1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጅማ ግጭት መከሰቱ ተሰማ

Merga Yonas Bulaሐሙስ፣ ሰኔ 9 2008

በጅማ ከተማ፣ የም ልዩ ወረዳ ቁምቢ ቀበሌ ሰኔ 8 ቀን 2008 ዓ.ም ማንነታቸዉ እንዳይለይ ፊታቸዉን የሸፈኑ ሰዎች መስጊድ በመግባት የአካባቢዉ ኗሪ በሆኑ ሙስሊሞች እና ከቤተክርስቲያን ወጥተዉ ወደ ቤታቸዉ ይሄዱ በነበሩ የኦርቶዶክ ክርስቲያን እምነት ተከታይ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸዉን የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እና ድረ ገፆች ያመለክታሉ።

https://p.dw.com/p/1J8IT
Karte Äthiopien englisch

[No title]

እንደዘገባዎቹ ከጥቃት አድራሾቹ አንዱ ሲያዝ ሌሎቹ አምልጠዋል። ተጎጂዎች ወሊሶ እና አዲስ አበባም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸዉ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉት መካከል ስማቸዉ እንዳይገለጽ የጠየቁት በጅማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ባልደረባ መንግሥትም ሆነ የማኅበረሰቡ አካላት ጉዳዩን እየመረመሩ መሆኑን በአጭሩ ገልጸዉልናል።

ይህን አስመልክቶ መረጃ እንዳለዉ ለማጣራት ወደ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም ደዉለን ነበር። ምክትል ፕሬዝደንቱ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ገልጸዉልናል።በፌደራል እና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቁ በተጠቀሰዉ ስፍራ ሃይማኖትም ሆነ ብሔር ላይ ያተኮረ ግጭት እንዳልተፈጠረ በመግለጽ፤ አንድ ግለሰብ ጉዳዩ ባልታወቀ ምክንያት በተባለዉ ቦታ አራት ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረሱን ተናግረዋል።

እንዲህ አይነት ግለሰባዊ ድርጊት በየትም ቦታ የሚከሰት ነዉ የሚሉት አቶ አበበ መንግሥት በጥብቅ እየተከታተለ እና ወደ ፍትህ እያመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