1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቱኒዝያ ከቤን አሊ በኋላ

ቅዳሜ፣ ጥር 10 2006

ከብዙ አዳጋች ሁኔታ በኋላ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት የተቃረበችው ቱኒዝያ " ባለፈው ማክሰኞ ቤን አሊ የተወገዱበትን 3ኛ ዓመት አስባ ዋለች። የቱኒዝያ ሕዝብ ዓመፅ እና ቤን አሊ የሸሹበት ድርጊት ግብፅ፣ ሊብያ ፣የመን እና ሶርያን ለዓብዮት ማበረታታቱ አይዘነጋም።

https://p.dw.com/p/1AsNw
Tunesien 3. Jahrestag Umsturz
ምስል picture-alliance/dpa
Bouguiba Avenue feiert Revolutionsjubiläum in Tunesien
ምስል DW/K. B. Belgacem

እነዚህ ሀገራት ጦርነት ላይ ሲገኙኙ ቱኒዝያ ግን ኤናሀዳ ፓርቲ በ2014 መጨረሻ ከተቀናቃኞቹ ጋ ይ በምርጫ ለመፎካከር ወስኖዋል። ከሁለት ዓመት በፊት በምርጫ ያሸነፈው እና በተጨባጭ ሁኔታ የሚያምነው የሙሥሊሞቹ ኤናሀዳ ፓርቲ ሀገሪቱን ለብዙ ወራት ውጣ ውረድን ለማብቃት በደረሰው ስምምነት ስልጣኑን የለቀቀበት ርምጃው፣ በቱኒዝያ ቤን አሊ ከተወገዱ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ፣ እንዲሁም፣ ከአዲሱ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት እና አስመራጩ ቦርድ ከተቋቋመ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከሚደረገው ቀጣዩ ምርጫ ድረስ፣ ሀገሪቱ በባለሙያ አስተዳደር የምትመራበትን መንገድ ክፍት ማድረጉን የእሥላማዊው ኤናሀዳ ፓርቲ አባል ዋሊድ ባናኒ ገልጸዋል።

« እስካሁን የተቀበልናቸውን ገላጋይ ሀሳቦች ውጤት ስንመለከት፣ ኤናሀዳ በተቻለው መጠን በሥልጣን ለመቆየት የማይፈልግ ሀገሩን የሚወድ ፓርቲ መሆኑን እናያለን። እኛ በግብፅ እየታየ ካለው ቀውስ ትምህርት ወስደናል። የግብፅ ዓይነቱ አስከፊ መዘዝ በቱኒዝያ እንዲደርስ አንፈልግም። »

ይህን ለማከላከልም ሲል ኤናሀዳ ከደረሰው ገላጋይ ሀሳብ አንዱ ጠቅላይ ሚንስትር አሊ ላራዬድህ ሥልጣን የለቀቁበት እና ተተኪያቸው ሜህዲ ጆማ ሀገሪቱ ነፃ ምርጫ የሚካሄድበትን መንገድ እንዲያዘጋጁ የተስማሙበት ርምጃ እንደሚጠቀስ የኤናሀዳ ፓርቲ አባል ዋሊድ ባናኒ አስረድተዋል።

Aidoudi
ምስል DW/Ute Schaeffer

« ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን እና ሁሉ እንዲሳተፍበት እንፈልጋለን። ካሁን በኋላ ኤናሀዳ ሥልጣኑን እንደጨበጠ ለመቆየት የሚያስብ ፣ እንዲሁም፣ አስተዳደሩን እና ሚንስቴር መሥሪያ ቤቶችን ለብቻው ተቆጣጥሮ ለመያዝ የሚፈልግ ፓርቲ ነው የሚል ምክንያት እንዲፈጠር አንፈልግም። »

ያም ቢሆን ግን ቱኒዝያ አሁንም በትልቅ ችግር ውስጥ ትገኛለች። እንደሚታወሰው፣ የቱኒዝያ ዓብዮት ጥቂቶችን ብቻ ሳይሆን ሁሉን የሀገሪቱን ሕዝብ ተተጠቃሚ ማድረግ ነበር፣ ግን፣ ይህ ገሀድ አልሆነም። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቆ አሁንም ገና ስራ ያላገኘው ሱዌይል አይዱዲ ፖለቲከኞች ከዓብዮቱ በኋላ የሀገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍ በቂ ችሎታ አላሳዩም ፣ ዓብዮቱ ያመቻቸውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም የራሳቸውን ማበልፀጊያ እና ጥቅማቸውን ማስጠበቂያ መሣሪያ አድርገው ነው የተጠቀሙበትበሚል አብዝቶ ይወቅሳል። አይዱዲ እንደሚለው፣ እንደርሱ ስራ ያጡ እና ብሩህ የወደፊት ዕድል የሌላቸው ብዙ የቱኒዝያ ወጣቶች አሉ።

NO FLASH Pressefreiheit in Tunesien nach der Revolte
ምስል DW/ Swissi

ከአስራ አንድ ሚልዮኑ የቱኒዝያ ሕዝብ መካከል ውደ 700,000 የሚጠጉ ስራ አጥ ናቸው። ከነዚህም 400,000 የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ናቸው። ይህ አሳሳቢ ሁኔታ በሀገሪቱ ካሁን ቀደም የታየውን ዓይነት የሕዝብ ዓመፅ ሊቀሰቅስ እንደሚችል መንግሥታዊ ያልሆነው የስራ አጦች ተሟጋች ድርጅት ኃላፊ ሳሌም አያሪ አስጠንቅቀዋል። የችግሩን አሰሳቢነት በመገንዘብ ስራ አጦችን በስራው ገበያ ማዋሀድ የሚያስችል መርሀግብር ተነድፎ እንደነበር ፣ ግን ተግባራዊ እንዳልሆነ አያሪ ያስታውሳሉ።

በዓብዮቱ ወቅት የተንፀባረቅውን አስተሳሰብ ወደፊትም የሚያራምደው ዛሬ በ20 እና በ30 ዓመት መካከል የሚገኘውን የቱኒዝያን ወጣት፣ የሴቶችን የወደፊት ዕድል በዚያው በሀገሩ አስተማማኝ እና የነፃነት መንፈሥ ተሰምቶት እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ብዙዎቹ የሀገሪቱ ዜጎች ይናገራሉ።

ይሁንና፣ የቱኒዝያ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ ያስገኘው አዎንታዊ ውጤት ሳይጠቀስ ሊታለፍ አይገባም። በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ከ40 የሚበልጡ የራድዮ ጣቢያዎች ተከፍተው እና ዕለታዊ ጋዜጦችም ወጥተው፣ በመንግሥቱ ፕሮፓጋንዳ አንፃር አስተያየት በነፃ የሚገለጽበት አሰራር መስፈኑን ለፕሬስ ነፃነት የሚሟገተው መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት አስተባባሪ ቤኺር ኡዋርዳ ገልጸዋል።

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