1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኮት ዲቯር ፣ የሁለት ርእሳነ-ብሔር መሠየም ያስከተለው ቀውስ፣

ሰኞ፣ ኅዳር 27 2003

በምዕራብ አፍሪቃ በምትገኘው ሀገር በኮት ዲቧር ኅዳር 19 ቀን 2003 ዓ ም፣ ዳግመኛ የማጣሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተካሂዶ አላሳነ ዑታራ ማሸነፋቸውን የምርጫ ኮሚሽን ቢያረጋግጥም፣

https://p.dw.com/p/QQrY
ታቦ እምቤኪ፣ ከሎራ ግባግቦ ጋር፣ምስል AP

እ ጎ አ ከ 2000 ዓ ም አንስቶ የቅርብ ጊዜው ምርጫ እስከታከሄደበት ድረስ በሥልጣን ላይ የቆዩት ሎራ ግባግቦ ሥልጣን አላስረክብም በማለታቸው ዐቢይ ውዝግብ ተፈጥሯል። የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚዳንት ታቦ እምቤኪ ያደረጉት የሽምግልና ጥረትም አንዳች የተከረው ነገር የለም። ሁለቱም የሥልጣን ተፎካካሪዎች ፤ የየበኩላቸውን የሚንስትሮችም/ቤት አቋቁመዋል። ውዝግቡ በአንዲህ ከቀጠለ ፣ ኮት ዲቯር እንደገና እርስ -በርስ ጦርነት ውስጥ እንዳትገባ ብርቱ ሥጋት አለ።

አላሳነ ዑታራ 54 ከመቶ ፤ ተፎካካሪያቸው ሎራ ግብግቦ ደግሞ 51,45 ከመቶ ድምፅ ማግኘታቸው የተገለጠ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ የዑታራን አሸናፊነት ተቀብሎታል። 53 አባላት ያሉት የአፍሪቃ ኅብረትም ተመሳሳይ አቋም ያለው በመሆኑ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚዳን ታቦ እምቤኪ፣ ይሸመግሉ ዘንድ ልኮ፣ ጥረታቸው ፍሬ አላስገኘም። ሎራ ግብግቦ በምንም ዓይነት ሥልጣን አሳልፌ አልሰጥም ከማለታቸውም ፣ የራሳቸውን የቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓት በማዘጋጀት ፕሬዚዳንትነታቸውን አውጀዋል። የቀድሞው የአማጽያን መሪና ያሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር ጊዮም ሶሮ፣ ትናንት የዑታራ ተጓዳኞች የተባሉ፣ የአዲሱ መንግሥት ሚንስትሮች ናቸው ያሏቸውን 13 ሰዎች ሠይመዋል። ራሳቸው የጠቅላይ ሚንስትርነቱንና የመከላከያ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ደራርበው ይዘዋል። ሶሮ፤ ለፈረንሳይ ራዲዮ በሰጡት ቃልም ፤ ኮት ዲቯር ከሁለት አትከፈልም ሲሉ ተናግረዋል። በምርጫ መሸነፋቸውን አልቀበልም ያሉት ሎራ ግባግቦ፣ በበኩላቸው የአቢጃ ዋና ዩኒቨርስቲ አስተዳዳሪ የነበሩትን የኤኮኖሚ ምሁር Gilbert Marie N’gbo Ake ን ጠ/ሚንስትር እንዲሆኑ ሾመዋቸዋል።

የአፍሪቃ የሰብአዊ መብት ማኅበር ፣ በፈረንሳይ ዓለም አቀፍ ራዲዮ ባሰማው ቃል ላይ፣ ሎራ ግባግቦ የመራጩን ህዝብ ፍላጎት ያከብሩ ዘንድ ጠይቋል። የዚሁ ማኅበር ሊቀመንበር፣ ኢብራሂም ኮነ፣

