1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብሬግዚት፤ ያልተቋጨው ውል

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 11 2012

ከቅዳሜው የብሪታንያ ፓርላማ ውሳኔ በኋላ የብሬግዚት እጣ ፈንታ እንደገና ማነጋገር ይዟል። «የብሬግዚት ሂደት እንዴት ይቀጥላል? ብሬግዚት ይሆናል አይሆንም? ከሆነስ እንዴት እና መቼ? ቀነ ገደቡስ ይራዘማል አይራዘምም? ቦሪስ ጆንሰንስ ከገቡበት አጣብቂኝ እንዴት ይወጣሉ?» የሚሉ እና ሌሎችም ግልጽ መልስ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎች ናቸው።

https://p.dw.com/p/3RjTl
Großbritannien London | Boris Johnson will keine Brexit Verlängerung verhandeln
ምስል picture-alliance/dpa/PA Wire/House of Commons

ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት የምትወጣበት የብሬግዚት ውል ከሦስት ዓመት ዓመት በኋላ ዛሬም እጣ ፈንታው አልታወቀም። ሃገሪቱ ከ40 ዓመታት በላይ የቆየችበትን ህብረቱን እንዴት እና መቼ ለቃ እንደምትወጣ ወይም ህብረቱን ጥላ ትውጣ፣ አትውጣ አሁንም ግልጽ አይደለም። የብሪታንያ ህዝብ ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት እንድትወጣ ድምጹን ከሰጠ ሶስት ዓመታት አልፈዋል። ይሁን እና ፍቺው እንዲህ በቀላሉ የሚሳካ አልሆነም። ከሶስት ዓመታት ግድም ድርድር በኋላ የብሪታንያ መንግሥት እና የአውሮጳ ህብረት ባለፈው ዓመት አግባቢ ባሉት፣ ብሪታንያ ህብረቱን ለቃ መውጣት በሚያስችላት የ(ብሬግዚት ውል) ቢስማሙም የብሪታንያ ፓርላማ በተደጋጋሚ ተቃውሞት ሳያፀድቅ ቀርቷል። ይህም ከህዝበ ውሳኔው በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ቴሬሳ ሜይ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ምክንያት ሆኗል።

እርሳቸውን የተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንም ከአውሮጳ ህብረት ጋር ማሻሻያዎች በተደረጉበት የብሬግዚት ውል ላይ ባለፈው ሳምንት ተስማምተው ነበር። ሆኖም ባለፈው ቅዳሜ በውሉ ላይ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የብሪታንያ ፓርላማ ውሉ የሚተገበርበት «ከህብረቱ መውጫ ሕግ» እስኪጸድቅ ድረስ በውሉ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ እንዲገፋ ወስኗል። ውሉ እስከዚያ ድረስ እንዲያዝ ድምጻቸውን የሰጡት 322 የምክር ቤት አባላት ሲሆኑ 306ቱ ደግሞ መቆየቱን ተቃውመው ነበር። 

Großbritannien | Parlament wählt für die Verschiebung des Brexit
ምስል Reuters/Parliament TV

የፓርላማው ውሳኔ ለቦሪስ ጆንሰን ከባድ ምት ተብሏል። ጆንሰን ሦስት ወር ሊደፍን ጥቂት ቀናት በቀሩት የሥልጣን ጊዜያቸው ብሪታንያ በተያዘው ቀነ ገደብ በጥቅምት 20፣ 2012 ዓ.ም የአውሮጳ ህብረትን ለቃ እንድትወጣ ነበር ሲወተውቱ የቆዩት። ይህ ግን የሚሳካ አልመሰለም። ምንም እንኳን ቦሪስ ጆንሰን ፓርላማው በውሉ ላይ የሚሰጠውን ውሳኔ ከገፋ በኋላ፣ «ቀነ ገደቡ ይራዘም ብዬ አልጠይቅም» ቢሉም ሳይወዱ በግድ ፤ ፊርማቸውን ባልያዘ ደብዳቤ፤ ሃገራቸው ህብረቱን ለቃ የምትወጣበት ጊዜ እንዲራዘም የአውሮጳ ህብረትን ጠይቀዋል። ለአውሮጳ ህብረት በላኩት ሌላ ደብዳቤ ደግሞ ቀነ ገደቡ ከጥቅምት 20፣ 2012 በላይ መገፋቱን በግላቸው እንደሚቃወሙ ጠቅሰዋል። 

