ቱርክ የኤርዶኻን መንግሥትና የገጠመዉ ተቃዉሞ
ሰኞ፣ ሰኔ 3 2005
ጥር አጋማሽ-ሁለት ሺ አስራ-አንድ።ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።ካይሮ ተሕሪር አደባባይ ሞላ-ጠርቃ፥ ሞቅ ደግሞም ወበቅ ማለት ያዘች።
ኢስታንቡል-ታክሲም አደባባይ በቀደም።
ይራራቃሉ።በሁለት ዓመት ከመንፈቅ እድሜ ይበላለጣሉም። ግን ይመሳሰላሉ።አንድ ይሆኑ ይሆን? የአንካራ መሪዎችን አመራር እንዴትነት፣የኢስታንቡሉን ተቃዉሞ ሰበብ ምክያት እየጠቃቀስን ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
የሃያ-ስድስት ዓመቱ ቱኒዚያዊ ወጣት መሐመድ ቡዋዚዚ ታሕሳስ 2010 አካሉ ላይ የቸለሰዉ ቤንዚን እና የለከሰዉ ክብሪት የሱን ሕይወት ቀጥፎ የቱኒዚያዎችን ቁጣ ሲያቀጣጥል እንደ አብዛኛዉ ዓለም የፓሪሶችን አፀፋ ከሩቅ አድፍጦ ከማየት በስተቀር ብዙ ያሉ-ያደረጉት አልነበረም። ከቡዋዚዚዋ ከተማ ሳይዲ ቡዚድ ላይ የገነፈለዉ ሕዝባዊ ቁጣ ቱኒዚያን አዳርሶ የቱኒዙን ጠንካራ መሪ የዘይን ኤል አቢዲን ቤን ዓሊን ሥርዓት በገረሠሠ ማግሥት ወደ ካይሮ ሲሸጋገር ግን በጥሞና ይከታተሉት ነበር።ካይሮ፥-
ከተሕሪር አደባባይ ጩኸቱ ሲቀልጥ የያኔዉ የሐገሪቱ ፈርጣማ መሪ ሆስኒ ሙባረክ የሕዝባቸዉን ጥሪ ከልብ እንዲሰሙ እንደ ወዳጅ ቀድመዉ ከመከሩ፥ እንደ ሕዝብ ጥያቄ አክባሪ ደፍረዉ ካሳሰቡ ጥቂት መሪዎች አንዱ ነበሩ።ጠቅላይ ሚንስትር ሬሴፕ ተይፕ ኤርዶኻን።ትናንት በርግጥ ዛሬ አይደለም።ኤርዶኸንም በምንም መመዘኛ ሙባረክን አይመስሉም።ኢስታንቡሎች ግን በሁለት ዓመት ከመንፈቃቸዉ ካይሮዎችን ባይሆኑ መስለዋል።እንዲሕ ይሉ ገቡ።ሴትዮዋ፥-
«እዚሕ የተገኘነዉ ሕዝቡን ለመደገፍ ነዉ።በነፃ የማሰብና የመናገር መብታችንን ለመጠየቅ እራሳችንን ለመግለጥ።» ሰዉዬዉም፥-አከሉበት፥-«የዚሕ ሁሉ ተቃዉሞና መልዕክት ሲታይ ኤርዶሐን ከእንግዲሕ ቦታ የላቸዉም»
የቱኒዝ ካይሮዉ አስተምሕሮት የነቀነቀዉ የየመን ሕዝብ የሰነዓን አደባባዮች ሲያደበላልቅ ሪያድ፥ ዶሐ፥ ዋሽግተኖችኖች የሚሉ የሚደርጉትን ከመከታተል ባለፍ ያሉ ያደረጉት ከነበረ ብዙም አልተሰማም።የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ሥርዓት፣ የእሳቸዉን፣ የልጆቻቸዉንና የብዙ ሺሕ ሊቢያዉያንን ሕይወት ላጠፋዉ ዘመቻ ኒኮላይ ሳርኮዚ ምዕራቡን ዓለም ሲመሩና ሲያስተባብሩ፣ ሙስሊሙን ዓለም፣ከመሩት ሰወስት መሪዎች አንዱ ግን እሳቸዉ ነበሩ።ሁለቱ ሐማድ ቢን ኸሊፋ አ-ሳኒ እና አብዱላሕ ኢብን አብድል አዚዝ።
በሽር አል አሰድን እንደ ቃዛፊ ለመፈጠም ያለመዉ የምዕራባዉያንና የተከታዮቻቸዉ ዘመቻ ጠቅላይ መሪ በርግጥ ባራክ ኦባማ ናቸዉ።የሶሪያ ሸማቂዎችን ያስጠጉት፥ የሚያደራጁ የሚስታጠቁት ደፋር ፊት አዉራሪ ግን እሳቸዉ ናቸዉ።ኤርዶኸን።
