1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሬግዚት አንደኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 20 2009

ብዙ ቀናት ከወሰደ ንግግር በኋላ በምርጫው 10 የምክር ቤት መቀመጫ ያገኘው የሰሜን አየርላንዱ ሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ በምህጻሩ DUP የሜይን መንግሥት ለመደገፍ ትናንት ተስማምቷል። ያም ሆኖ ሜይ ባለፈው ሳምንት በተጀመረው የብሬግዚት ድርድር የብሪታንያን ፍላጎት ማሟላት የሚችሉበት አቅም ይኖራቸዋል ተብሎ አይታመንም ።

https://p.dw.com/p/2fVJH
Großbritannien Theresa May mit Vertreter der DUP vor Downing Street
ምስል Getty Images/AFP/D. Leal-Olivas

ብሬግዚት በብሪታንያ ፖለቲካ ላይ ያስከተለው ጣጣ

የብሪታንያ ህዝብ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት ለመውጣት ማለትም ለብሬግዚት ከወሰነ አንድ ዓመት አለፈ። ሀገሪቱም ከህብረቱ ለመውጣት የምታካሂደው ድርድር ባለፈው ሳምንት ተጀምሯል። ይሁን እና በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ በብሪታንያ የተከሰቱ ያልተጠበቁ ለውጦች በድርድሩ ሂደት ላይ ጫና ማሳደራቸው እንደማይቀር እየተነገረ ነው። የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው።ለዝግጅቱ ኂሩት መለሰ ።

ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት በተካሄደው የብሪታንያ ህዝበ ውሳኔ ከብሪታንያ ህዝብ 52 በመቶው ከህብረቱ ለመውጣት ከወሰነ ወዲህ ብሪታንያ የፖለቲካ ነውጥ ውስጥ ነው የምትገኘው። የቀድሞ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ከመመረጣቸው በፊት ለብሪታንያ ህዝብ በገቡት ቃል መሠረት በጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 23 ፣2016 ዓም በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ከህብረቱ መውጣትን የደገፈው እና ከህብረቱ ጋር መቀጠልን የመረጠው ህዝብ ቁጥር መቀራረብ ብዙ ያልተገመቱ ክስተቶችን አስከትሏል። ከነዚህም አንዱ የህዝቡ መከፋፈል ነው። ከአንድ ዓመት በኋላ አሁንም ይህ ስሜት እንዳለ ነው። ብሬግዚትን በመደገፋቸው የሚፀጸቱ እንዳሉ ቢሰማም የብሪታንያን ከህብረቱ መውጣት ደግፈው ድምጻቸውን የሰጡ አብዛኛዎቹ ዜጎች ግን አሁንም በዚሁ አቋማቸው የፀኑ መሆናቸውን በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት አስታውቋል። ጆን ከርቲስ የምርጫ ጉዳዮች አጥኚ ናቸው። 

«የህዝቡን አስተያየት በተመለከተ ዋና የሚባል ግልጽ ለውጥ መኖሩን የሚጠቁም ምንም መረጃ የለም። ከ12 ወራት በኋላም አሁን በብሪግዚት የተከፋፈለች ሀገር ናት።»

ቶኒ ጌሪ ኤሴክስ ውስጥ የምትገኘው የትንሽትዋ ከተማ የሮምፎርድ ነዋሪ ናቸው። እርሳቸውን ጨምሮ ከዚህ ከተማ ነዋሪዎች  አብዛኛዎቹ የብሬግዚት ደጋፊዎች ናቸው።

Belgien Brüssel Start der Brexitverhandlungen
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Dunand

«በዚህች ሀገር ውስጥ ብዙ ህዝብ አለ። ዘራቸው ቀለማቸው መጠናቸው አይደለም የሚያሳስበው በጣም ብዙ ሰዎች ናቸው ያሉት። ወደፊት ብዙ ሰዎች እንዳይመጡ ማስቆም አለብን። ምክንያቱም እንሰምጣለን »

የለንደኑ ወኪላችን ድልነሳው ጌታነህም ብሬግዚትን ደግፈው ድምጻቸውን በሰጡት ዜጎች ዘንድ ከአንድ ዓመት በኋላ አሁን የአቋም ለውጥ አይታይም ይላል።

ባለፈው ዓመቱ ህዝበ ውሳኔ ውጤት ሰበብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ከሥልጣናቸው ሲወርዱ የተኩዋቸው ቴሬሳ ሜይ የብሪግዚት ተቃዋሚ የነበሩ ቢሆንም  ወደ ኋላ መመለስ የለም «ብሬክዚት ማለት ብሬክዚት ነው» ብለው የህዝቡን ፍላጎት እንደሚያሟሉ ቃል ቢገቡም ሁሉም ነገር እንዳሰቡት አልሄደላቸውም። ሜይ ባለፈው መጋቢት ከአውሮፓ ህብረት አባልነት

