1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቱአሬጎች ከሊቢያው ጦርነት በኋላ

ረቡዕ፣ መጋቢት 5 2004

የቱአሬግ አርብቶ አደሮች ‘አዛዋድ’ብለው በሚጠሩት የሰሜን ማሊው በረሃ በመንግሥት ወታደሮችና በቱአሪግ አማጽያን መካከል ከጥር መጀመሪያ አንስቶ የተኩስ ልውውጥ እና የአየር ድብደባም እየተካሄደ ነው ። ሰለ ውጊያው የሚወጡ ዘገባዎች

https://p.dw.com/p/14HrP
ምስል AP



የቱአሬግ አርብቶ አደሮች ‘አዛዋድ’ብለው  በሚጠሩት የሰሜን ማሊው በረሃ  በመንግሥት ወታደሮችና በቱአሪግ አማጽያን መካከል ከጥር መጀመሪያ አንስቶ የተኩስ ልውውጥ እና  የአየር ድብደባም እየተካሄደ ነው ። ሰለ ውጊያው የሚወጡ  ዘገባዎች ግን በርሰ በርስ የሚጋጩ  ናቸው ። ስለ ሞቱና የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር አስተማማኝ መረጃ የለም  ። ይሁንና ከ120,000በላይ ሰዎች ከአካባቢያቸው ተሰደው ወደ ተባበሩት መንግሥታት መጠለያዎች ሸሽተዋል ። ጉዳዩን በቀርብ የሚያውቁ ተንታኞች እንደሚሉት ውጊያው የሊቢያው ጦርነት መዘዝ ነው ። የዶቼቬለዋ Julia Hahn የዘገበችውን ሂሩት መለሠ አጠናቅራዋለች ።
እጅግ የደየኽየውና አስቸጋሪው ሰሜን ማሊ የሚገኘው በረሃ  የቆዳ ስፋቱ ከፈረንሳይ ጋር ይስተካከላል ። በዚህ አካባቢ ከሳምንታት አንስቶ የማሊ ጦርና የአዛዋድ በሔራዊ የነፃነት ንቅናቄ በእንግሊዘኛው ምህፃር MNLA በመባል የሚጠራው አዲሱ የአማፅያን ቡድን እየተዋጉ ነው ። በ ጀርመኑ የ Bayreuth ዩኒቨርስቲ የማሊ ጉዳዮች አጥኚ Georg Klute እንደሚሉት የአሁኑ ውጊያ የሊቢያው ጦርነት መዘዝ ነው  ።
« ከባዱ ውጊያ ፣የሊቢያው ጦርነትና የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህፃሩ NATO የሊቢያ ዘመቻ  ወጤት ነው ። ምክንያቱም በሊቢያ አገዛዝ ልዩ ልዩ ክፍሎች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ በርካታ ወታደሮች ወደ ደቡብ ተሰደዋልና ። »

Libyen Sahara Sanddüne Tuareg mit Turban
ምስል picture-alliance/Bildagentur-online/RUN-McPhoto