ኢስታንቡል ቤንጋዚ ወይም ሆምስ አይደለችም።ኢስታንቡሎች እንደ ቤንጋዚ ሆምሶች ጠመንጃ መንከስ አያስፈልጋቸዉምም።እንዲያዉ ምናልባት ነገሮች ተቀያይረዉ ቢፈልጉ እንኳን በኩርዶች የደረሰና የሚደርሰዉን ማየት፥ ማስተዋል አለባቸዉ።ከሁሉም በላይ ኤርዶኻን እንደ ቃዛፊ ወይም እንደ አሰድ የዋሽግተን ብራስልሶችን ጥቅምና ትዕዛዝ እስኪጥሱ መጠበቅ ግዳቸዉ ነዉ። ሰዉዬዉ የሚያደርጉት አይመስልም።
ብቻ ምን ይታወቃል። ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ በዋሽግተን፥-ለንደን-ፓሪስ፥ በሪያድ፥ ዶሐ፥ አንካራዎች ድጋፍ የተደራጁ፥ የሰለጠኑና የታጠቁ ተቃዋሚዎቻቸዉ ቤንጋዚ ላይ ምሽግ መማስ፥ ጠመንጃ መተኮስ ሲጀምሩ «አሸባሪ አይጦች» ብለዋቸዉ ነበር።
በሪያድ ዶሐዎች ገንዘብ፥ በዋሽግተን ብራስልሶች ሥለላ፥ ዲፕሎማሲ እየተረዱ አንካራዎች በፈቀዱት ምድር መሽገዉ የሶሪያ መንግሥትን የሚወጉት አማፂያን ለፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ «የተደራጁ አሸባሪዎች» ናቸዉ።ተሕሪር አደባባይ የፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክን አገዛዝ በሚቃወመዉ ሕዝብ መጥለቅለቅ በጀመረበት ሰሞን ሙባራክ ግመል ጋላቢ፥ ጩቤ ታጣቂ ነዉጠኛ ደጋፊዎቻቸዉን እዚያዉ አደባባይ አፍስሰዋቸዉ ነበር።
ያኔ ሙባረክ ደጋፊዎቻቸዉን ከተቃዋሚዎቻቸዉ ማጋጨት፥ የአብዛኛዉን ሕዝብ ጥያቄን አልቀበልም ማለታቸዉን የተቹት ኤርዶኻን ትናንት አንካራ ላይ ደጋፊያቸዉን አሰለፉ።ያኔ የቃዛፊ አሸባሪ አይጦችን እንደ ነፃነት ተዋጊ የረዱ የደገፉት፥ አሁን የአሰድን «የተደራጁ አሸባሪዎች» የሚያደራጁት ኤርዶኻን ተቃዋሚዎቻቸዉ በዚያዉ ቃል አወገዟቸዉ።አሸባሪ።
«ሥርዓተ-አልበኞች እና አሸባሪዎች የሕዝብ አደባባይን እንዲቆጣጠሩ መፍቀድ አለብን-እንዴ? ምን ለማግኘት ነዉ የሚታገሉት።ፖሊስ የሚፋለመዉ ይሕን ሁኔታ ለመከላከል ነዉ።እፍኝ የማይሞሉ ወርሮ በሎች ያደረጉትን ማድረግ አንፈልግም።የሰላማዊ ሰዎችን መኪኖች ሰባብረዋል።የዚችን ሐገር ጠቅላይ ሚንስትር እስከመስደብ የደረሱ ወራዶች ናቸዉ።»
ያም ሆኖ ጋዛፊን፥ሙባረክን፥ ሳሌሕን፥ ወይም አሰድን አይደሉም።ሥልጣን የያዙት በሕዝብ ተመርጠዉ እንጂ እንደ ቃዛፊ በመፈንቅለ መንግሥት፥ እንደ ዓሊ አብደላ ሳሌሕ በሞተ-ከዳ፥ እንደ ሙባረክ፥ እንደ አሰድ በዉርስ አይደለም።እርግጥ ነዉ እንደ አሰድ የጦር መኮንን ልጅ ናቸዉ።
