላሽ መጥቷል» ብሏል። 
ዩኒስ ሻሚል በፌስቡክ ገጻቸው «አሜሪካኖቹ አሸባሪ የሚሏቸውን ግለሰቦች ድርጅቶችና የሃገራት ዜጎች ሃገራቸው እንዲገቡ አይፈቅዱላቸውም እኛ ስለምንድነው ከሃገራችን ሃይማኖት ባህልና እሴት ተጻራሪ የሆኑ ቡድኖች ሃገራችን እንዲገቡ የምንፈቅደው? ይህ የሞራል ሉአላዊነት ድፍረት ነው።» ሲል ጽፈዋል
በቀለ ተሾመ እንዲሁ በትዊተር፦ «እውነት ነው እኛ ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይ ነን። መቀበል ብቻም ሳይሆን ዝቅ ብለን እግር እናጥባለን የተመቻቸ የምንለውንም መኝታ ለቀን ወለል ላይ እንተኛለን ያለንንም ሳንሰስት እንሰጣለን። ይህ ይሁን የሚያስብል ባህላችን ነው። ላልመሰለለን እንግዳ ደግሞ መራር እና ርምጃ ለመውሰድ ወደ ኋላ የማንል ነን። ስለዚህ መንግሥት ይገባሉ እየተባለ የሚወራው ግብረሰዶማዊያኑ ቶቶ አስጎብኚ ድርጅት የህዝብን ሞራል እና ሃያማኖት የሚጋፋ ስለሆነ የመከላከል ግዴታ አለብህ። ካልሆነ ህዝቡ ራሱን ላለማስደፈር ይጥራል። መንግሥት ለምን የህዝብን ፍላጎት አያከብርም እነሱ መጥተው የሚያስገኙት ገቢ ገድል ይግባ» ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሮማን ጂ ተሾመ በሚል ስም በትዊተር «ማንም በወሲብ ዝንባሌው ምክንያት ሊገለል እና ሊዋከብ አይገባም ይህ የሰው ልጅ መሠረታዊ መብት ነው» ሲሉ
ዮናስ ፋልስ በሚል ስም በትዊተር «ግብረ ሰዶማዊነት በሃያማኖታዊ ቦታዎች ዙሪያ ሊፈቀድ አይገባም ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን ሊያስከትል የሚችለውን ኤኮኖሚያዊ መዘዝ ሊረዱት ይገባል» ብሏል።  ለዚህ አስተያየት ሲልቬስተር ኦቦጉሉ የተባሉ በትዊተር በሰጡት መልስ «በጥቅሉ ከእግዚአብሔር የተሰጠንን የኦርቶዶክስ ክርስትና ውርስ እና እንደ ቅድስት ሀገር ያለንን ሥነ መለኮታዊ ቦታ እና የቃል ኪዳን ጠባቂ አገርነት ሊያስተው የሚችል ምን ያህል ገንዘብ ይዘው ይመጡ ይሆን?ሲሉ ይጠይቁና መልሰው ይህን ለመግለፅ አስቸጋሪ የሆነውን ነገር ለማግኘት፣ ስንት ትሪሊዮን ዶላር ትከፍላለህ ሲሉ ገንዘብ ከክብር እና ከመንፈሳዊ ሀብት እንደማይበልጥ» በጽሁፋቸው አስፍረዋል።
ቲጂ የማርያም ልጅ የሚል የፌስ ቡክ ስም ተጠቃሚ ደግሞ «በዘር ተከፋፍለዋል ምንም አያደርጉንም ብለው ከሆነ በእውነቱ ተሳስተዋል።የቤተሰብ_ጠብ መሆኑን አልገባቸውም ።እኛ ኢትዮጵያውያን በማንነታችን እና በሀይማኖታችን"የማንዳራደር ፈጣሪያችን የምንፈራ ኩሩ ህዝብ ነን።መጥፍያቸው ደርሶ መሰለኝ።»ብለዋል።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