ድምጽለመውጣት በሚያስችለው በህብረቱ ውል አንቀጽ 50 መሰረት ብሪታንያ ከህብረቱ መውጣት እንደምትፈልግ በይፋ ካሳወቁ በኋላ የወሰዱት እርምጃ ልዩ ልዩ ችግሮችን አስከትሎባቸዋል። በተለይ ሜይ ሀገራቸው ከህብረቱ አባልነት በምትወጣበት ድርድር ላይ ጠንካራ አቋም ይዤ መቅረብ ያስችለኛል ሲሉ በጠሩት እና ባለፈው ሰኔ በተካሄደ ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ በብሪታንያ ምክር ቤት የነበራቸውን አብላጫ ድምጽ በማጣታቸው ድጋፍ ፍለጋ ሲባዝኑ ነው የከረሙት። ብዙ ቀናት ከወሰደ ንግግር በኋላ በምርጫው 10 የምክር ቤት መቀመጫ ያገኘው  የሰሜን አየርላንዱ ሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ በምህጻሩ DUP የሜይን መንግሥት ለመደገፍ ትናንት ተስማምቷል። ያም ሆኖ የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ ሜይ ባለፈው ሳምንት በተጀመረው የብሬግዚት ድርድር የብሪታንያን ፍላጎት ማሟላት የሚችሉበት አቅም ይኖራቸዋል ተብሎ አይታመንም ይላል።

 

London Demo gegen Brexit
ምስል picture-alliance/dpa/A. Rain

የብሪታንያ ወግ አጥባቂ መንግሥት እና የሰሜን አየርላንዱ UDP ትናንት በተስማሙት መሠረት የብሪታንያ መንግሥት ለሰሜን አየርላንድ ኤኮኖሚ ድጋፍ የሚውል 1 ቢሊዮን ፓውንድ ለመስጠት ተስማምቷል። በስምምነቱ ለሰሜን አየርላንድ ከሌሎቹ ግዛቶች በተለየ ድጋፍ መሰጠቱ የዌልስ እና የስኮትላንድ ግዛት መሪዎችን አስቆጥቷል። የሰሜን አየርላንድ ተቃዋሚ የሺንፌን መሪም የትናንቱ ስምምነት በብሪታንያ በአየርላንድ መንግሥት እና በሰሜን አየርላንድ  ስምንት ፓርቲዎች  መካከል ከዚህ ቀደም በሰሜን አየርላንድ ሰላም ለማውረድ የተፈረመውን ጉድ ፍራይዴይ የተባለውን ስምምነት ይጥሳል ሲሉ ተቃውመዋል። ገበያው እንደሚለው ይህም ሌላው በብሬግዚት ድርድር ላይ ጫና ማሳደሩ የማይቀር በሜይም ላይ ችግር የዞ የመጣ ጉዳይ ነው።

የብሬግዚት ድርድር የዛሬ ሳምንት በይፋ ሲጀመር የብሪታንያው ተደራዳሪ የብሬግዚት ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ዴቪስ ድርድሩ ፈታኝ እንደሚሆን ሳያነሱ አላለፉም። ሆኖም ሁሉም ወገን ተጠቃሚ የሚሆንበት ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሚጥሩ አስታውቀዋል።

Brexit Verhandlungen beginnen David Davis PK in Brüssel
ምስል Reuters/F. Lenoir

«እነዚህን በመሳሰሉ አስቸጋሪ ጊዜያት ነው ከአውሮፓ የቅርብ አጋሮቻችን ጋር የምንጋራቸውን እሴቶቻችንን እና ውሳኔዎቻችንን  የምናስታውሰው። ከሚለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ይበዛሉ። በድርድሩ ወደፊት ያለጥርጥር ፈታኝ  ጊዜያት ቢጠብቁንም  የሁሉንም ዜጎች ጥቅም የሚያስጠብቅ ውል ለማረጋገጥ  የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።» 

ብሪታንያ የሚኖሩ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ዜጎች ጉዳይ በብሬግዚት ድርድር ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው አብይ ጉዳዮች አንዱ ነው። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ሜይ  ከ3 ሚሊየን የሚበልጡ በብሪታኒያ የሚኖሩ የሌሎች አዉሮጳ ሃገራት ዜጎች ብሪታንያ ከህብረቱ ከወጣች በኋላ መብት እና ጥቅማቸው የሚከበርበትን እቅድ እና ስልት አቅርበዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ አውሮፓ ውስጥ የሚኖሩ 2 ሚሊዮን እንደሚደርሱ የሚገመቱ ዜጎቻቸው መብት እንዲጠበቅ ጠይቀዋል። ድልነሳ እንደሚለው ከዚህ ሌላ ብሪታንያ ከህብረቱ ስትለቅ አንዳንድ ተቋማትን እና ከዚህ ቀደም የገባቻቸውን ውሎችን ጥላ መውጣቷም አይቀርም።

ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት ለመውጣት ከወሰነች በኋላ የብሪታንያ ውሳኔ ህብረቱን ይከፋፍላል ያዳክማል የሚሉ አስተያየቶች ቢሰነዘሩም ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሆኖ

ድምጽነው የሚታየው ። ገበያው እንደሚለው ከዚያን ወዲህ የአውሮጳ ህብረት ይበልጥ የተጠናከረ እና ግልጽ አቋም ይዞ ነው ለድርድር የቀረበው።   

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