1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታዳጊው ዓለምና አዲስ የልማት ዕርዳታ አቅጣጫ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 25 1996
https://p.dw.com/p/E0gA

አፍጋሃኒስታን፣ ኢራቅ፣ መካከለኛው ምሥራቅ! የዓለም ጋዜጦችንና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ዕለት ከዕለት አጣበው የሚገኙት በነዚህ አካባቢዎች በየቀኑ የሚከሰቱት አሰቃቂ የዓመጽ ድርጊቶች ናቸው። ሌሎች ዓበይት ችግሮች፤ ለምሣሌ የአፍሪቃ ሕዝብ ስቃይ ችላ ተብሎ፣ አለዚያም ተረስቶ ነው የሚገኝው። ይሁንና የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሽካ ፊሸር ሰሞኑን አፍሪቃን መጎብኘታቸው እዚህ የሚገኙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዓይናቸውን እንደገና ወደተረሳችው የዓለም ክፍል እንዲያዞሩ ምክንያት መሆኑ አልቀረም። እርግጥ በመሠረቱ ስለጉዞው ዘግበዋል ማለቱ ነው የሚሻለው። ለነገሩ በአፍሪቃ ላይ የሚተኮረው በአንድ አካባቢ የእርሰነርስ ጦርነት ሲከሰት ወይም በዚህ የሚገኙ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች እንዳሁኑ የገና በዓል በተቃረበበት ወቅት ዕርዳታ ለመሰብሰብ የተራቡ ሕጻናትን ስዕል በሚያሳዩበት ሰዓት ነው። አፍሪቃ ከሁሉም የበለጠ የልማት ትኩረት እንክብካቤ የሚያስፈልጋት መሆኑ ታጥቶ ይሆን? ለማንኛውም ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች አዲስ የትብብር ጽንሰ-ሃሣብ ለማፍለቅ ጥረት ይዘናል ያላሉ። ይህና የኤውሮ-ቻይና የንግድ ትብብር ሂደት በዚህ ዝግጅት አጣምረን የምናተኩርባቸው ሁለት ርዕሰ-ጉዳዮች ናቸው።

የአፍሪቃ መንግሥታት ዓለምአቀፍ ዕርዳታና ድጋፍ ሳይታከል ድህነትን፣ የዕዳ ጫናን፣ የእርስበርስ ጦርነት መዘዝንና ማሕበራዊ ውድቀትን በራሳቸው አቅም ለማስወገድ እንደማይችሉ ዛሬ ማወቅ ተስኖት የሚገኝ የለም። በተለይ ለብዙሃኑ አፍሪቃውያን መሪሩ ሃቅ ይህ ሲሆን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታትና በዚያው የሚገኙ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶችም እስካሁን ለዘላቂ ሰላም የሚያበቃ አስተዋጽኦ ለማድረግ አለመቻሳቸው፤ ምናልባትም ከሞላ-ጎደል የሚሹ ሆነው አለመገኘታቸው ሌላው ግንዛቤ ነው። የአፍሪቃ ሕዝብ ከነጻነት ማግስት ወዲህ ባለፊት አርባ ዓመታት ከሰማኒያ ለሚበልጡ ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ዓመጾች የዓይን ምሥክር ሊሆን በቅቷል። ባለፈው 2002 ዓ,ም. ብቻ 17 የአፍሪቃ አገሮች በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ የተነከሩ ነበሩ። አፍሪቃ እንግዲህ አብዛኛው የዓለም ክፍል በ 21ኛው ክፍለ-ዘመን የዕድገት አቅጣጫ መገስገስ በያዘበት በአሁኑ ወቅት አቆልቋይ አዝማሚያ ይዛ መቀጠሏ ነው የሚታየው።

“ዶቼ ቬልት ሁንገር-ሂልፈ” የተሰኘው የጀርመን የረሃብ ዕርዳታ ድርጅት አመራር አባል ቴዎ ዞመር የአፍሪቃን ወቅታዊና የወደፊት ሁኔታ አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ-”አፍሪቃ በሶስተኛው ዓለም ውስጥ ሌላ ሶስተኛ ዓለም ሆናለች። 800 ሚሊዮን ሕዝብ ወይም 13 በመቶው የሰውልጅ የሚኖርባት አህጉር ዛሬ በዓለም አጠቃላይ ማሕበራዊ ምርት ላይ ያላት ድርሻ 1.2 በመቶ ብቻ ነው። በዓለም የውጭ ንግድ ላይ በ 60ኛዎቹ ዓመታት የነበራት የ 3 በመቶ ድርሻም በግማሽ አቆልቁሏል። 300 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጋ ሕዝብ ኑሮውን የሚገፋው በቀን አንዲት ዶላር እንኳ በማትሞላ የዕለት ገቢ ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንዳመለከቱት የሕዝቡ ቁጥር እስከ 2025 ዓ,ም, ወደ 1.2 ሚሊያርድ ከፍ ማለቱ የማይቀር ሲሆን እስከ 2050 እንዲያውም 1.8 ሚሊያርድ ገደማ ይደርሳል ነው የሚባለው። ትንበያው ትክክል ከሆነ አፍሪቃ በ 21ኛው ምዕተ-ዓመት የድህነት መጠን የሚጨምርባት ብቸኛዋ የዓለም ክፍል ትሆናለች ማለት ነው።” ይህን የቴዎ ዞመርን አባባል ጥቂትም ቢሆን የተጋነነ አድርገው የሚመለከቱ አንዳንድ ታዛቢዎች አይጥፉ እንጂ ግምቱም ሆነ ትንቢቱ በመሠረቱ ያን ያህል ከዕውነት የራቀ አይደለም።