ከወታደር አባታቸዉ ድፍረትን፥ የትምሕርትን ጥቅም፥ ሐይማኖትን ጠንከር አድርጎ የመያዝን አስፈላጊነት፥ ደሐን የመርዳት፥ ሐገርን የመዉደድ ፍቅርን እንጂ በመፈንቅለ መንግሥት የተያዘ ሥልጣንን አልወረሱም።ገና በወጣትነታቸዉ ፖለቲካንና ስፖርትን እኩል ይወዱ ነበር።የፖለቲካ ጥልፍልፍን አንድ ሁለት ያሉትም፥ የተለማመዱትም ገና የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያሉ የተማሪዎች ማሕበር አባል ሆነዉ እንጂ እንደ ሌሎቹ ሥልጣን ከያዙ በኋላ አልመዱትም ወይም ድንገት አልተሞጀሩበትም።
በ1954 በጥንታዊቷ፥ በታሪካዊቷ ትልቅ የንግድ ከተማ ተወለዱ።ኢስታንቡል።በ1980 የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያሉ የቱርክ ጦር ሐይል የያኔዉን የቱርክ ሲቢላዊ አስተዳደር ከስልጣን አስወግዶ ሥልጣን መያዙን ከጓደኞቻቸዉ ጋር ሆነዉ አጥብቀዉ ተቃዉመዉት ነበር።ያኔ ሐያ ስድስት ዓመታቸዉ ነበር።ዘንድሮ የያኔ-እድሜያቸዉን የያዙ ወጣቶች ሲቃወሟቸዉ ግን አወገዙ፥ ረገሟቸዉም።
«የራሳቸዉን ጠቅላይ ሚንስትር የሚያወግዙ ወጣቶች የኔ ወጣቶች ሊሆኑ አይችሉም።የቤቶች መስኮቶችን የሚሰባብሩ ወጣቶች መብታቸዉን በትክክል የሚጠቀሙ ወጣቶችን መልክና ባሕሪ ሊይዙ አይችሉም።ሱቆችን የሚያፈራሱ በዚች ሐገር ያላቸዉን መብት በተገቢዉ መንገድ ለመጠቀም የሚሹ ናቸዉ ሊባሉ አይቻልም።»
ከ1980 ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ እስልምናን የሚያጠብቀዉ ፓርቲ አባል ነበሩ።በ1994 በተደረገዉ የከተሞች ምርጫ የተወለዱባትን ትልቅ ከተማ የኢስታንቡል የከንቲባነት ሥልጣን ሲይዙ ጠንካራ ሐይማኖታዊ መርሕ ይከተሉ ይሆናል ተብለዉ በተቃዋሚዎቻቸዉ ዘንድ ሲተቹ ነበር።አንዳድ ሥፍራ አልኮሖን እንዳይሸጥ ከልክለዋል።ከዚሕ ይልቅ ግን የተዘበራረቀችዉን ግዙፍ ከተማ ዘመኑ-የሚጠይቀዉን የከተማ ማዕረግ አጎናፀፏት።
አራት ዓመት ብቻ በዘለቀ-ሥልጣናቸዉ ኢስታንቡል ላይ የተንሰራፋዉን ሙስናን ነቅለዉ ጣሉ።ብዙ መቶ ኪሎ ሜትር የሚረዝም ቧንቧ ዘርግተዉ የዉሐ ችግሯን አስወገዱ።ከሐምሳ በላይ ድልድዮች፥ ብሺ ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ መንገዶች ገንብተዉ የትራፊክ መጨናነቅን አስወገዱ።የአየር ብክለትን በሰባ-አራት ከመቶ ቀነሱ።ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ሲያበቃ ከተማይቱ የነበረባትን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ከፍለዉ ለኢስታንቡል አራት ቢሊዮን ዶላር ከኢስታንቡል ባንክ አስቀምጠዉ በ1998ተሰናበቱ።
ዛሬ የዓለም የከንቲቦች ጉባኤ የሚባለዉን ማሕበር የመሠረቱት እሳቸዉ ናቸዉ።ኤርዶኸን።ለዚሕም ሐቢታት የተሰኘዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሽልማትን ተሸልመዋል። ሥልጣን በለቀቁ ባመቱ ግን መጥፎ ግጥም ሕዝብ ፊት አንብበሐል ተብለዉ የፓርቲ ሥልጣናቸዉን ተገፈዉ አስር ወር እስራት ተፈረደባቸዉ።አራት ወር ታስረዉ ሲፈቱ የፍትሕ እና የልማት ፓርቲ (AKP በቱርክኛ) የተሰኘዉን የፖለቲካ ማሕበር መሥርተዉ አንካራ ቤተ-መንግሥት የሚገቡበትን ሥልት ያዉጠነጥኑ ያዙ።
