1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦዲንጋ ደጋፊዎቻቸው በምርጫው እንዳይሳተፉ አሳስበዋል

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 14 2010

በኬንያ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በድጋሚ እንዲካሄድ የተወሰነው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የፊታችን ሐሙስ ጥቅምት 16 ይካሄዳል፡፡ ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ቀናት ግን የተቃዋሚ ዕጩ ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው፡፡ ከፖሊስ ጋርም ተጋጭተዋል፡፡ 

https://p.dw.com/p/2mR3I
Kenia Wahl | Protest in Nairobi | Anhänger Opposition National Super Alliance
ምስል Reuters/T. Mukoya

ኦዲንጋ ደጋፊዎቻቸው በምርጫው እንዳይሳተፉ አሳስበዋል

ራይላ ኦዲንጋ በምርጫ ዕለት ሐሙስ ሰልፍ ጠርተው እንደነበር ቀደም ሲል ተዘግቦ የነበረ ቢሆንም ዛሬ በሰጡት ቃለ ምልልስ ግን ይህን አስተባብለዋል፡፡ ደጋፊዎቻቸውን ያሳሰቡት “በምርጫው እንዳይሳተፉ እና በድምጽ መስጫ ዕለት በቤት እንዲቀመጡ” እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ኦዲንጋ እንዲህ እርስ በእርስ የሚጣረሱ መግለጫዎች ማውጣታቸው ስጋት ፈጥሯል፡፡ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታም “ከፋፋይ መግለጫዎች” በማውጣት ተተችተዋል፡፡ እንደዚህ አይነት የፖለቲከኞቹ ሽኩቻዎች ሀገሪቱን ከምርጫ በኋላ ወደ ብጥብጥ እንዳይከታት ተፈርቷል፡፡ በሀገሪቱ ከምርጫው አስቀድሞ ውጥረት ሰፍኗል፡፡  

የተቃዋሚ መሪው ራይላ ኦዲንጋ በምርጫው እንደማይሳተፉ ቀደም ብለው ቢያሳውቁም አንድ የኬንያ የምክር ቤት አባል ግን ኦዲንጋ በምርጫው “የመሳተፍ ግዴታ አለባቸው” ሲሉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውት ነበር፡፡ ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት “በኬንያ ህገ መንግስት መሰረት ማንኛውንም ዕጩ ተወዳዳሪ በምርጫ ተሳተፍ ብሎ ማስገደድ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ከምርጫ የመውጣት መብት አላቸው” ብሎ በዛሬው ዕለት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የምክር ቤት አባሉን አቤቱታም ውድቅ አድርጎታል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች ይህንን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ “ለተቃዋሚዎች ትልቅ ድል ነው” ብለውታል፡፡ በምርጫው እንዳይሳተፉ እየተጎተጎቱ ላሉት የተቃዋሚ ዕጩው ደጋፊዎችም “ትልቅ ትርጉም አለው” ይላሉ፡፡

ምርጫውን አስመልክቶ ከተባባሪ ዘጋቢያችንን ፍቅረማርያም መኮንን ጋር የተደረገውን ቃለምልልስ የድምጽ ማቀፉን በመጫን ያድምጡ።

ፍቅረማርያም መኮንን    
ተስፋለም ወልደየስ
አርያም ተክሌ