ዓለምአቀፍ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በአፍሪቃ አህጉር የዕርዳታ ስራ ከጀመሩ ወዲህ የተወሰኑ አሠርተ-ዓመታት አልፈዋል። የውሃ ምንጮችን ይሰራሉ፣ መንገድ፣ ትምሕርት ቤቶችና የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ያንጻሉ። የምግብ ዕርዳታ ማቅረቡም የዘወትር ተግባራቸው ሆኖ ነው የቆየው። ይሁን እንጂ ጥረቱ ሁሉ ዘላቂ ለሆነ ልማት እምብዛም ፍሬ እንዳልሰጠ ድርጅቶቹ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተረዱት መጥተዋል። በክፍለ-ዓለሚቱ ማለቂያ አጥቶ የቀጠለውን ጦርነትና ዕልቂት ዛሬም ለመግታት አልተቻለም። ይህ ደግሞ ለአፍሪቃ መለያ የሆነው ድህነት ይበልጥ እየጠነከረ እንዲሄድ ምክንያት እየሆነ ነው። ስለዚህም በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የልማት ዕርዳታ ፖሊሲያቸውን መሥረተ-ዓላማ መልሰው እንዲያጤኑ ጉዳዩን የሚከታተሉ ጠበብት ይመክራሉ። በሰሜናዊቱ የጀርመን ከተማ ሃምቡርግ የሣይንሳዊ ጥናት ሰነዶች ግምጃ ቤት ባልደረባ ቮልፍጋንግ ቬንከ እንደሚሉት በበለጸጉት መንግሥታት የልማት ፖሊሲ ላይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የለውጥ አዝማሚያ እየታየ ነው። በቬንከ አነጋገር አፍሪቃ ውስጥ የውዝግቦች መከሰትና መባባስ በየቦታው ቀደም ብሎ ቢታይም ተገቢው ክብደት አልተሰጠውም። ለዚህም ነው በብዙ አሠርተ-ዓመታት ጥረት የተገነባው የልማት ትብብር ዕርምጃ አደጋ ላይ የወደቀው ወይም ከናካቴው ከንቱ ሊሆን የበቃው። በዚህም የተነሣ የልማት ትብብርን ይበልጥ በውዝግቦች ላይ ባተኮረ መንገድ ማራማዱ ግድ እየሆነ መምጣቱ ዓቢይ ጉዳይ እየሆነ ነው።

አዲሱ የልማት ትብብር ጽንሰ-ሃሣብ መሪ መፈክር “መዋቅራዊ ዕርጋታ” የሚል እየሆነ ሄዷል። ይህም ማለት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት አገሮችና ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በቀውስ አካባቢዎች ማሕበራዊ መዋቅራትን በማነጹ ተግባር ይበልጥ ማተኮር ይኖርባቸዋል ማለት ነው። ከዚሁ ተግባር አንዱ ለምሳሌ እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን የወደፊት ዕድል እንዲያቃና የትምሕርትና የሙያ ሥልጠና ተቋማትን ማራመዱ ይሆናል። አለበለዚያ የተረጋጋ የሕብረተሰብ ሕይወት ሳይኖር ሰላም ይሰፍናል ብሎ ማሰቡ ዘበት ነው። የኤኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ዕድገት ሊደረግ የሚቻለው ሰላም በሰፈነበት አገር ብቻ መሆኑ ነው የሚታመነው። ሰላም ወይም ጸጥታ ሲባል ደግሞ እርግጥ ሰፋ ባለ መልክ መታየት ይኖርበታል። የሕብረተሰብ ጸጥታ በጦር ሃይሎች ብቻ የሚሰፍን ነገር ሆኖ መታየት የለበትም። በአንድ ሕብረተሰብ ውስጥ እርካታን ማስፈንና ለአስተማማኝ ሰላም መሠረት መጣል የሚቻለው ሃቁን ላስተዋለ፣ የሕዝብን የኑሮ ሁኔታ ለሚያሻሽል የልማት ፖሊሲ ተገቢውን ሁኔታ ማመቻቸት ሲቻል ነው።

