1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታዳጊ ሃገራትና የዓለም ንግድ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 4 2002

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በዓለም ንግድ ላይም ከባድ ችግርን አስከትሏል። የዓለም ንግድ ባለፈው 2008 ዓ.ም. ከውድቀት አፋፍ ሲደርስ ዘንድሮም አሥር ከመቶ ያህል ማቆልቆሉ እንደማይቀር ነው ከወዲሁ የሚገመተው።

https://p.dw.com/p/K65e
የድህነት መንስዔና የዓለም ንግድ
የድህነት መንስዔና የዓለም ንግድምስል picture alliance/dpa

በዚህ ደግሞ በተለይ ተጎጂዎቹ ታዳጊዎቹ አገሮች ናቸው። የፊናንሱን ቀውስ ችግር እንደበለጸገው ዓለም በኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅድ ለማለዘብ ሃብቱም ሆነ አስፈላጊው ማሕበራዊ መዋቅር የላቸውም። ለዚህም ነው የዓለም ንግድ ድርጅት “ዕርዳታ ለንግድ” በሚል እነዚህን አገሮች ለመርዳት የሚጥረው። ሃሣቡ ታዳጊ አገሮች የዓለምአቀፉ ንግድ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ፍቱን መዋቅራትን ማነጽ ነው። በዚህ በጀርመን የሃምቡርግ ከተማ የዓለም ኤኮኖሚ ኢንስቲቲዩት አስፋላጊውን መርህ የሚጠቁም አዲስ የጥናት ውጤት ትናንት አቅርቦ ነበር።

ነጻና በለዘብተኛ ፖሊሲ ላይ የተመሠረተ የዓለም ንግድ ታዳጊ አገሮችን ይጠቅማል ወይስ ጎጂ ነው? የሃምቡርግ የዓለም ኤኮኖሚ ኢንስቲቲቱትና PricewaterhouseCoopers የተሰኘው የምጣኔ-ሐብት መርማሪ ድርጅት ለዚህ ሲነሣ ብዙ ዓመታት ላለፉት ጥያቄ ኬንያን፣ ታንዛኒያንና ኡጋንዳን እንደምሳሌ በመውሰድ በቅርቡ ባካሄዱት አዲስ ጥናት ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል። የጥናቱ የመጀመሪያ ግንዛቤ ከንግዱ ተጠቃሚ የሚሆነው በሚገባ የሠለጠነ የሥራ ሃይል ያለውና መንግሥት የተረጋጋ ሁኔታን መፍጠር የቻለበት አገር ብቻ ነው የሚል ነው።

እንደ ጥናቱ እንግዲህ ጠንካራ የሆነ መንግሥት የግድ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የሃምቡርጉ የኢንስቲቲዩቱ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ማቲያስ ቡሰ እንደሚያስገነዝቡት ታዳጊ አገሮች በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸገው ዓለም ጋር ንግድ በሚያካሂዱበት ጊዜ ሕብረተሰባቸው በተጠቃሚዎችና በተጎጂዎች የተከፋፈለ ነው የሚሆነው።

“ፍቱን የሆነ ጠንካራ መንግሥት ያለው አገር ብቻ ነው የአጽናፋዊውን የኤኮኖሚ ትስስር ተጎጂዎች ለመርዳት ብቁ ሊሆን የሚችለው”

ጥናቱ ካተኮረባቸው ሶሥት የአፍሪቃ አገሮች መካከል ኬንያ ምንም እንኳ ከሁለት ዓመታት በፊት ተካሂዶ በነበረው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ከፖለቲካ ቀውስ ላይ ብትወድቅም በዚህ ረገድ ከሌሎቹ ሻል ያለችው መሆኗን አመልክቷል። ሁለተኛው የምርምሩ ተቋማት ግንዛቤ የሚጠቁመው በታዳጊ አገሮች ቀደም ባሉ ዓመታት በተለይም የዳበረ መዋቅር የተሻለ የንግድ ዕድልን ለመፍጠር ያለው የልማት ሚና የተናቀ እንደነበር ነው። ማቲያስ ቡሰ እንደሚሉት አንዳንዶቹ መዋቅራዊ ፕሮዤዎች በጊዜው አስፈላጊ ነበሩ አልነበሩ ተገቢው ስሌት አልተደረገም።

“በቀድሞው ጊዜ ዋናው ነገር መንገዶች፣ ድልድዮችና ወደቦችን ማነጽ ነበር። ግን እነዚህ መዋቅራዊ ፕሮዤዎች ለልማት ወይም አገርን ከዓለም ኤኮኖሚ ለማስተሳሰር ተፈላጊ ይሁኑ አይሁኑ በሚገባ አልታሰበባቸውም”

