1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ከአሜሪካ ሳይንስ ፋውንዴሽን ሽልማት አግኝተዋል

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 11 2009

መቀመጫቸውን ከሀገራቸው ውጭ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ከፍ ያለ ስም ያላቸውን ሽልማቶች በየጊዜው ሲቀዳጁ ታይቷል፡፡ የኬምስትሪ ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር ተረፈ ጌታሁን ከወራት በፊት በአሜሪካን ሀገር ካለ የሳይንስ ተቋም ተመሳሳይ ሽልማት አግኝተዋል፡፡ በኒው ሜክሲኮ ዩኒቨርስቲ መምህር ሲሆኑ ተመራማሪም ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/2bY83
Deutschland Graphen - Die dünnste «Wellpappe» der Welt
ምስል picture alliance / dpa

“ተወልጄ ያደግኩት ሸዋ ክፍለ ሀገር የሚባለው ቦታ ነው፡፡ ቡልጋ የወረዳዋ ስም ሀገረ ማርያም ይባላል፡፡ ስቻት ይባላል ልዩ ቦታ ስሙ፡፡ እንደዚያ ዓይነት ቦታ ባንቧ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንኳን በዚያን ጊዜ አሁንም የለም” ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ተረፈ፡

ረዳት ፕሮፌሰር ተረፈ ከአስኳላ ትምህርት ጋር የተዋወቁት ቀያቸው አቅራቢያ ከተከፈተ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ለአካባቢው ህዝብ ማመልከቻ ጸሀፊ ከነበሩትና ቀለም ከቀመሱት አባታቸው መሰረታዊውን ትምህርት በቤታቸው የተማሩት ተረፈ የአንደኛ ክፍል ትምህርትን በአጭር ጊዜ ፉት አሉት፡፡ አባት ልጃቸው ወደ ሌላ ደረጃ እንዲሸጋገር ጉጉት በማሳደራቸው አስተማሪዎቹን ይጎተጉቱ ያዙ፡፡ በወቅቱ በትምህርቱ ጥሩ የነበረ ተማሪ አንድ ክፍልን ዘሎ በሌላኛው እንዲማር ይደረግ ነበርና እርሱን ለተረፈ እንዲደረግ ጠየቁ፡፡ ትምህርት ቤቱ አንደኛ ክፍልን ብቻ ይዞ የተመሰረተ መሆኑ ችግር ፈጠረ፡፡ ይሄኔ ታዳጊው ተረፈ ሶስት ሰዓት ያህል በእግር ከሚያስኬሄደው የአክስቱ ቤት እንዲማር ተወሰነ፡፡

ተረፈ ከቤቱ ሲርቅ ለትምህርት ያለው ፍቅር ቀዘቀዘ፡፡ አነስተኛ ውጤት በማስመዝገቡም ወደ ቀጣዩ ክፍል ሳይሸጋገር ቀረ፡፡ የቤተሰቡን ናፍቆት ለመወጣት የዘየደው መላ የተሳካላት የመሰለው ተረፈ ወደ ተወለደበት ቀዬ ተመለሰ፡፡ ሆኖም አባታቸው በድንገት በመሞታቸው ነገሩ ሁሉ የጨለመ መሰለ፡፡ ያኔ በትምህርታቸው መበረታት እንዳለበት ተረዳ፡፡ የወላጆቹ ቤት አቅራቢያ ካለችው ትምህርት ቤትም ተመልሶ ገባ፡፡ አንድ ዓመት በዚያ ካሳለፈ በኋላ ግን ቀጣይ ክፍል ባለመኖሩ በድጋሚ ቀዬውን ለመልቀቅ ተገደደ፡፡ ስንቅ እየተላከለት ከሚማርበት ወረዳ ከተማ ተላከ፡፡  

Bildmaterial - der kleinste magnetische Datenspeicher der Welt
ምስል Max-Planck Institut

እንዲህ እንዲህ ሲማሩ እስከ ስምንተኛ ክፍል የቆዩት ተረፈ ደግሞ ለሌላ ዝውውር ተነሱ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታታል ለአራት ዓመታት ደብረብረሃን መከተም ነበረባቸው፡፡ በደብረብርሃን ከመብራት ጋር ተገናኙ፡፡ መጽሐፍት በአንጻራዊነት እንደልብ ማግኘት ቻሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዷቸው ሰባት ትምህርቶች በስድስቱ “ኤ” በማምጣት በአጥጋቢ ውጤት አለፉ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ተረፈ ከስኬታቸው ጀርባ የነበረውን እንዲህ መለስ ብለው ያስታውሳሉ፡፡   