አልቆዩም በሁለት ሺሕ ሁለት በተደረገዉ ምርጫ አሸንፈዉ ካሰቡት ደረሱ።ሐያ-አምስተኛዉ የቱርክ ጠቅላይ ሚንስትር።በተከታታይ ለሰወስት ዘመነ-ሥልጣን ቱርክን ሲመሩ የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት አንቻረዉታል። ቱርክ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ለመሆን ከሕብረቱ ጋር የተፈራረመችዉ ሕብረቱ እንደተመሠረተ ነበር።ዉሉ ከተፈረመ-ከአርባ አምስት ዓመት በኋላ አባል የመሆኑን ድርድር የጀመሩት ግን ኤርዶኻን ናቸዉ።
የአዉሮጳ ሕብረት አባል የሆኑት ግሪኮች፥ ስጳኞች፥ ፖርቱጋሎች፥ ኢጣሊያዎች፥ አየር ላንዶች ሲሽመደመዱ የኤርዶኻንዋ ቱርክ ኢኮኖሚ በየዓመቱ የሰባት ነጥብ ሰወስት በመቶ ግስጋሴዉ እንደቀጠለ ነዉ።ሥልጣን ሲይዙ ቱርክ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት IMF 23.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ነበረባት።ኤርዶኻን አብዛኛዉን ዕዳ ከፍለዉ ባለፈዉ ዓመት ማብቂያ የቀረባት ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነዉ።ዘንድሮ ተከፍሎ ያልቃል-ነዉ የኤርዶኻን ዕቅድ።
ኩርዶች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ ትምሕርት በኩርዶች ቋንቋ እንዲሰጥ፥ ጋዜጦች እንዲታተሙ ፈቅደዋል።ከማርኪስስቱ ከኩርድ ነፃ አዉጪ ፓርቲ (PKK) የሰላም ሥምምነት ተፈራርመዋል።
ኤርዶሐን ከቅርብ አመታት ወዲሕ በሚተቿቸዉ ጋዜጠኞችና በመብት ተሟጋቾች ላይ የሚወስዱት ጠንካራ እርምጃ ግን ሁሉም ሲሳካላቸዉ ሁሉም ባልኩት ይደር ስሜት የታበዩ አስመስሎባቸዋል። በሁለት ሺሕ ሰወስት ሥልጣን እንደያዙ ከሁሉም ጎረቤቶች ጋር «የዜሮ-ችግር» የወዳጅነት መርሕ እንከተላለን ብለዉ ነበር።የሊባኖስ ፖለቲከኞችን ለማስማማት የተደረገዉን ጥረት ደግፈዉ ነበር።እስራኤልና ሶሪያን ለማደራደር ብዙ ሞክረዉም ነበር።ዛሬ ግን በማደራደር ሰበብ ብዙ ሚስጥር ያጋሯቸዉን አሰድን ቀንደኛ ጠላታቸዉ አድርገዋቸዋል።
ከዉጪም ከዉስጥም የተጠራቀመዉ ቅሬታ ለተቃዋሚዎቻቸዉ ጉልበት ነዉ-የሆነዉ።እንጂ መንግሥታቸዉ አንድ አደባባይ አፍርሶ አንድ የገበያ አዳራሽ ለማስገንባት ማቀዱ ይሕን ያሕል የሕዝብ ቁጣና ተቃዉሞ ይቀሰቅሳል ማለት በርግጥ ሰበብ እንጂ ምክንያት ነዉ-ማለት ይከብደል።ብቻ ናፋቂዉ አፈፃፀሙና ፍፃሜዉ ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