1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡድን-ሃያና የፊናንሱ ችግር

ረቡዕ፣ የካቲት 13 2005

ሞስኮ ላይ በአጠቃላይ ከባንኮች ቁጥጥር እሰከ ግብር፤ ከግብር እስከ ምንዛሪ ይዞታ ብዙ ነገር ተነስቷል። የኮሎኝ ዓለምአቀፍ የምጣኔ-ሃብት ምርምር ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ዩርገን ማተስ እንደሚሉት።

https://p.dw.com/p/17hIC
ምስል Reuters

ቡድን-ሃያ በመባል የሚታወቀው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታትና በተፋጠነ ዕድገት በመራመድ ላይ ያሉ ሃገራት ስብስብ ባለፈው ሰንበት ሞስኮ ላይ የፊናንስ ሚኒስትሮች ጉባዔ አካሂዷል። ጉባዔው በዓለም የፊናንስ ይዞታ ላይ በአጠቃላይና በተለይም በምንዛሪ ልውውጥ ይዞታ ችግሮች ላይ ሲነጋገር የተገኘው ውጤት ብዙም አመርቂ አለመሆኑን ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት።

ጉባዔው ሞስኮ ላይ የተካሄደው ሩሢያ በዚህ ዓመት የስብስቡን ተፈራራቂ ሊቀ-መንበርነት የያዘችው አገር በመሆኗ ነው። ቡድን-ሃያ የሌህማን ባንክ ክስረት ከአሜሪካ ተነስቶ ዓለምአቀፍ የፊንናስ ቀውስን ካስከተለ በኋላ እንደ እሣት አደጋ ተከላካይ ችግሮቹን በጋራ ለመቋቋም መነሣቱ ይታወሳል። ሆኖም አደጋ ላይ የወደቀውን የዓለምን ኤኮኖሚ በማዳን ፍላጎት በጊዜው የታየው አንድነትና ቁርጠኝነት ዛሬ ያን ያህል ጠንክሮ አይታይም። ረገብ ብሏል ለማለት ይቻላል።

ለምሳሌ ያህል በ 2010 ዓ-ም መንግሥታዊ ዕዳን በከፊል ለመቀነስ ቶሮንቶ ላይ ተላልፎ የነበረው ውሣኔ ተግባራዊነት ከግማሽ ልብ ዕርምጃ አላለፈም። የባንኮችን የፊናንስ ቁጥጥርና ሌሎች የፊናንሱን ቀውስ አስመልክተው በጊዜው የተነሱ ለምሳሌ የባንኮችን ቁጥጥር የመሳሰሉ ችግሮችን በመፍታቱ ረገድ ሂደቱ አዝጋሚ ሆኖ ነው የሚገኘው። በጉባዔው ዋዜማም የምንዛሪ ጦርነት እስከመሰኘት የደረሰው የገንዘብ መለዋወጫ ተመን ችግር ብዙ ማነጋገሩ አልቀረም።

ይህን ያስከተለውም የጃፓን የምንዛሪ ዋጋ ቅነሣ ነው። ራሷ የቡድን-ሃያ ዓባል የሆነችው ጃፓን በርካታ ገንዘብን በማተም በቅርቡ የምንዛሪዋን የየንን ዋጋ ስታወርድ ለዚህም ምክንያቷ የአገሪቱን የውጭ ንግድ ማጠናከር ነው። ሆኖም ሞስኮ ላይ የተሰበሰቡት የፊናንስ ሚኒስትሮች የምንዛሪውን ዋጋ ከፍታ የሚወስነው ገበያው ብቻ ሊሆን ይገባል ከሚል መግለጫ ያለፈ ግፊት ለማድረግ አልከጀሉም።

G20 Finanzminister Treffen in Moskau
ምስል Yuri Kadobnov/AFP/Getty Images

የሃያው መንግሥታት ፊናንስ ሚኒስትሮች ሰንበቱን ሞስኮ ላይ የተሰበሰቡት በአንድ ጊዜ በርካታ ቃጠሎዎችን ለማክሰም ወይም ለዓለም የፊናንስ ስርዓት ጥበቃ የቃጠሎ መከላከያ ዘዴዎቻቸውን ለማሻሻል በማሰብ ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ባንኮችን በመቆጣጠሩና የምንዛሪ ጦርነት እንዳይከሰት በማድረጉ ረገድ ከስምምነት ለመድረስ ማለማቸው አልቀረም። ግን የታሰበው ሁሉ አልተሳካም።

ይሁን እንጂ ቡድን-ሃያ መንግሥታት በመጨረሻ ባወጡት የጋራ መግለጫቸው አንዳንድ ሃገራት የምንዛሪያቸውን ዋጋ ዝቅ ለማድረግ የያዙትን ጥረት በማያሻማ ሁኔታ አጥብቀው ኮንነዋል። እርግጥ መግለጫው ጠንካራ ይሁን እንጂ በጉዳዩ ጭብጥ በሆኑ ዕርምጃዎች አልመስማማታቸውም ሌላው ሃቅ ነው።