የቀነ ገደቡ ማራዘሚያ የቀረበላቸው የአውሮጳ ህብረት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ «በጉዳዩ ላይ ከህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ጋር እመክርበታለሁ» ሲሉ መልስ ሰጥተዋል። ከቅዳሜው የብሪታንያ ፓርላማ ውሳኔ በኋላ የብሬግዚት እጣ ፈንታ እንደገና ማነጋገር ይዟል። «የብሬግዚት ሂደት እንዴት ይቀጥላል? ቀነ ገደቡ ይራዘማል አይራዘምም? ቦሪስ ጆንሰንስ ከገቡበት አጣብቂኝ እንዴት ይወጣሉ?» የሚሉ እና ሌሎችም ጥያቄዎች ማነጋገራቸው ቀጥሏል። 
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ እንደሚሉት የቅዳሜው የብሪታንያ ፓርላማ ውሳኔ በቦሪስ ጆንሰን ላይ ገመዱን አክሯል። በተለይ የብሪታንያ ፓርላማ በጠባብ ልዩነት ከብሬግዚት ውል በፊት ይጽደቅ ያለው «የአውሮጳ ህብረት መውጫ ሕግ» በራሱ ለቦሪስ ጆንሰን ተጨማሪ ጫና መሆኑ አይቀርም እንደ አስተያየት ሰጪዎች። «በለውጥ ላይ በሚገኘው አውሮጳ ውስጥ ያለችው ብሪታንያ» (The UK in a changing Europe) በተባለው ድርጅት ተመራማሪ ጂል ሩተር እንደሚሉት ይህ ሕግ ለቦሪስ ጆንሰን ተጨማሪ ፈተና ነው የሚሆነው።

«ሰዎች ቁጥሩ በጣም ተቀራራቢ፣ በአንድ ወይ በሁለት ድምጾች ሊያስተካክሉት የሚችሉት ነው ብለው ያስባሉ። ትኩረት የሚስበው ነገር በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ ቢደርሱም እንኳን በሕጉ በራሱ ለብዙ ጫናዎች መዳረጋቸው አይቀርም። ሕጉን ለመቀየር የሚፈልጉ የብሪታንያ ፓርላማ አባላት በሕጉ ላይ በርካታ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ግፊት ሊያደርጉ ይችላሉ። ምናልባትም ሁለተኛ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ሊጫኗቸው ይችላሉ። ቦሪስ ጆንሰን እነዚህን ሁለት መሰናክሎች ማለፍ መቻል አለመቻላቸውን ጠብቀን ማየት ይኖርብናል።»