ለዓለም ንግድ ተሳትፎ በሚገባ ያልተዘጋጁ ወይም ብቁ ያልሆኑ ታዳጊ አገሮች የተወሰኑ ጥሬ ዕቃዎችን ብቻ ለውጭ ንግድ ገበያ በማቅረብ ላይ ነው የሚያተኩሩት። በዚህ የተነሣም ታዲያ ኤኮኖሚያቸው ለቀውስ በጣሙን የተጋለጠ ነው። በዓለም ገበዮች ላይ ለምሳሌ የጥጥ፣ የኮኮ ወይም የዕሕል ዋጋ ውጣ-ውረድ መከሰቱ ለነዚህ አገሮች ብልጽግናም መከራም ወሣኝነት ይኖረዋል። ይህ ደግሞ ኢንስቲቲዩቱ እንደሚለው ትኩረቱን ባሳረፈባቸው ሶሥት አገሮች በሙሉ የሚታይ ሃቅ ነው።

ሶሥተኛው ግንዛቤ በግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ ሚና ላይ ያተኩራል። ይበልጥ የሕብረተሰብ ቡድኖች ከንግዱ ተጠቃሚ እንዲሁኑ የግሉ ኤኮኖሚ ዘርፍ ተጠሪዎች በተሻለ ሁኔታ መደራጀት ይኖርባቸዋል። የምጣኔው-ሐብት ዘርፍ ማሕበራትና ሸንጎዎች መጠናከር እጅግ ወሣኝነት አለው። የምጣኔው-ሐብት መርማሪ ድርጅት የ pricewaterhouseCoopers ሃላፊ ኒኮላውስ ሮሎፍ እንደሚሉት የንግዱን ተሳታፊዎች በአንድ መረብ ሊያስተሳስሩና የዘርፉን ጥቅምም ሊያስጠብቁ የሚችሉ ናቸው።

“በፖለቲካው የድርድር ሂደት ውስጥ እነዚህ ጠለቅ ባለ መልክ እንዲሳተፉ ቢደረግ እርግጥ የሚወደድ ነው። ነገር ግን ከማሕበራቱ አኳያም ይህን ሚና ለመያዝ የሚያበቃ ይዞታ መገንባት ይኖርበታል”

ጥናቱ ሶሥቱ የአፍሪቃ አገሮች ኬንያ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ ከዓለም ገበያ ጋር ባላቸው ንግድ ላይ ብቻ በማተኮር ነው የተወሰነው። የውስጣቸውን የአካባቢ የንግድ ግንኙነት አያይዞ አለመመርመሩ ከአሁኑ ትችት ማስነሳቱ አልቀረም። በመሆኑም እንደተጠየቀው የግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ ማሕበራት ጥቅም መጠናከር ለጋራ ዕርምጃ ይበጅ አይበጅ አጠያያቂ ሆኖ ይቀጥላል። በሌላ በኩል ጠበብቱና የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጠሪዎች ቀደም ካለው ጊዜ ለየት ባለ መልክ ሃሣብ በመንቀሳቀሱ ደስተኞች ናቸው። የሃምቡርጉ የዓለም ኤኮኖሚ ኢንድስቲቲዩት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ማቲያስ ቡሰ ቀድሞ የሚታሰበው ስለ ኤኮኖሚ ትብብር ወይም ንግድ ብቻ እንደነበር ያመለክታሉ።

“በልማት የተሰማሩ ሰዎች ቀድሞ ተቋማት እንዴት እንደሚሰሩ ወይም ከውስጥ የፖለቲካ ስሌት አንጻር የልማት ፖሊሲው እንዴት እንደሚቀናጅ ነበር የሚከታተሉት። የልማት አዋቂዎቹ ዕይታ በጉዳዩ ዓለምአቀፍ ገጽታ ላይ ያተኮረ ነበር። ንግዱ ብቻ ነበር የሚታያቸው። እና አሁን ዕርዳታ ለንግድ የሚለው ጥረት ዓላማ ሁለቱን ወገኖች ማገናኘት ነው”

እርግጥ ጥረቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ አከራካሪ ለሆኑት የዶሃ ድርድር ዙር የንግድ ጥያቄዎች መፍትሄ ሊያቀርብ አይችልም። ምናልባት ለአዲስ ክርክር መነሻ ይሆን እንደሆን እንጂ! የዓለም ንግድ ድርጅትን “ዕርዳታ ለንግድ” የሚል ጥረት ካነሣን ለምን አስፈለገ? ብሎ መጠየቁ ግድ ነው። ታዳጊ ሃገራት፤ በተለይም ከነዚሁ መካከል በዝቅተኛ የልማት ደረጃ ላይ ያሉት ድህነትን ለመቀነስ ሊበጅ የሚችል የንግድ ዕድላቸውን ሁሉ በአግባብ እንዳይጠቀሙ በርካታ መሰናክኖች ተደቅነውባቸው ነው የሚገኙት።