ወጣቱ ተረፈ ዩኒቨርስቲን ከተቀላቀለ በኋላ ለማጥናት የመረጠው ዘርፍ ኬሜስትሪ አልነበረም፡፡ መጀመሪያ የገባው ከፋርማሲ የትምህርት ክፍል ነበር፡፡ ተረፈ የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት እንደ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪነታቸው ሁሉ በከፍተኛ ውጤት ነው፡፡ ሊያውም የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆን፡፡ ከመጀመሪያው ዓመት ጀምሮ በውጤታቸው ላይ ተጠንቅቀው መስራታቸው በስተኋላ ላይ ላስመዘገቡት ውጤት ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ተረፈን በታታሪ ተማሪነታቸው ዘመን የሚያውቋቸው የቀድሞ አስተማሪዎቻቸው በከፍተኛ ውጤት ከተመረቁ በኋላ በመምህርነት አብረዋቸው ሰርተዋል፡፡

ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የኬሜስትሪ ትምህርት ክፍል ዲን ናቸው፡፡ ተረፈን በተማሪነት ዘመኑ በደንብ ያስታውሱታል፡፡ እርሳቸውም ሆነ ሌሎች የኬሜስትሪ ትምህርት ክፍል መምህራን ተረፈን በጥሩ ተማሪነት እና ረዳት መምህርነት እንደሚያነሱት ይናገራሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኬምስትሪ ትምህርት ክፍል አሰራር መሰረት አንድ ጀማሪ መምህር የዶክትሬት ዲግሪውን እሰኪይዝ ረዳት መመህር አሊያም የቤተ-ሙከራ ረዳት ሆኖ ነው የሚቆየው፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ተረፈም ተመርቀው በዚያው በተማሩበት ለመምህርነት ሲቀሩ ይህንኑ መንገድ ተጉዘዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አህመድ ምስክርነት ተረፈ በዚያን ጊዜ በተመሳሳይ ደረጃ ከነበሩት የተሻሉ የሚባሉ መምህር ነበሩ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ተረፈ የሙሉ መምህርነትን ካባ ጭነው ብዙም ሳይቆዩ ነው ወደ ባህር ማዶ የተሻገሩት፡፡

Nano-Auto
ምስል picture-alliance/dpa/Universität Gröningen/R. Wind/M. Roelfs

የዛሬ ሰባት ዓመት የተቀላቀሉት የአሜሪካው አሪዞና ዩኒቨርስቲ የረዳት አስተማሪነት ስራ ሰጣቸው፡፡ ከመምህርነታቸው ጎን የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሲያጠኑ ቆዩ፡፡ በዚያን ጊዜ ነበር “ኳንተም ኬሚስትሪ” ወደሚባለው ዘርፍ አዘነበሉ፡፡ በዚህ ዘርፍ ምርምራቸውን ለማካሄድ የሚረዳቸውን መሳሪያ መስራት ነበረባቸው፡፡ ለዚህም ዩኒቨርስቲው በገንዘብ እንዳገዛቸው ይናገራሉ፡፡ ለምርምር የሚጠቅም አዲስ ዓይነት መሳሪያን መስራት አሁን ወደሚገኙበት ኒው ሜክሲኮ ዩኒቨርስቲ ከመጡም በኋላ ቀጥለውበታል፡፡

ባለፈው ጥር ወር ከአሜሪካ ሳይንስ ፋውንዴሽን የ600 ሺህ ዶላር የምርምር ማካሄጃ የገንዘብ ሽልማት ያስገኘላቸውም ይህ አዲስ አይነት መሳሪያ የመፈልሰፍ ጥረታቸው ነው፡፡ ሽልማቱ በውድድር የሚገኝ እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰር ተረፈ ይናገራሉ፡፡ በሽልማቱ ያገኙትን ገንዘብ አብረዋቸው ለሚሰሩ ተመራማሪዎች ደመወዝ ለመክፈል፣ በምርምሩ የሚሳተፉ ተማሪዎችን ለመደገፍ እና ለምርምሩ የሚያስፈልግ ቁሳቁስ ለመግዛት እንደሚጠቀሙበት ይናገራሉ፡፡ የምርመራቸው ዋና አስኳል “ናኖ ማቴሪያል” ተብለው የሚታወቁ በዓይን የማይታዩ በጣም ጥቃቅን ነገሮችን ለመመልከት የሚያስችል ማይክሮስኮፕ መስራት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ 

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በነበራቸው የትምህርት ጊዜ ያሳለፉትን አስቸጋሪ ጊዜ የማይረሱ የሚስመሉት ረዳት ፕሮፌሰር ተረፈ በተቻላቸው ሁሉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችንም ሆነ የተሻለ የመማር ዕድል ያላገኙትን ለመርዳት ይሞክራሉ፡፡ የመጀመሪያ አመት ትምህርቷን በአሜሪካ ሜኒሶታ ተከታትላ እርቸው ወደሚገኙበት ኒው ሜክሲኮ ዩኒቨርስቲ የተዛወረችው ሜሮን ግርማ በረዳት ፕሮፌሰር ተረፈ እርዳታ ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ አንዷ ነች፡፡ እንደ እርሳቸው የኬሜስትሪ ተማሪ የሆነችው ሜሮን በምርምር ስራቸው እንድትሳተፍ እንዳደረጓት ትናገራለች፡፡ ስለመምህሯ ተከታዩን ትመስክራለች፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