1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በድሬዳዋ 21 የጤና ባለሙያዎች በሥራቸው ላይ ሳሉ በኮሮና መያዛቸውን አስተዳደሩ አስታወቀ

ሰኞ፣ ሐምሌ 27 2012

በድሬዳዋ 21 የጤና ባለሙያዎች በሥራቸው ላይ ሳሉ በኮሮና መያዛቸውን የከተማ አስተዳደሩ የጤና ቢሮ አስታወቀ። በድሬዳዋ በኮሮና ከተያዙ መካከል 23 ታራሚዎች እና 24 የጸጥታ አስከባሪዎች ይገኙበታል። የዘጠኝ አመት አዳጊን ጨምሮ ለስደት ወደ ጅቡቲ የተጓዙ ኢትዮጵያውያን በተሕዋሲው መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል።

https://p.dw.com/p/3gM5l
Äthiopien Lemlem Bezabih

ታራሚዎች፣ ፖሊሶች እና ስደተኞች ጭምር በኮሮና ተይዘዋል

በድሬደዋ የኮሮና በሽታ ስርጭት አሁን ባለበት ደረጃ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መምጣቱን የመስተዳድሩ ጤና ቢሮ አስታወቀ። የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል አስገዳጅ መመሪያዎችን ማስተግበር እና የእንቅስቃሴ ገደብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንድ የጤና ባለሞያ ተናግረዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ይዘሮ ለምለም በዛብህ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በህብረተሰቡ ዘንድ እየታየ ባለው መዘናጋት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱንና ድሬደዋ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ከፍተኛ ስጋት ያለባት ከተማ ሆናለች። 

በአስተዳደሩ አቅም በፈቀደ መልኩ እየተካሄደ ባለው የኮቪድ ምርመራ ቫይረሱ እየተገኘባቸው ካሉ የህብረተሰቡ ክፍሎች አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸውን ኃላፊዋ አስረድተዋል። 

የጤና ባለሞው ዶክተር አቤል መልካሙ ለዶይቼ ቬለ በስልክ  በሰጡት አስተያየት “የመመርመር እቅም ዝቅተኛ መሆን እንጂ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል” ጠቅሰው መደረግ አለበት ያሉትን አስተያየት ሰተዋል። 

ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤት የኮሮና ስርጭት ስጋት ናቸው መባሉን በሚመለከት ጥያቄ የቀረበላቸው የጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በፖሊስ ጣቢያዎች የጥንቃቄ አሰራር ስራ ላይ እንዲውል መደረጉን ገልፀው በማረሚያ ቤት ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር እየተሰራ ያለውን ስራ ጠቁመዋል። 

በአስተዳደሩ እስካሁን የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው አምስት መቶ ሰባ አምስት ሰዎች አስራ አምስቱ ህይወታቸው ማለፉን፤ አራት መቶ ሃያ አምስት የሚሆኑት አገግመው መውጣታቸውንና  በአሁን ሰዓት አንድ መቶ ሰላሳ ሶስት የሚሆኑ ሰዎች በተለያዩ ህክምና ማዕከላት ውስጥ መኖራቸውን ወ/ሮ ለምለም በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል፡፡
መሳይ ተክሉ
ነጋሽ መሐመድ