1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

በጥናቱ ስምንት ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ

ረቡዕ፣ ሰኔ 6 2010

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ትልቁ የተባለውን የዘረ መል አወቃቀር ጥናት እንደሚያካሄዱ ባለፈው ሚያዝያ አስታውቀው ነበር። ስር ሰደድ በሚባሉት “ስኪዞፈርኒያ” እና “ባዮፖላር ዲስኦርደር” የአእምሮ ጤና በሽታዎች ላይ ትኩረት የሚያደርገው ዝግጅቱ ተጠናቀቆ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀምር ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/2zVTp
Symbolbild Grundsatzurteil USA zur Patentierung menschlichen Erbguts
ምስል Fotolia/Vasiliy Koval

በኢትዮጵያ ትልቁ የዘረ መል አወቃቀር ጥናት ሊካሄድ ነው

በጎርጎሮሳዊው 1913 ዓ.ም. የተመሰረተው የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የህዝብ ጤና ትምህርት ቤት በአሜሪካ በዘርፉ ትምህርት ከሚሰጡ እና ምርምር ከሚያካሄዱ ተቋማት በዋናነት ይጠቀሳል። ትምህርት ቤቱ በአፍሪካ ካሉ ስድስት ዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር የጀመረው የዘረ-መል አወቃቀር ጥናት በየዓይነቱ ለየት ያለ እንደሆነ ይነርለታል። 

የአእምሮ ጤና በሽታዎችን መንስኤ ለማወቅ የሰው ልጅን ዘረ መል አወቃቀር ማጥናት የተለመደ አሰራር ቢሆንም ምርምሩ እስካሁን በምዕራባውያን ሀገራት ዜጎች ላይ ብቻ ማተኮሩ ግን ከፍተኛ ክፍተት ፈጥሮ ቆይቷል።  ይህን አሠራር ለመለወጥ ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት የአፍሪካ ሀገራት ሰፋ ያለ ጥናት ለማካሄድ በየሀገራቱ ካሉ ዩኒቨርስቲዎች ጋር ስምምነት አድርጓል። በኢትዮጵያ በኩል ጥናቱን ለማካሄድ ኃላፊነቱን የወሰደው አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው።

Äthiopien Universität Adis Ababa
ምስል picture alliance/robertharding/M. Runkel

ጅማሬው ከአንድ ወር በፊት ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያው ጥናት እስከዛሬ ከተካሄዱት ትልቁ መሆኑ ተገልጿል። በአዲስ አበባ  ዩኒቨርስቲ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚያስተምሩት ዶ/ር ሰለሞን ተፈራ በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ጎብኚ ተመራማሪ ናቸው። “በሀገራችን የእዚህ የዘረ መል (genetics) ጥናቶች በሰውም ላይ፣ በዕጽዋት እና እንስሳት ላይም ይደረጋል። በተለይ ከእኛ ጥናት ቀደም ብሎ በሰው ላይ ይደረጉ የነበሩ የዘረ መል ጥናቶች በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ ናሙናዎች ላይ ነው እነዚህ ጥናቶች የተደረጉት። እኛ የምናካሂደው ጥናት ግን በሀገራችን እስከዛሬ ከተደረጉት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነው። ስምንት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ናቸው እንግዲህ በጥናቱ የሚሳተፉት። ስለዚህ ይሄ ቁጥሩ በራሱ እስካሁን በሀገራችን በተመሳሳይ ከተደረጉ ተመሳሳይ በሰው ላይ የተደረጉ የዘረመል ጥናቶች ጋር ሲነጻጸር ይሄ ቀዳሚው ያደርገዋል” ይላሉ ተመራማሪው። 

የእነ ዶ/ር ሰለሞን ጥናት ትኩረት የሚያደርገው በዓለም  ከባድ የአእምሮ ጤና ችግሮች ተብለው በሚታወቁት “ስኪዞፈርኒያ” እና “ባዮፖላር ዲስኦርደር” በሽታዎች ላይ ነው። በአማርኛ አቻ ትርጓሜ ያልተበጀላቸው እነዚህ የአእምሮ ጤና ችግሮች እንዴት ያሉ ናቸው? ዶ/ር ሰለሞን ትንታኔ አላቸው።

