1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡሩንዲ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 17 2001

በቡሩንዲ የተሟላው ሰላም ወረደ። የሀገሪቱ መንግስትና በሀገሪቱ የሰላም ሂደት ውስጥ ሳይጠቃለል የቆየው የመጨረሻው ያማጽያን ቡድን፡ የብሄራዊው ነጻነት ኃይላት በምህጻሩ፡ ኤፍ ኤል ኤን ከጥቂት ቀናት በፊት ከመንግስት ጋር የሰላሙን ስምምነት ተፈራርሞዋል።

https://p.dw.com/p/HeBH
ፕሬዚደንት ፒየር እንኩሩንዚዛ
ፕሬዚደንት ፒየር እንኩሩንዚዛምስል AP

በቡሩንዲ ይንቀሳቀስ የነበረውን የመጨረሻውን ያማጽያን ቡድንና መንግስትን ለማስማማት በደቡብ አፍሪቃ፡ በአፍሪቃ ህብረት እና በተመድ ሸምጋይነት ለብዙ ዓመታት የተካሄደው ድርድር የተሳካውን ውጤት በማስገኘት ከጥቂት ቀናት በፊት ተጠናቀቀ። ያማጽያኑ ቡድን፡ የብሄራዊው ነጻነት ኃይላት በምህጻሩ፡ ኤፍ ኤል ኤን ባለፈው ረቡዕ በይፋ የብረቱን ትግል በመተው በቡሩንዲ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ተቀባይነትን አግኝቶዋል። የኤፍ ኤል ኤን ዓማጽያን መሪ አጋቶን ርዋሳም እአአ በ 1993 ዓም የተጀመረው ጦርነት ማብቃቱን ከአራት ቀናት በፊት ከመዲናይቱ ቡጁምቡራ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ በተካሄደ ስነ ስርዓት አረጋግጠዋል። በዚሁ ወቅትም የኤፍ ኤን ኤል ቃል አቀባይ ፓስተር ራቢማና ቡሩንዲ ሰላማዊውን የፖለቲካ ሂደት መጀመርዋን፡ እንዲሁም ወደ መረጋጋቱ ጎዳና መሸጋገርዋን በመግለጽና ተዋጊዎቻቸው ድጋሚ የጦር እንደማያነሱ በማስታወቅ የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን እንደሚፈቱ በአደራዳሪዎቹ ፊት አረጋግጠዋል።
« የኤፍ ኤል ኤን መሪ አጋቶን ርዋሳ ወደ ሀገር ከተመለሱ ጀምሮ ካለፈው ዓመት አንስቶ ጦርነቱ አብቅቶዋል፡ ከመንግስት ጦር ኃይላት ጋር ተዋግተው አያውቁም። »
የአስራ ሶስት ዓመቱ የርስበርስ እአአ በ 2006 ዓም ከተደረሰ የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ቢበርድም ጦርነቱ ወደ ሶስት መቶ ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ህይወት ማጥፋቱ አይዘነጋም። ይኸው አስከፊ ጦርነት አሁን በይፋ ማብቃቱ የተገለጸበት ድርጊት በሀገሪቱ ህዝብ መደዳ የሰላሙን ተስፋ አሳድሮዋል። በሀገሪቱ በብዛት የቱትሲ ጎሳ አባላት በሚገኙበትና በተለያዩ የብዙኃኑ የሁቱ ዓማጽያን ቡድኖች መካከል ለብዙ ዓመታት ስር ሰዶ የነበረው የጎሳ ልዩነት እአአ በ 2005 ዓም ቀዝቅዞ፡ ቡሩንዲ አሁን በቀድሞው የሁቱ ዓማጽያን መሪ በፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ትመራለች፤ የሀገሪቱ ጦር እና የፖሊስ ኃይላትም ከቱትሲ እና ከሁቱ ጎሳ አባላት የተውጣጡ እንዲሆኑ ግልጽ መመሪያ ወጥቶዋል። የቡሩንዲ መንግስትና