1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጋምቤላ ላሬ ወረዳ ጎርፍ ከ18ሺህ በላይ ሰዎችን ማፈናቀሉን ባለስልጣናት አስታወቁ 

ማክሰኞ፣ መስከረም 5 2013

በጋምቤላ ክልል ላሬ ወረዳ ጎርፍ ከ18ሺህ በላይ ሰዎችን ማፈናቀሉን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ  ወረዳው ኢትዮጵያን ከሱዳን የምትዋሰንበት አካባቢ ነው፡፡ 

https://p.dw.com/p/3iVOl
Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

በጋምቤላ ክልል ላሬ ወረዳ ጎርፍ ከ18ሺህ በላይ ሰዎችን ማፈናቀሉን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ ። ወረዳው ኢትዮጵያን ከሱዳን የምትዋሰንበት አካባቢ ነው፡፡ 
የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ከተፈናቃዮች መካከል ወ/ሮ ኛዳክ ፓችን ጠቅሶ እንደዘገበው ሰሞኑን እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በፈጠረው ጎርፍ ምክናያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከነቤተሰቦቻቸው በትምህርት ቤት አጥር ጊቢ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡  መንግስት የአልባሳትና የምግብ አቅርቦት ባለማድረጉም ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ወ/ሮ ኛዳክ ተናግረዋል፡፡ 
በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን የላሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋርዊች ቢየል በስልክ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ሱዳንንና ኢትዮጵያን የሚያዋስነው ጂካዎ ወንዝሞልቶ በተፈጠረው ችግር ከ18ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ የሚኖሩትም በትምህርት ቤቶች እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ 
እንስሳት እንደሞቱና የግጦሽ ሜዳዎችም በጎርፍ በመሸፈናቸው እንስሳቱም ለከፋ ርሀብ መጋለጣቸውን ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል፡፡  አደጋው ከጳጉሜ ጀምሮ የተከሰተ ሲሆን ከክልል እርዳታ እንዲቀርብ ሪፖርት ቢደረግም ጉዳቱን መጥቶ ከመመልከት ውጪ እስካሁን ምንም እርዳታ እንዳልተገኘ ገልፀዋል፡፡ 
የጋምቤላ ክልል አደጋ መከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ አቶ ሰይፉ ወልዴ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የአካባቢው ሰዎች አኗኗር ለእንደዚህ ዓይነት አደጋ እንደሚያጋልጥ አመልክተዋል፡፡ በመሆኑም ሰሞኑን በአካባቢው የጎርፍ መጥለቅለቅ መድረሱን አመልክተው የተጠቀሰው የእርዳታ ፈላጊ ቁጥር ግን የተጋነነ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ሆኖም እርዳታ ወደ አካባቢው ለመላክ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡  በዘንድሮው ክረምት በተለያዩ አካባቢዎች የጣለው ከባድ ዝናብ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጎርፍና ናዳ በመፍጠሩ በርካቶች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ 
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