“ስኪዞፈርኒያ በዋናነት  የአስተሳሰብ፣ የሀሳብ መዋዥቅ ወይም ደግሞ መዛባት ነው። አንድ ሰው አስተሳሰቡ ሲዛባ ለምሳሌ ያለምክንያት መጠራጠር፣ ያለ ምክንያት የተለያዩ ጉዳዮችን ሌሎች ሊጋሩት የማይችሉትን ሀሳቦች አእምሮው እያመጣ ሲያስጨንቀው ነው። ለምሳሌ በቴሌቪዥን ስለእኔ ይነገራል፣ ሰዎች ይከታተሉኛል፣ ሊያጠቁኝ ነው የመሳሰሉት የተዛቡ ሀሳቦች ሲያመነጭ እንዲሁም ደግሞ በስሜት ህዋሳቶቹ ሌሎች ሰዎች የማይጋሩት ስሜቶች ሲቀበል ነው። ለምሳሌ ድምጾች መስማት፣ የሌሉ ነገሮች ማየት የመሳሰሉት እንግዲህ የስኪዞፈርኒያ ዋናዎቹ መገለጫዎች ናቸው። ባይፖላር ደግሞ በተቃራኒው የስሜት መዛባት፣ ምክንያታዊ ያልሆነ ደስታ፣ መፈንደቅ እንዲሁም ደግሞ ምክንያታዊ ያልሆነ ድብርት እንግዲህ አንድ ሰው ባይፖላር አለበት ስንል ስሜቱ በሁለት የስሜት ጽንፎች መሃል ሲዋዥቅ ማለት ነው። ስያሜው ራሱ ባይፖላር የተባለበት ምክንያት ሁለት ዋልታዎች ወይም ጽንፎች ለማመልከት ነው። ለምሳሌ በጂኦግራፊ ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ እና ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ አለ። እነዚህ በጣም የተራራቁ ጽንፎች ናቸው። የአንድ ባይፖላር ያለበት ሰው ስሜትም ልክ እንደእነዚህ ጽንፎች የdepression እና mania መፈራረቅ ነው እንግዲህ ባይፖላር የተባለበት ምክንያት። ከመደበኛው የስሜት መለዋወጥ ከፍ ባለ ደረጃ የስሜት መዛባት ሲያጋጥም ነው።  ስለዚህ ልዩነታቸው ስኪዞፈርኒያ የአስተሳሰብ መዛባት ሲሆን ባይፖላር ደግሞ የስሜት መዛባት ነው” ሲሉ ልዩነቶቻቸውን ይዘረዝራሉ።      

Symbolbild Außerirdische Silhouette
ምስል Colourbox

በእነዚህ የአእምሮ ጤና ችግሮች ላይ አተኩሮ የዘረ መል ጥናት ማካሄድ የተፈለገበት ምክንያት የህመሞቹ መንስኤ በዘር የሚወረስ የበሽታዎቹ ተጋላጭነት ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው። በሽታዎቹ በዋናነት በአዋቂነት የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ሰዎችን የሚያጠቁ ቢሆኑም የህመሞቹ ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት በአስራዎቹ መጨረሻ ወይም በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል መጀመሪያ ላይ እንደሆነ ዶ/ር ሰለሞን ያስረዳሉ። የበሽታዎቹ ተጋላጭነት በዘር የሚወረስ ስለመሆኑ በጥናትም ጭምር እንደተደረሰበት ምሳሌ ጠቅሰው ያብራራሉ። 

