1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባልደራስ የከተማይቱን ነዋሪዎች ማደራጀት ሊጀምር ነው

ሰኞ፣ መጋቢት 30 2011

በአዲስ አበባ ጉዳይ ያሉትን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዲያስችል፣ ህዝባዊ ስብሰባዎች ሊፈቀዱ ይገባል በሚለዉ ሃሳብ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ሙሉ በሙሉ እንደሚስማሙ ተነገረ። የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት የከተማይቱን ነዋሪዎች ማደራጀት ሊጀምር መሆኑም ታዉቋል።

https://p.dw.com/p/3GTPl
Äthiopien PK Addis Abebas Treuhänderrat
ምስል DW/S. Muche

 

በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ዋና ሰብሳቢነት የሚመራው የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት በከተማይቱ ባሉ አስር ክፍለ ከተሞች የአደረጃጀት ስራ ሊጀምር ነው። ምክር ቤቱ የአደረጃጀት ስራውን የሚጀምረው ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ በየክፍለ ከተሞቹ በሚጠሩ ህዝባዊ ስብሰባዎች በኩል መሆኑን አስታውቋል።

የምክር ቤቱ ጸሀፊ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ለDW እንደተናገረው ዛሬ ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ጋር የተገናኘው እስክንድር “በአዲስ አበባ ጉዳይ ያሉትን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዲያስችል፣ ህዝባዊ ስብሰባዎች ሊፈቀዱ እንደሚገባ” ሃሳብ አቅርቧል። በሰላማዊ መንገድ ስብሰባ ማድረግን በተመለከተ ከምክትል ከንቲባው ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ኤልያስ ገልጿል። “በአስሩም ክፍለ ከተማ የከተማውን ነዋሪ ለማደራጀት የተግባር እንቅስቃሴ ሲሰራ ነበር። እርሱ እንቅፋት ገጥሞት ነበር” ብሏል የምክር ቤቱ ጸሀፊ። “በቀጣይ ከሚቀጥለው ቅዳሜ ጀምሮ በክፍለ ከተሞች የማደራጀት ስራ እና አመራሮችን እየመረጡ የመንቀሳቀስ ስራ እንቀጥላለን” ሲል አክሏል።

ከዛሬው የእስክንድር እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ውይይት በኋላ ጋዜጠኛ እስክንድር ከከተማው የፀጥታ ኃላፊ ጋር በስልክ ተነጋግረዋል። የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት ሰብሳቢው እስክንድር፣ ጸሀፊው ኤልያስ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል የፀጥታ ኃላፊው ካገናኟቸው ሰው ጋር በአካል ተገናኝተው ተወያይተዋል።

እነ እስክንድር ሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድን በተከተለ መልኩ ለመንቀሳቀስ ከአዲስ አበባ ከተማ ኃላፊዎች ጋር ከስምምነት ላይ ቢደርሱም ከዚህ ቀደም ባካሄዱት ስብሰባ ያወጡትን የአቋም መግለጫ ለምክትል ከንቲባው በጽሁፍ ለመስጠት ያደረጉት ሙከራ ግን ሳይሳካ ቀርቷል። አራት ነጥብ ያለው የአቋም መግለጫ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በባልደራስ አዳራሽ የተሰበሰቡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ያጸደቁት መሆኑን ጋዜጠኛ ኤልያስ ተናግሯል። የአቋም መግለጫውን አቶ ታከለ ኡማ በፅሁፍ እንዲቀበሉ በእስክንድር በኩል ጥያቄ ቢቀርብም ምክትል ከንቲባው ግን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጨምሮ ገልጿል።

 

አዜብ ታደሰ 

ተስፋለም ወልደየስ