ተቃውሞ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአማራ ክልል
የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጋጋት ቢፈጥርም በመንግሥት ለውጥ እምነት በጠፋበት በአማራ ክልል ቁጭት ቀስቅሷል።
ኩራት
በጎንደር ከተማ እምብርት የአፄ ቴዎድሮስ ኃውልት ይታያል። ጎንደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ገቢራዊ ከመሆኑ በፊት ከፍተኛ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰባቸው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከተሞች አንዷ ናት።
ትናንት እና ዛሬ
የአብያተ-መንግሥታት እና የአብያተ-ክርሥቲያናት መገኛ የሆነችው ጎንደር በአንድ ወቅት የመናገሻ ከተማ ነበረች። ዛሬ ከከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ወጣ ሲባል ድህነት በርትቶ ይታያል። «የዋጋ ንረት እየከፋ ነው። መንግሥት ደሞዝ የሚጨምረው በጥቂት የሥራ ዘርፎች ለሚገኙ ሠራተኞች ነው።» ይላል የአንድ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ የሆነው እስጢፋኖስ። ሌሎች መንግሥት በከተማዋ መዋዕለ-ንዋይ እያፈሰሰ አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ።
የወጣቶቹ ስሜት
እንደ ሄኖክ ያሉ ወጣቶች ስለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲያወሩ በምሬት ነው። የቀደመውን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ መከልከላቸውንም ወጣቶቹ ያማርራሉ።
የነጋ ጠባው የኑሮ ትግል
«መኪና አጥባለሁ። ሌላ ሥራ ማግኘትማ አይቻልም።» ይላል የ25 አመቱ ዳዊት «በነርሲግ ዲፕሎማ አለኝ። ነገር ግን መንግሥት ሥራ ሊሰጠኝ ፈቃደኛ አይደለም። መቶ ጊዜያት ሞክሪያለሁ።» ዳዊት ያክላል። ሌሎች በቻሉት መንገድ ሰርተው ገንዘብ ለማግኘት ይሞክራሉ። ታዳጊዎች ጫማ ይጠርጋሉ። ጠዋት ወደ ቤተ-ክርስቲያን የሚሔዱት እንስቶች በምሽት በወሲብ ንግድ ሥራ ይሰማራሉ።
ለመተንበይ አስቸጋሪው ጊዜ
ከጎንደር በሥተ-ደቡብ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመናገሻ ከተማ-ባሕር ዳር ከጣና ሐይቅ ዳርቻ ጀልባዎች አገር ጎብኚዎችን ወደ ገዳማት ለመውሰድ እየተሰናዱ ነው። በዚህ ከጠብ ይልቅ ይቅር መባባል ነግሷል። «ሰዉ በችግሮች ተሰላችቶ ወደ መደበኛ ሕይወቱ መመለስ ይፈልጋል።» ይላል የቱሪስ አስጎብኚው ተስፋዬ። «ግን ደግሞ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ምን እንደሚፈጥር የሚያውቅ የለም።»
ሥራ ፍለጋ
ከዘንባባ ዛፎቹ ሥር በርካቶች የሥራ ማስታወቂያ መለጠፊያ ሰሌዳ ይመለከታሉ። የሥራ ዕድል እጦት እና ድህነት በክልሉ ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ መባባስ ዋና ምክንያቶች ናቸው። ሳምራዊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሉታዊም አዎንታዊም ጎኖች እንዳሉት ትናገራለች። በእሷ አባባል «ኹከቱን በማብረዱ ጥሩ ነው። ነገር ግን ለዜጎች መልካም አይደለም።»
የችግሮቹ ምንጭ
በኢትዮ-ቴሌኮም ተቀጥሮ ለሚሠራው እና 500 ብር መዥረጥ አድርጎ ጅንስ ሱሪ መግዛት ለሚችለው እንደ ኃይሌ ላሉት ጭምር አሳሳቢው ጉዳይ ኤኮኖሚያዊ ብቻ አይደለም። «ከሦስት ዓመታት በፊት በዩኒቨሲቲ ስማር ስለ ከየት መጣነትህ የሚጨነቅ ማንም አልነበረም» የሚለው ኃይሌ «አሁን የአማራ እና የትግራይ ተማሪዎች እርስ በርስ መጋጨታቸው።» ያሳስበዋል።
የኤኮኖሚ እድገት ለማን?
በባሕር ዳር ከተማ የተጀመረ ግንባታን ከሚያሳይ ትልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳ ሥር ያደሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከእንቅልፋቸው እየነቁ ነው። ግንባታው ለእነሱ የሚፈይደው ነገር የለም። ቴሬንስ ሊዮንስ የተባሉት የግጭት አፈታት እና ትንተና ባለሙያ «በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ይሁን መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት እና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በገባቸው ቃል-ኪዳኖች ቅሬታዎች አልተፈቱም።» ሲሉ ይናገራሉ።
አስቀያሚው ቀን-በባሕር ዳር
ከስድስት ወራት በፊት ከባሕር ዳር ከተማ ዳርቻ በሚገኘው ድልድይ በርካቶች የሰላም ምልክት የሆነውን የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው መንግሥትን እየተቃወሙ ተሻግረዋል። ተቃውሞው ከድልድዩ ትንሽ ራቅ ብሎ በ52 የጦር መሳሪያ ባልያዙ ሰዎች ላይ የጸጥታ አስከባሪዎች በከፈቱት የተኩስ እሩምታ ተበተነ። «የጸጥታ አስከባሪዎች ድንገት ከድልድዩ ብቅ ብለው ያለ ምክንያት በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ተኩስ ከፈቱ።» ሲሉ አንድ ቄስ ዕለቱን ያስታውሱታል። «ለመተኮስ ምክንያት እየፈለጉ ነበር።» በማለትም ቄሱ ያክላሉ።
መረጃ
ዛሬ ዛሬ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከወትሮው በተለየ በርካታ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች መመልከት ኢንተርኔትም መጠቀም ይችላሉ። የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በቂ መረጃ ያለው እና ነፃ አሳቢ እንዲሁም ነገሮችን ማነፃጸር የሚችል እየሆነ መጥቷል። «የደርግ ሥርዓት የተሻለ ነበር፤» ይላሉ የ65 አመቷ ወ/ሮ፦ ምክንያታቸው ደግሞ «ከሐብታም ነጥቀው ለደሐ ይሰጣሉ፤» የሚል ነው። በእግሮቻቸው ላይ ባለዉ የጤና እክል ሳቢያ ከቤት የዋሉት እናት «እግሮቼ ቢራመዱ ኖሮ መቃወም እሻ ነበር፤» ሲሉም ይናገራሉ። ጄምስ ጄፈሪ/እሸቴ በቀለ/ ሸዋዬ ለገሠ