1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታጣቂዎቹ መንግሥትን ንቀውት ይሆን?

ዓርብ፣ ጥቅምት 2 2011

በቅርቡ ወደ አገር ቤት ለሠላማዊ የፖለቲካ ውድድር የተመለሱት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መሪ ዳውድ ኢብሳ በቅርቡ ስለትጥቅ መፍታት አለመፍታ ለተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች የሰጧቸው መግለጫዎች እና ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር የገቡበት እሰጣገባ ሳይቋጭ፣ የሠራዊቱ ልዩ ኃይል አባላት ትጥቃቸውን ሳይፈቱ ሰልፍ መውጣታቸው ተሰማ፡፡

https://p.dw.com/p/36PqB
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

ይህ ነገር የነጻነት መገለጫ ነው ወይስ የቀውስ አዝማሚያ?

ከኦነግ እስከ ልዩ ኃይሉ
አቶ ዳውድ ኢብሳ ከአገር ውስጥ ብዙኃን መገናኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ትጥቅ ማስፈታት የሚለው ንግግር ‹ሴንሲቲቭ› ነው፤ ማነው ፈቺ? ማነው አስፈቺ?” ብለው ሲናገሩ መጀመሪያ ላይ የአፍ ወለምታ ይመስል ነበር፡፡ ይሁንና እየቆዩ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በሰጧቸው ማብራሪያዎች ግን ከመንግሥት ጋር በተደረገው ድርድር “ትጥቅ መፍታት” ስለሚባል ነገር እንዳልተነጋገሩ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ መስከረም 30፣ 2011 አዲስ አበባ ተሸብራ ዋለች፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በተለምዶ ‹ቀይ ለባሾች› እየተባሉ የሚታወቁት የጦር ሠራዊቱ አባላት አራት ኪሉ አካባቢ ተሰብስበው መታየታቸው ነው፡፡ ከዚህ በፊት አድማ እና ሰልፎችን ለመበተን ይታዩ የነበሩት የሠራዊት አባላት መሣሪያዎቻቸውን እንዳነገቱ ሰልፈኛ ሆነው መታየታቸው ተሰማ፡፡ ይህ ያልተለመደ ትዕይንት ‹ጉዳዩ መፈንቅለ መንግሥት ነው እንዴ?› እስከሚባል ድረስ አደናጋሪ ነበር፡፡ ወደ ቤተ መንግሥቱ የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ ተዘጉ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የተንቀሳቃሽ ስልክና የብሮድባንድ የኢንተርኔት ግንኙነቶች ተቋረጡ፡፡ ይህም የክስተቱን ምሥጢራዊነት ስላባባሰው ፍርሐቱ በከተማዋ ላይ ነገሠ፡፡ በዚያ ላይ የወታደር መኪናዎች በየአቅጣጫው ውር ውር ሲሉ ይታያል፤ የጦርነት ድባቡ ሙሉ ሊሆን የቀረው የተኩስ ድምፅ ብቻ ነበር፡፡
ከሁለት ሰዐታት በኋላ የታገደው ኢንተርኔት ግንኙነት ተመልሶ ቀጠለ፡፡ ምሥጢራዊው ክስተት በመንግሥት የዜና እወጃ ተድበስብሶ አለፈ፡፡ ከመንግሥት በኩል የተሰጠው ማስተባበያ የልዩ ፖሊስ አባላቱ በአስተዳደር እና የደሞዝ ቅሬታዎች ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ፈልገው እንደሔዱ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ የዚህን ያህል ቀላል እንዳልሆነ ማንም የዕለቱን ግርግር ያስተዋለ ሰው አይጠፋውም፡፡ በተጨማሪም፣ የሠራዊት አባላት እንዲህ ዓይነት ሰልፎችን ያውም መሣሪያ ታጥቀው እንዲያደርጉ በሕግ አይፈቀድላቸውም፡፡ ስለሆነም፣ የማስተባበያ ዜናው “የመንግሥቱ ሠራዊት አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማነጋገር አስገደዱ” ቢባል ተአማኒነት ይኖረው ነበር፡፡

የመንግሥት ሕግ የማስከበር አቅም
ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች በሥም በማይታወቁ ቡድኖች የተለያዩ ጥቃቶች በተለያዩ ዜጎች ላይ ሲሰነዘሩ ነበር፡፡ ይህም ለዜጎች ሕይወት መቀጠፍ፣ ከቀዬ መፈናቀል እና ንብረት መውደም መንስዔ ሆኖ መክረሙ ይታወቃል፡፡ ይህ ጉዳይ ‹መንግሥት ሕግን የማስከበር አቅሙ ተዳክሟል ወይ?› የሚል ጥያቄ እያስነሳ ባለበት ወቅት ተደራጅተው የታጠቁት አካላት እንዲህ አደባባይ መውጣታቸው ስጋቱን የሚያባብስ ነገር ነው፡፡
በአንድ አገር ከመንግሥት ውጪ የኃይል የበላይነት ያለው አካል መኖር የለበትም፡፡ ሆኖም ከኦነግ አመራር በቅርቡ የተደመጠው ‹የመንግሥት ወታደሮች ለኢሕአዴግ ወገንተኛ ናቸው› በሚል መከራከሪያ ሰበብ ትጥቅ ላለመፍታት መወሰን አሳማኝ ምክንያት አይደለም፡፡ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ከገዢው ፓርቲ ጥገኝነት እንዲላቀቁ መሥራት አስፈላጊ ቢሆንም፣ የራስን ሠራዊት ይዞ ይህንን ለማድረግ መሞከር ግን የትጥቅ ትግል ከመጋበዝ አይለይም፡፡ ከዚህም በላይ ግን አሳሳቢው ነገር ‹የኦነግ ሠራዊት እስከ ዛሬ ትጥቁን ሳይፈታ ከቆየ መንግሥት ምን እየሠራ ከረመ?› የሚለው ነው፡፡ ይህ ትጥቁን ያልፈታ ሠራዊት የት ነው የሰፈረው? የራሱ ካምፕ አለው ወይስ አባላቱ የየራሳቸውን ትጥቅ እንደያዙ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለዋል?
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ በዚህ ላይ የመንግሥት ሠራዊት አባላት ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ አካሔድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ለመግባት ተፅዕኖ ማድረጋቸው፣ የመንግሥት የፀጥታ ማስከበር አቅም የሆነ ፈተና እንደገጠመው ብቻ ሳይሆን የፀጥታ አስከባሪ አባላቱ ከዕዝ ሰንሰለት ቁጥጥር ውጪ ሆነዋል ለሚለው ጥርጣሬ ማሳያ ይሆናል፡፡ ይህ የዜጎችን ደኅንነትንም ይሁን የደኅንነት ስሜት አደጋ ላይ የሚጥል ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አካሔዱ ከቀጠለ፣ መንግሥት ጉዳዩን ማድበስበሱን አቁሞ አስቸኳይ መፍትሔ ካልሰጠው በቀር ሕግ ማስከበር ጉዳይ የባሰ ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡  

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ « DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።

 

በፍቃዱ ኃይሉ

አርያም ተክሌ