«ሎራ ግባግቦ ፣ ኀላፊነት የሚሰማው ሰው መሆናቸውን እንዲያሳዩ፣ ለራሳቸውም ክብር ሲሉ ተገቢውን እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። በኮት ዲቯር ህዝብ ለተመረጡትና፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ድጋፍ ለተሰጣቸው አላሰነ ዑታራ ሥልጣኑን ቢያስከብሩ ይበጃል።»

ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሣ፣ የምዕራብ አፍሪቃው የምጣኔ ሀብት ማኅበረሰብም (ECOWAS)ነገ ፤ በናይጀሪያ መዲና በአቡጃ አስቸኳይ የአባል ሀገራት የመሪዎች ስብሰባ እንዲካሄድ ጥሪ አስተላልፏል። ይህን ማኅበረሰብ በመወከል ፤ የቡርኪና ፋሶው ርእሰ ብሔር ብሌስ ኮምፓዖሬ ይሆናሉ ለሽምግልና የሚሠማሩት። የተባበሩት መንግሥትት ድርጅት፣ ዩናይትድ እስቴትስና የአውሮፓው ኅብረት፣ በድምፅ ቆጠራው መሠረት ብላጫ ያመጣውን የደገፉ ሲሆን፣ የአፍሪቃ ኅብረት በበኩሉ፣ ካለፈው ሳምንት ወዲህ ከምርጫው ጋር በተያያዘ አምባጓሮ ቢያንስ 17 ሰዎች መሞታቸውን መንስዔ በማድረግ፣

ውዝግቡ፣ በአገሪቱ ላይ ሊገመት የማይችል ብርቱ መዘዝ ያስከትላል ሲል አስጠንቅቋል። በመሃሉም ፍጥጫው ያስፈራቸውበመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፤፣ የዑታራ ደጋፊዎች በከፊል ከሚቆጣጠሩት የኮት ዲቯር ግዛት ወደ ምዕራብ እየሸሹ አጎራባች ላይቤሪያ ገብተዋል። ሎራ ግባግቦ፣ የአገሪቱ ድንበር በመላ ዝግ እንዲሆን የሚል አዋጅ ቢያስነግሩም፤ ከ 300 በላይ የሚሆኑ የአገሪቱ ተወላጆች አሁን ላይቤሪያ ግዛት ውስጥ ነው የሚገኙት።

20 ሚሊዮን ዜጎች ያሏት ኮት ዲቯር፣ አሁን በጭንቅ ላይ የምትገኝ ስትሆን ምን ቢደረግ ይበጃል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ከመገኘቱ በፊት ታቦ እምቤኪ ፣ ትናንት አቢጃ፣ እንደገቡ እንዲህ ብለው ነበር።

«ምን ማድረግ እንደሚገባ ሃሳብም ሆነ ምክር ከማቅረባችን በፊት፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚነሱትን ነጥቦች ሁሉ ለማዳመጥ እንፈልጋለን። »

እ ጎ አ በ 2002 እና 2003 ዓ ም፤ በተካሄደ የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ፣ አገሪቱ በሰሜንና ደቡብ መካከል ከሞላ ጎደል መሳ-ለመሳ ከሁለት መከፈሏ አይዘነጋም።

ኮት ዲቯር እንደገና ወደ እርስ -በርስ ጦርነት ካመራች ፤ የምዕራብ አፍሪቃ አገሮች ፀጥታ እንዳይታመስ በተጨማሪ ያሠጋል። ሴራሊዮንና ላይቤሪያ ገና ከእርስ በርስ ጦርነት ቁስል አላገገሙም። ማሊና ቡርኪና ፋሶም በፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ረገድ ስደተኞችን የማስተናገድ አቅም የላቸውም። ባለፉት ጊዜያት ፣ ህግ-ወጥ በሆነ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመግባት ከጣሩት ምዕራብ አፍሪቃውያን ፣ አብዛኞቹ፤ ከኮት ዲቯርና አጎራባቾቿ የፈለሱ መሆናቸውም ይነገራል።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