እነዚህ የሕብረተሰብ ማረጋጊያ ዕርምጃዎች ተጨማሪ አገሮች በዓመጽ እንዳይዋጡ ሊገቱ የሚችሉ መሆናቸው ነው የሚታመነው። ይህ አዲሱ የልማት ትብብር ጽንሰ-ሃሣብ በወቅቱ በግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ተግባር ላይ መንጸባረቅ መጀመሩ ከቦታ ወደቦታ እየታየ ነው። ለምሳሌ ያህል የጀርመን የረሃብ ዕርዳታ ድርጅት በዚህ ዓመት በኮንጎ ዓመጽ ላጠቃው ሕዝብ አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ማቅረቡን ችላ ባይለውም ከረጅም ጊዜ አንጻር ሕብረተሰቡን የሚለውጡ ዕርምጃዎችን ዓቢይ ዓላማው ማድረጉ ታይቷል። ከድርጅቱ ተግባራት መካከል ተኩስ አቁሙን በመጠቀም መዋቅራትን ማቆሙ፣ የገጠሩን ገበሬ በእርሻ ልማት ተግባር መደገፉና ትምሕርት ቤቶችን ማነጹ ይገኙበታል። እንግዲህ የልማት ዕርዳታው ተግባር በተለይ በቀውስ አካባቢዎች የቀድሞ ፈሩን እየለቀቀ በመሄድ ላይ መሆኑ ነው። እርግጥ በዚህ የአሠራር ዘይቤ ድህነት በተጫነው አካባቢ ጦርነትና ዓመጽን ለዘለቄታው ማስወገድ መቻሉን ጥቂት ጠብቆ ከመታዘብ ሌላ ለጊዜው የተሻለ ምርጫ የለም።

ሕዝባዊት ቻይናና የአውሮፓው ሕብረት የንግድ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ባለፈው ሣምንት መስማማታቸው በተለይ በዚህ ዘርፍ ከቤይጂንግ ጋር የምትነታረከውን አሜሪካን ስጋት ላይ መጣሉ አልቀረም። ሁለቱ ወገኖች የጠነከረ ተራድኦ ለማድረግ ጽኑ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የገለጹት ከአንድ ሣምንት በፊት ለስድሥተኛ ጊዜ ያካሄዱትን የጋራ ጉባዔ አጠናቀው ሶሥት ውሎችን ከተፈራረሙ በኋላ ነበር። የአውሮፓው ሕብረት ተጠሪዎች የኮሚሢዮኑ ርዕስ ሮማኖ ፕሮዲና በወቅቱ ሕብረቱን በሊቀ-መንበርነት የምትመራው ኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሢልቪዮ ቤርሉስኮኒ ከአዳዲሶቹ የቻይና መሪዎች ሲገናኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ከውይይቱ የተገኝው ውጤት አርኪ ሆኖ ነው የታየው። ሕዝባዊት ቻይና እስከ 2010፤ ይህም በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ መሆኑ ነው ከአውሮፓው ሕብረት ያለው የንግድ ልውውጥ በእጥፍ ከፍ እንዲል ለማድረግ የምትጥር መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ ከጉባዔው በኋላ ቤይጂንግ ውስጥ ባካሄዱት ጋዜጣዊ ጉባዔ አስረድተዋል። የሁለቱ ወገን የንግድ ልውውጥ ገና ከአሁኑ ያለፈውን ዓመት መጠን እንዳለፈና እስከያዝነው ዓመት መጨረሻ መቶ ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ሊጠጋ እንደሚችል ዕምነት አለ። ዌን ጂያንባዎ እንዳመለከቱት ቻይና በፖለቲካ ግንኙነትም ቢሆን ከተባበረች አውሮፓ የምትጠብቀው ትብብርና አስተዋጽኦ ትልቅ ነው።