Brüssel | Zweiter Tag des EU Gipfel | Donald Tusk
ምስል Reuters/P. van de Wouw

ባለፈው ቅዳሜ የብሪታንያ ፓርላማ ያሳለፈው ውሳኔ ዓላማ፣ ብሪታንያ የአውሮጳ ህብረትን ለቃ እንድትወጣ በተያዘው ቀነ ገደብ ማለትም ጥቅምት 20፣2012 «ያለ ስምምነት ህብረቱን እንዳትለቅ መከላከል ነው» ተብሏል። የቦሪስ ጆንሰን መንግሥት ቅድሚያ ይሰጠው የተባለውን ብሪታንያን ከህብረቱ መውጣት የሚያስችላት ሕግ ከጥቅምት 20፣2012 በፊት ይፀድቃል ብሎ ተስፋ እያደረገ ነው። በሌላ በኩል የብሪታንያ ፓርላማ ስለ ውሉ የሚሰጠውን ውሳኔ ባዘገየበት ባለፈው ቅዳሜ «ብሪታንያ የአውሮጳ ህብረትን ለቃ ትውጣ ወይስ በአባልነት ትቆይ» በሚለው ምርጫ ላይ አዲስ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ በአስር ሺህዎች የተገመቱ ሰልፈኞች በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል። 
በእለቱ የፓርላማ አባላት ባካሄዱት ክርክር ላይ የሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ጆ ስዊንሰን የህዝቡ ጥያቄ ምክንያታዊ  መሆኑን አስረድተዋል። ጆንሰን ግን በርሳቸው አባባል ለህዝቡ ጥያቄ ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉበት ምክንያት አላቸው። «የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውል የሠራተኞች መብቶችን ጥበቃዎችን ያስቀራል፤ በአየርላንድ ባህር ላይ ድንበር ያስቀምጣል። መንግሥት እንዳቀረበው ትንታኔ ከፊናንስ ቀውሱ በላይ በሆነ ደረጃ ኤኮኖሚያችንን ይጎዳል። ዛሬ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ውጭ ሆነው ህዝቡ ለመጨረሻ ጊዜ ድምጹን እንዲሰጥ እየጠየቁ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነዚህን ሰዎች ጥሪ የማይቀበሉት ምርጫው ከተሰጣቸው  ህዝቡ የርሳቸው መጥፎ ውል ተቃውሞ ከአውሮጳ ህብረት ጋር ለመቆየት እንደሚመርጥ ስለ ሚያውቁ ነው።» 
ለዚህ ንግግር ጆንሰን በሰጡት የአጸፋ መልስ ስለ ውሉ መጥፎነት የተነሳውን አስተባብለዋል። «ክቡር አፈ ጉባኤ፤ የተከበሩት እመቤት የተናገሩት ትክክል አይደለም። አዲሱ ውል ለሠራተኞች የሚደረግ ጥበቃን አያነሳም። በተቃራኒው እነዚህን ጥበቃዎች የማጠናከር እድል ይሰጠናል። ህዝቡ ለመጨረሻ ጊዜ ድምጹን እንዲሰጥ ይጠይቃሉ። የዚያኑ ያህል ደግሞ አጠቃላይ ምርጫ እንዳይካሄድ ይከላከላሉ። ለአጠቃላይ ምርጫ ዘመቻ ከማድረግ ይልቅ ብራሰልስ ውስጥ የአውሮጳ ህብረት ለዚህች ሃገር አዲስ እና የተሻለ ውል እንዳይሰጥ ይጠይቃሉ።»
በአዲሱ ውል የከዚህ ቀደሙ የብሬግዚት እና የብሪታንያ የፍቺ ሕግ እንዳለ ይቀጥላል። የአውሮፓ ህብረት የብሬግዚት ዋነኛ ተደራዳሪ ሚሼል ባርንየ እንዳሉት ብሪታንያ ለአውሮጳ ህብረት የምትከፍለው እዳ ወደ 39 ቢሊዮን ፓውንድ ወይም 50 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል። እስከ ጎርጎሮሳዊው 2020 የ14 ወራት የሽግግር ጊዜ ይኖራል። ይህም ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ሊራዘም ይችላል። ብሪታንያ እና የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ሐሙስ የተስማሙበት አዲሱ ውል የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ከዚህ ቀደም ካቀረቡት ውል የሚለይባቸው ነጥቦችም አሉ። የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ ዋና ዋና የሚባሉትን ለውጦች እንዲህ ዘርዝሯቸዋል። 
ይሁን እና እነዚህ ማሻሻያዎች የተደረጉበትን ውል የዋነኛው ተቃዋሚ የሌበር ፓርቲ መሪ ጀርሚ ኮርቢን ከቀደመውም የባሰ ሲሉ አጣጥለውታል። «ይህ ውል ለሥራ ጥሩ አይደለም። ኢንዱስትሪያችንንም ይጎዳል። ለአካባቢ ጥበቃ እና ለተፈጥሮአዊው ዓለማችን አደጋ ነው። መጪው ትውልድ ተጽእኖው ይሰማዋል» በማለት ውሉ በምክር ቤቱ  መጣል ያለበት ነው ሲሉ አሳስበው ነበር። 
የፓርላማ አባላት ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል የተባለው አዲሱ ውል እነዚህን የመሳሰሉ ትችቶች እየቀረቡበት ባለበት በአሁኑ ጊዜ ቦሪስ ጆንሰን ሌላም ሃሳብ አላቸው - አዲስ ምርጫ መጥራት። ካሸነፉ ደግሞ ብሪታንያን ያለ ስምምነት ከአውሮጳ ህብረት ሊያስወጡ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ። በተቃዋሚዎች ግፊት በብሬግዚት ጉዳይ ላይ ሁለተኛ ህዝበ ውሳኔ ሊካሄድም ይችላል። ሌላ አማራጭ ይዘው የሚቀርቡ ፓርቲዎችም ሥልጣን ከያዙ ከአሁኑ የተለየ ሁኔታ ሊፈጠርም እንደሚችል ነው ገበያው የሚገልጸው።
እነዚህ ወደፊት ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ናቸው። አሁን ግን በግልጽ የሚታወቀው የብሬግዚት ውል መቋጫ አለማግኘቱ ነው። ብሬግዚት ይሆናል አይሆንም? ከሆነስ እንዴት እና መቼ? ግልጽ መልስ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎች ናቸው።

Großbritannien London | Demonstration für ein zweites Referendum
ምስል Getty Images/AFP/N. Halle'n

ኂሩት መለሰ

ተስፋ አለም ወልደየስ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