በመገናኛ ብዙሃን ዘገባ መሠረት ቁጥራቸው እስከ 4000 የሚደርስ የቱአሬግ ቅጥርኛ ተዋጊዎች ከሊቢያ በተለይም ወደ ኒዠር ና ማሊ  ገብተዋል ። አበዛኛዎቹ በሊቢያው ህዝባዊ አብዮት ወቀት ለጋዳፊ ጦር ተሰልፈው ተዋግተዋል ። ቅጥረኞቹ የማሊን ድንበር አቋርጠው ጥር መጀመሪያ ላይ ሮኬቶች ና ሌሎች በቀላሉ የሚንቀሳቀሱ የጦር መሣሪያዎችን በሻንጣቸው ሸክፈው ነው ማሊ የገቡት ።
« እነዚህ የጦር መሣሪያዎች የጋዳፊ ጦር መሆናቸው ፍፁም ግልፅ  ነው ። የጦር መሣሪያዎቹ የማሊ ጦር ከታጠቃቸው መሣሪያዎች  እጅግ በጣም የተሻሉ ናቸው ። በአማፅያን ዘንድ ያለው አዲሱ ነገር ይሄ ነው ። »
ይላሉ በፍራንክፈርት ዩኒቨርስቲ የሰነ ሰበ ምሁር  የማሊው ተወላጅ ማማዱ ዲያዋራ ።
MNLA ራሱን  ፣ የአብዮታዊ ንቅናቄ ቡድን ፣ የቱአሬጎች ድምፅ አድርጎ የሚቆጥረው  ። ከዚህ በተጨማሪም አረቦችን ማውሮችንና ፉላኒዎችንም ደጋፊዎቼ  ናቸው ነው የሚለው ። ግቡ አዝዋድ የምትባል ነፃ ሃገር መመሥረት  ነው ።ሙሳ አግ አሳሪ የአማፅያኑ ቃል አቀባይ ናቸው ። ከመንግሥት ጋር የሚካሄደው ድርድር ያልሰመረበትን ምክንያት ያስረዳሉ
« በሰላማዊ ፣ዴሞክራሲያዊ መንገዶች ሞክረናል ። ሆኖም መፈናፈን የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው ።  አዎ መደራደር እንፈልጋለን ። ይሁንና እንዳለመታደል ሆኖ መንግሥት መልስ የሚሰጠን በጦር እርምጃ ነው ። »

Libyen Sahara Tuaregs
ምስል picture-alliance / dpa


የቱአሬጎች ትግል  እድሜ ማሊ ነፃነትዋን ካወጀችበት ጊዜ ጋር ይስተካከላል  ። በማሊና በሌሎቹም የሳህል ሃገራት አናሳ የሆኑት  አርብቶ አደር የህብረተሰብ  ክፍሎች በመንግሥት ውስጥ ውክልና የለንም የሚል ስሜት ነው ያላቸው  ።  እጎአ ከ 1960 አንስቶ በተለይም ማሊና ቻድ የሚገኙት አርብቶ አደሮች በየጊዜው እንዳመፁ ነው ። እጎአ ከ 2005 እስከ 2009 ዓም የተካሄደው የቅርብ ጊዜው  አመፅ ነው ። እነዚህን ግጭቶች ለማስቆም የተካሄዱት ድርድሮች ከሽፈዋል ። ለማሊው ፐሬዝዳንት የሃገሪቱ መከፈል ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም ።  በሚያዚያ አጋማሽ አካባቢ ምርጫ ይካሄዳል ። እስከዚያ ድረስ የማሊ ጦር አማፅያኑን ድል ማድረግ ነወ ፍላጎቱ ። የማሊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሜሊያ ቦቤዬ ማይጋ ፣ መንግሥት የደኽየውን ሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል ኤኮኖሚ ለማልማት  ፣ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሱን አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ ።  ያም ሆኖ ግን ስህተት  መኖሩንም ያምናሉ ።

Tuareg mit blauem Turban
ምስል AP


« እርግጥ ነው መንግሥት እዚያ በቅርበት የለም ።ይህም  በተለያዩ ምክንያቶች ለዓመታት ዘልቋል  ። መንግሥት ይህን ግዛት መቆጣጠር እንዳይችል የሚንቀሳቀሱ በርካታ ቡድኖች አሉ ። »
መነገሥት አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ ባለመቆጣጠሩ ምክንያት ተጠቃሚ የሆነው MNLA ብቻ አይደለም ። አስቸጋሪው ሰሜን ማሊ ከረዠም ጊዜ አንስቶ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ፣ የአክራሪ ሳላፊስቶችና በመግሬብ የአልቃይዳ አባላት መነኻሪያ ሆኗል ። በመግሬብ የአልቃይዳ  ቡድን ባለፉት ጊዜያት አገር ጎብኝዎችን  በማገት ይታውቃል  ። የቱኣሬግ አማፅያን ከዚህ  ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ  ይጠረጠራል ። ይሁንና ደያዋራ እንደሚሉት ለዚህ ማረጋገጫ የለም ።

ሂሩት መለሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