በዚህ በጀርመን የባደር ባንክ ባልደረባ ሽቴፈን ሻርፌተር የጉባዔውን ውሣኔ አስመሳይ ፓኬት ነው ለማለት ይቻላል ብለዋል። የኮሜርስ ባንክ ዋና የኤኮኖሚ ባለሙያ ዮርግ ክሬመር እንደገለጹት ደግሞ የጉባዔው መግለጫ ይዘት ለነገሩ ብዙም ባልከፋ። ሆኖም ባለሙያው ችግሩንም አያይዘው ጠቁመዋል።

«እርግጥ ጃፓንና ሌሎች ሃገራት ተቃራኒውን ከፈለጉ ስምምነቱ የሚያመጣው ጥቅም የለም። እነርሱ የሚፈልጉት በአጭር ጊዜ በሌሎች ትከሻ ለመጠቀም የሚበጅ የደካማ ምንዛሪ ፖሊሲን ማራመድ ነው»

በተለይም የቶኪዮው የሕትመት ባንክ የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ባለፉት ሣምንታት የምንዛሪ ጦርነት የመፈንዳቱን ስጋት የቀረበ አደጋ እንዲመስል ነበር ያደረጉት። የባንኩ ባለሙያ ሽቴፈን ሻርፌተር እንዲያውም የጃፓንን የገንዘብ ፖሊሲ በሌሎች ምንዛሪዎች ላይ ያለመ የጦርነት ዕርምጃ ብለውታል። እንግዲህ በጉዳዩ ላይ ያለው አመለካከት የተለያየ መሆኑ ነው።

ኮሎኝ ከተማ ውስጥ ተቀማጭ በሆነው በጀርመን የምጣኔ-ሃብት ኢንስቲቲዩት የዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ስርዓት አዋቂ የሆኑት ዩርገን ማተስ በፊናቸው ችግሩ በተለያየ መልክ ተነጣጥሉ መታየት ይኖርበታል ባይ ናቸው። እንደርሳቸው አገላለጽ አንዳንድ የሕትመት ባንኮች፤ ለምሳሌ በስዊትዘርላንድ ከኤውሮ አንጻር የራስን ምንዛሪ ዕርጋታ ለመጠበቅ የሚረዳ የምንዛሪ ፖሊሲን ይከተላሉ።

G20 Finanzminister Treffen in Moskau
ምስል Reuters

ጃፓን በበኩሏ አሁን ለያዘችው የምንዛሪ ፖሊሲዋ መነሻው ሌላ እንደሆነ ነው የምትናገረው። በርሷ አባባል የቶኪዮው የሕትመት ባንክ አዲስ ገንዘብ የሚያትመው የምንዛሪን ዋጋ የሚጥሉ ሂደቶችን ራሱ ለመቋቋም በመፈለጉ ነው። እንግዲህ ገበዮችን በአዲስ ገንዘብ ማጥለቅለቁ በመጀመሪያ ደረጃ የየንን ዋጋ ዝቅ ለማድረግ የሚያገለግል ሣይሆን ይልቁንም የአገሪቱን ኤኮኖሚ መልሶ በማንቀሳቀስ ላይ ያለመ ዕርምጃ ነው።

በቡድን-ሃያ ጉባዔ ላይ ሌላው አጥጋቢ ዕርምጃ ያልተየበት ጉዳይ የቁጠባው ፖሊሲ ነው። እንበል በትክክል የቶሮንቶው የ 2010 ዓ-ም የቁጠባ ግብ! በጊዜው ካናዳ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የቡድን-ሃያ መሪዎች ጉባዔ በኤኮኖሚ ሃያላን የሆኑት መንግሥታት ጃፓንን ሳይጠቀልል የዕዳቸውን መጠን እስከ 2013 በግማሽ ለመቀነስ ተስማምተው ነበር። ታዲያ አሁን 2013 ላይ ስንደርስ አብዛኞቹ የቶሮንቶው ኮሙኒኬ ተፈራራሚዎች ዛሬም ከግቡ ገና ብዙ ርቀው ነው የሚገኙት።

የኮሎኙ ዓለምአቀፍ የምጣኔ-ሃብት ምርምር ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ዩርገን ማተስ ለዕርምጃው መጓደል ምክንያት የሚያደርጉት የአመለካከት ፖሊሲ ልዩነትን ነው።

«እና ጀርመን ውስጥ የምናምነው ኤኮኖሚው በፍጥነት የሚያገግመው ያላሳለሰ ማረጋጊያ ዕርምጃ ሲወሰድ ነው ብለን ነው። እናም ይሄው ለሚኖረው ጎጂ የግብር መቀነስና የወጪ መቆጠብ ተጽዕኖ ብዙም ክብደት አንሰጥም»