ከዚህ አንጻር ችግሩን ለማቃለል በዓለም ንግድ ድርጅት የተያዘው ዕርዳታ ለንግድ የተሰኘ ጥረት በወቅቱ ቢቀር በጉዳዩ ንቃትን ማስከተሉ አልቀረም። በዚሁ የተነሣም በልማት ግባቸው የንግድን ሚና ከፍ ማድረግ የጀመሩት ታዳጊ አገሮች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑ ነው የሚነገረው። ለጋሽ መንግሥታትም በፖሊሲ ረገድ፣ በተቋማትና በመዋቅራዊ ግንቢያ ዘርፎች የንግድ ብቃትን ለማሳደግ የሚሰጡትን ዕርዳታ እየጨመሩ ነው። በቅርቡ በጉዳዩ የወጣ ዘገባ እንዳመለከተው ዕርዳታ ለንግድ የልማት ዕርዳታ አንድ ጠቃሚ ክፍል ሆኖ እንዲቀጥል ነው የሚፈለገው።

በሌላ በኩል የታዳጊ አገሮች ችግር ባለፉት ዓመታት እየከፋ እንጂ እየለዘበ አልመጣም። ዛሬ በዓለም ላይ 1,2 ሚሊያርድ ሕዝብ ይራባል። ከሁለት ዓመታት በፊት 700 ሚሊዮን ገደማ ይጠጋ ነበር። በዓለምአቀፉ የምግብ ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ በማድረግ ሁኔታውን ያባባሱት ሶሥት የተፈራረቁ ቀውሶች ናቸው። ከመጠን በላይ በመጠቀ የምርት ዋጋ ሳቢያ በ 2007/2008 የተከሰተው የምግብ እጥረት ቀውስ የመጀመሪያው ነው። ይህንኑ ተከትሎም ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በእንቅርት ላይ ጆር ደግፍ እንዲሉ የምግቡን ችግር ይበልጥ ያባብሰዋል። በዚሁ ጊዜ የአካባቢ አየር ለውጥ ደግሞ በችግሩ ላይ መታከሉ አልቀረም። በብዙ የዓለም አካባቢዎች ድርቅና የሰብል እጥረት ለረሃብተኛው መጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ ነው ያደረገው።

ቀደም ሲል የነበረው ዝቅተኛ የምግብ ዋጋ በታዳጊ አገሮች ለከተሞች ቢበጅም በእርሻ ልማት የተሰማራው ገበሬ ግን ተጎጂ ነበር። ከ 2006 ዓ.ም. ወዲህ ለተከተለው የዋጋ ንረት ምክንያቶቹ ዘርፈ ብዙ ናቸው። በአንድ በኩል በጊዜው የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ናፍታና ማዳበሪያዎችን ሲያስወድድ በአጠቃላይ የምርት ዋጋ እንዲጨምር ያደርጋል። በሌላም የበለጸጉ መንግሥታት የባዮ-ዲዝል ምርት ማስፋፋት ሂደት ተጨማሪ ችግር መሆኑ አልቀረም። በአጠቃላይ የዓለም የዕሕል ክምችት በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከማቆልቆል ነበር የደረሰው።

የምግቡ ቀውስ የከፋውን ያህል ከፍቶ በአማካይ ጊዜ ግን በእርሻ ልማት ላይ መዋዕለ-ነዋይን ሊያዳብር ይችላል የሚል ተሥፋን አሳድሮም ነበር። ግን ብዙ ሳይኬድ ዓለም በፊናንስ ቀውስ ይወጠራል። እርግጥ ይህ የነዳጅ ዘይትና የዕሕል ዋጋም መልሶ ዝቅ እንዲል ነው ያደገው። ይሁንና በምግብ ይዞታው ላይ ለዘብተኛ የአጭር ጊዜ ዕፎይታ ከመሆን አላለፈም። በእርሻው ዘርፍ ላይ መዋዕለ-ነዋይ የመፍሰሱን ተሥፋ መልሶ ሲያደነዝዝ ብቃቱም እንዲያቆለቁል ነው ያደረገው። የቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ ማቆልቆል፣ የመንግሥት ገቢ መቀነስና የበጀት እጥረት ታዲያ በተለይም በድሆቹ አገሮች ሁኔታውን ይብስ ያከብደዋል።

ችግሩን ለመቋቋም የሚኖረው ብቸኛ አማራጭ ወደፊትም መዋዕለ-ነዋይን በእርሻ ልማት ላይ ማፍሰስ ነው። ይህ የምግብ ምርትን ከፍ ለማድረግና በተለይ በታዳጊ አገሮች ከዓለምአቀፉ የዕሕል ዋና ጥገኝነት ለመላቀቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ይህና ሌሎች አጋዥ ዕርምጃዎች ካልተወሰዱ ታዳጊ አገሮች ሊጠቀሙ በሚችሉበት መንገድ ከዓለም ንግድ መተሳሰራቸው ቀርቶ የራሳቸውን ፍላጎት እንኳ በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ለመሸፈን መብቃታቸው አስቸጋሪ ነው።

MM/DW

Negash Mohammed