የመጨረሻው ያማጽያን ቡድን ኤፍ ኤን ኤል ባለፈው ታህሳስ አራት እአአ በ 2006ዓም በተደረሰው የተኩስ አቁም ደምብ ላይ ተደቅነው የቆዩትን የመጨረሻ መሰናክሎች ለማስወገድ መስማማታቸው ይታወሳል። በዚሁ መሰረት፡ ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች በደቡብ አፍሪቃ ባለፈው ሳምንት ተገናኝተው ሶስት ሺህ አምስት መቶ የኤፍ ኤን ኤል ተዋጊዎችን በቡሩንዲ ጦር ኃይል እና ፖሊስ ውስጥ ለማዋኃድ ተስማምተዋል። ሌሎች አምስት ሺህ ተዋጊዎች ደግሞ አራት መቶ ዶላር የአንድ ጊዜ ክፍያ፡ እንዲሁም ለአስራ ስምንት ወራት፡ እንደየማዕረጋቸው፡ ደሞዝ ለመክፈልም ስምምነት ደርሰዋል። ባለፈው ቅዳሜ በአርአያነት ኤኬ አርባ ሰባት የጦር መሳሪያቸውንና መለያቸውን አውልቀው የጣሉት የኤፌን ኤል መሪ አጋቶን ርዋሳ የተደረሰውን ስምምነት ለሀገሪቱ ትልቅ እመርታ ነው ሲሉ አድንቀውታል፤ ይሁንና፡ አሁን ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት የተቀየረው ቡድናቸው በሀገሪቱ በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ቀጣዩ ምርጫ የሚያሸንፍበት ሁኔታ ወደ ሌላ ትልቅ ድል እንደሚያሸጋግረው ተስፋቸውን ገልጸዋል። ራሳ በሀገሪቱ ፕሬዚደንት አንጻር በተፎካካሪነት የመወዳደር ዕቅድ እንዳለቸው ገልጸዋል።
ዋነኛው የመንግስት ተደራዳሪ የነበሩት ጀነራል ኤቫሪስት ንዲያሺምዬ እንዳስረዱት፡ የኤፍ ኤን ኤል ተዋጊዎች በጠቅላላ አሁን በቡሩንዲ በሚገኘው ልዩ የአፍሪቃ ህብረት ጦር ኃይል ዕዝ ስር ይገኛሉ። በምህጻሩ ሲ ኤን ዲ ዲ ኤፍ ዲ ዲ የሚሰኘው የገዢው ፓርቲ ቃል አቀባይ ኦኔዚም ንዱዌማና
የመጨረሻው ያማጽያን ቡድን የብረቱን ትግል እርግፍ አድርጎ የተወበትን ውሳኔውንና በሀገሪቱ ሀቀኟው መረጋጋት ለሚወርድበት ሁኔታ ያሳየውን አዲስ ታታሪነት አሞግሶዋል።
« በዚች ሀገር ውስጥ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ቦታ አለው። የቡሩንዲ ህዝብ በቅርቡ በምናካሂደው ነጻና ግልጽ ምርጫ ይህን ራሱ ይፈርዳል። ህዝቡ ጦርነት የትም እንደማያደርስ ተገንዝቦታል። »
በቡሩንዲ የተመድ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ አማዱ ኡስማን ስምምነቱን ቢያደንቁም፡ የቡሩንዲ መንግስትና ህዝብ አሁን የተገኘውን የሰላም ስምምነትን ወደፊት በትጋት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ከማሳሰብ አልተቆጠቡም።
« የቡድኑ ተዋጊዎች የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን መፍታት መጀመራቸው መልካሙን ሁኔታ ፈጥሮዋል። የጦር መሳሪያ መቀነስ በሀገሪቱ ጸጥታ ዋስትና ይሰጣል ማለት ነው። ለኛ ስምምነቱ የማይቀለበስ ሆኖ እናየዋለን። ግን፡ የጦርነት የማካሄድ ልማድ ጨርሶ ላይጠፋ ስለሚችል ጠንቀቅ ብለን መጠባበቅ ይኖርብናል። ብዙ የምንሰራው ብዙ ነገር ገና አለን። »

DPA/AFP/DW/AAMM