በሌሎች ሃገራት በተለይም በአሜሪካ ግን ዕይታው የተለየና መንገዱም ተቃራኒው ነው። በቁጠባ ፈንታ ገንዘቡን በማውጣት የገበያ ፍላጎትን ለማሳደግና በተጨማሪ ዕድገትም ቀውሱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ነው የሚፈለገው። ዓለምአቀፉን የፊናንስ ቀውስ ለመታገል በሚደረገው ጥረት እርግጥ የገንዘብ ገበዮችን ቀረብ አድርጎ መቆጣጠሩ ተገቢ ነው። ግን ማተስ እንደሚሉት ንግዱ እንዳይኮበልል መጠንቀቅም ያስፈልጋል።

«ባንኮችን በጥብቅ መቆጣጠር ካለብን ፤ ይህ እርግጥ የግድ አስፈላጊ ነው፤ ንግዱ እንዳይሸሽና ቀጣዩ ቀውስ በዘርፉ እንዳይከተል ማድረግም ይኖርብናል»

Moskau Treffen G20-Finanzminister
ምስል Reuters

የሆነው ሆኖ የሞስኮው የቡድን-ሃያ ጉባዔ ዓለምአቀፉን የፊናንስ ቀውስ በመታገሉ ረገድ አስፈላጊ የሆነውን የፊናንስ ገበዮች ቁጥጥር በተመለከተም ጉዳዩን ወደፊት ማሸጋሸጉ ነው የታየው። ርዕሱ ምናልባት በፊታችን መስከረም ወር ሣንት-ፔተርስቡርግ ላይ በሚካሄደው የቡድን-ሃያ የፊናንስ ሚኒስትሮች ስብሰባ እንደገና የንግግር አጀንዳ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው። ግን በዚያም ማሰሪያ ማግኘቱ እርግጠኛ ነገር አይደለም።

«ሣንት-ፔተርስቡርግ ላይ ጠቃሚ ውሣኔዎች ሊተላለፉ በመቻላቸው ላይ በበኩሌ እርግጠኛ አይደለሁም። ግን ከዚያ በሚቀጥለው ወይም ቢዘገይ በሚከተለው ጉባዔ ጭብጥ ውጤት ማየታችን የማይቀር ነው»

በቡድን-ሃያ የፊናንስ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ሌላው ዓቢይ የውይይት ርዕስ የግብር ገንዘብ ሹልከትን የመግታቱ ጉዳይ ነበር። ሆኖም የዓለም የፊናንስ ዘብ ለመሆን የሚጥረው ቡድን እዚህም የረባ ዕርምጃ ሲያደርግ አልታየም። ዛሬ እንደ ጉግል፣ አማዞን ወይም ስታርባክስ የመሳሰሉት በዓለምአቀፍ ደረጃ የተስፋፉ ኩባንያዎች ገቢያቸውን ወዲህ ወዲያ በማንሸራሸር ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሲሆኑ ነው የሚታዩት። በዚሁም በመጨረሻ የሚከፍሉት ግብር እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል።

ይህ ደግሞ በዚህ ሊቀጥል አይገባውም። እናም አሁን ይህንኑ ጉዳይ የሚመረምር አንድ የባለሙያዎች ኮሚሢዮን በጀርመን፣ በፈረንሣይና በብሪታኒያ ጥረት ተቋቁሞ አስፈላጊውን ዕርምጃ እያረቀቀ ሲሆን ይህም ተሥፋ ሰጭ ዕርምጃ ሆኖ የሚታይ ነው።

« ታላቋ ብሪታኒያ በዚህ ጉዳይ አብራ ለመስራት መፈለጓ ራሱ ጥሩ ምልክት ነው»

ይሁንና ውጤቱ ለአንዱ ባዶ፤ ለሌላው ደግሞ በተወሰነም ደረጃ ዕርምጃ ሆኖ ሊታይ የሚችል ነው። ግን ይህ የቡድን-ሃያን መሠረታዊ ባህርይ የሚያንጸባርቅ ሣይሆን አልቀረም። ስብስቡ ሃሣብን ከመሰንዘርና የመንፈስ ግፊት ከማድረግ ባሻገር ትዕዛዝ የማስተላለፍና የማስፈጸምም ሆነ መቀጮ የመጣል ሥልጣን የለውም።

ይህም በተለይ በምንዛሪ ፖሊሲው ረገድ ጎልቶ የታየ ነገር ነው። በመሠረቱ ዓለምአቀፍ የምንዛሪ ዋጋን ዝቅ የማድረግ ሂደትን ለመግታት የዲሲፕሊን መሣሪያ የግድ ያስፈልጋል። ይህ ቢኖር ኖሮ የሚጻረረውን መቅጣቱ ባልገደደ! ለማንኛውም በዓለም የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ማግሥት የተዛባውን ሊያርቅ ታላቅ ተሥፋ ተጥሎበት የነበረው የዓለም እሳት አደጋ መከላከያ ሃይል ቡድን-ሃያ በአሁን አዝማሚያው ጥርስ-የለሽ ነብር እየሆነ እንዳይሄድ በጣሙን ነው የሚያሰጋው።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