“ቻይና የአውሮፓውን ሕብረት የመስፋፋት ሂደት በታላቅ ደስታ ነው ስትከታተል የቆየችው። በፖለቲካና በኤኮኖሚ የጠነከረች አውሮፓ የዓለምን ሰላምና እርጋታ ለማረጋገጥ አንድ ዋና መሠረት እንደምትሆን ጽኑ ዕምነታችን ነው። ሕዝባዊት ቻይና የአውሮፓው ሕብረት ታላቅ የንግድ ሸሪኳ እንዲሆን ትሻለች።” ይሁንና ሕብረቱ ከቻይና ጋር ባለው የንግድ ልውውጥ በወቅቱ ገና ከአሜሪካና ከጃፓን ቀጥሎ በሶሥተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ከዚህ አንጻር የዌን ጂያባዎ አነጋገር ቻይና ታላቅ የኤኮኖሚ ሃይል ለመሆን በያዘችው ዓላማ በጥርጣሬ ዓይን በሚመለከቷት በሁለቱ አገሮች ላይ የትግል ዛቻ ነው የሚመስለው። እርግጥ ከቻይና ጋር በከፍተኛ ኪሣራ የንግድ ልውውጥ የምታደርገው አሜሪካ በዚህና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ምርቶችን ከማባዛት እስከ ዓለም ንግድ ድርጅት ደምቦች ችላ መባል ድረስ በቤይጂንግ ላይ ያላት ቅሬታ ለአውሮፓውያኑ የተሰወረ አይደለም። ሆኖም የሕብረቱ ኮሚሢዮን ርዕስ ሮማኖ ፕሮዲ ጉዳዩ የንግድ ግንኙነቱን በማስፋፋቱ በኩል መሰናክል ሊሆን አይገባውም ባይ ናቸው።

ቻይናና የአውሮፓው ሕብረት የንግድ ልውውጡን ከመስፋፋቱ ባሻገር አከራካሪ ሆኖ በቆየው የቴክኖሊጂ ተራድኦ መስክም አንድ ውል ተፈራርመዋል። በሕብረቱ የንግድ ኮሜሣር በፓስካል ላሚይና በቻይናው የሣይንስ ዘርፍ ሚኒስትር በሹ-ጉዋንግ-ሁዋ መካከል የተፈረመው የትብብር ውል “ጋሊሌዎ” የተሰኘ የሣቴላይት፣ ማለት ከፍተኛ የመረጃ አካል ቴክኖሎጂ ፕሮዤን የሚመለከት ነው። በውሉ መሠረት ቻይና በፕሮዤው በሁለት መቶ ሚሊዮን ኤውሮ የምትሳተፍ ሲሆን በወታደራዊ መስክ ጭምር ለመጠቀም የሚያስችለውን የቴክኖሎጂ ጥበብ የማግኘት ጥርጊያ ይከፍትላታል። የአውሮፓው ሕብረት በዚህ መልክ ለቻይና መንገድ መክፈቱ በተለይ ቤይጂንግ ወደፊት የተፎካካሪነት ብቃት ማግኘት መቻሏ ያሰጋውን የአሜሪካን መንግሥት እጅግ ነው ያስቆጣው። የኢጣሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤርሊሉስኮኒ ውሉ በሲቪል ግልጋሎት ላይ ያተኮረ ነው ማለታቸውም የዋሺንግተንን ቅሬታ የሚያለዝብ ሆኖ አልተገኘም።

የአውሮፓው ሕብረት ተጠሪዎች የቻይናን የሰብዓዊ መብት ይዞታ መሻሻል ለንግዱ ትብብር መስፋፋት ቅድመ-ግዴታ ለማድረግ አልቃጡም። ጉዳዩ ቢነሣም ከሕብረቱ ተጠሪዎች አኳያ ጽናት የተመላበት አቋምም ሆነ አሣሪነት ባህርይ ላለው ስምምነት የሚያበቃ ግፊት አልተንጸባረቀም። አጠቃላዩ አመለካከት የሰብዓዊ መብት ጥያቄ በሁለቱ ወገን ግንኙነት ላይ መሰናክል ሊሆን አይገባውም የሚል ነው። ለዘወትሩ በአፍጋሃኒስታን፣ በርማ ወይም ሌሎች አካባቢዎች የዴሞክራሲ ዕርምጃ እንዲደረግ ከመወትወት ወደኋላ የማይሉት አውሮፓውያን በቻይና ጉዳዩን ማቃለሉን መከጀላቸው ቅር ያሰኛቸው ብዙዎች ታዛቢዎች ሕብረቱ የያዘው ባለ ሁለት መስፈርት ፖሊሲ እንዳልጣማቸው መናገራቸው አልቀረም። ይሁንና የአውሮፓው ሕብረት በቻይና ከሞራላዊ ጥያቄዎች ይልቅ የረጅም ጊዜ የኤኮኖሚ ጥቅሙን ማስቀደሙን የመረጠ ነው የሚመስለው። የወደፊቷ የኤኮኖሚ ሃይል፣ መጪዋ ሰፊና ማራኪ የዓለም ገበያ ሕዝባዊት ቻይና በወቅቱ ከፈላጊነት ይልቅ ተፈላጊነቷ የበለጠ ሆኖ ነው የሚገኘው። በተለይ በከፍተኛው የቴክኖሎጂ ትብብር በጋሊሌዎ ፕሮዤ ውል ቅር የተሰኙት አሜሪካና ጃፓን እንግዲህ ነገሩን ጥርሳቸውን ነክሰው ከማለፍ በስተቀር ቢቀር ለጊዜው ሌላ ምርጫ አይኖራቸውም።