“ለምሳሌ ስኪዞፈርኒያ የተባለው በሽታ 80 በመቶ ያህል በዘር የመተላለፍ ባህሪ እንዳለው ታይቷል። ባይፖላር ዲስኦርደር የተባለው እንደዚሁ እስከ 70 በመቶ በዘር የመተላለፍ ባህሪ እንዳለው ታይቷል። ስለዚህ ይህንን ጥናት ለማድረግ መሰረት አለው። ጥናቱ ከፍተኛ ገንዘብ እና ጉልበት የሚጠይቅ በዓለም ላይ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ጥናት ነውና ይህን ጥናት ለማድረግ ስንነሳሳ በዋናነት እስካሁን  የተደረጉ ምርምሮችን መሰረት አድርጎ ነው ይሄ እንግዲህ ለበርካታ አስርተ ዓመታት ሲደረጉ የነበሩ ምርምሮች ያሳዩትን ፍንጭ ተከትሎ ዓለም አቀፍ ይዘት ባለው መልኩ ጥናቱ እንዲደረግ ነው እንግዲህ የተወሰነው” ይላሉ ዶ/ር ሰለሞን።    

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ ሀገራት ላይ ከአእምሮ ጤና ችግሮች ጀርባ ያሉ የዘረ መል ምክንያቶችን ለመረዳት የሚደረጉ ምርምሮች በጣም አናሳ ናቸው። በእነዚህ ሀገራት የህዝብ ቁጥር ማሻቀቡ እና አማካኝ የዕድሜ ጣሪያ  እየጨመረ መምጣቱ ለጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጠው ምክንያት ሆኗል። በላንሴት የምርምር መጽሄት የታተመ አንድ ጥናት ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ ሀገራት ከአእምሮ በሽታዎች ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ጉዳቶች የተጠቁ ሰዎች በህመም የሚያሳልፉት ጊዜ በቀጣዩዎቹ 30 ዓመታት በእጥፍ እንደሚጨምር ጠቁሟል።

Symbolbild DNA Probe Y-Chromosom
ምስል picture-alliance/dpa

ቁጥሮቹ ይህን ቢያመለክቱም በእነዚህ ሀገራት ለበሽታዎቹ አሁን እየተሰጠ ያለው ህክምና በአብዛኛው ውጤታማ አይደለም ይላል ጥናቱ። ከአእምሮ ጋር ለተያያዙ በሽታዎች ከሚሰጡ ህክምናዎች ግማሽ ያህሉ ብቻ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣታቸውን በማንሳት የጉዳዩን አሳሳቢነትም አመልክቷል። ዶ/ር ሰለሞን እስካሁን ሲደረጉ የነበሩ ሳይንሳዊ ምርምሮች እና በእነሱ ላይ ተመስርተው የሚሰጡ ህክምናዎች ሙሉውን የሰው ዘር ያካተቱ አለመሆናቸው ለችግሩ አንድ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። 

“በዓለም ላይ የሚኖረው የሰው ዘር ምን ያህል ነው ውክልናው የሚለውን ያየን እንደሆነ ለምሳሌ የአፍሪካ አህጉር ከዓለም ህዝብ 14 ከመቶው የሚሆነውን የዘር እኩሌታ ይወክላል። Caucasian የምንለው የነጩ ዘር ደግሞ 16 ከመቶ የሚሆነውን የሰው ዘር የሚወክል ነው። ሌሎችም እንግዲህ የእስያ ሀገራት ምስራቅ እስያ የሚባሉት 27 ከመቶ የሚሆነውን የሰው ዘር ይወክላሉ። እንዲሁም ደግሞ ደቡብ እስያ የሚባለው 29 ከመቶ ይወክላል። እንግዲህ እነዚህ ሁለቱን ሀገራት ህንድና ቻይናን የሚወክሉ ናቸው። ሌሎችም እንግዲህ ላቲኖ፣ የአረብ ሀገራት እንዲሁም ደግሞ ኦሽኒያ የሚባሉት እንግዲህ የሰው ዘር የሚኖርባቸው አካባቢዎች አሉ። እነዚህ እንግዲህ በዓለም ላይ ምን ያህል ውክልና አላቸው? የሚለው ነው። 

ስለዚህ የዓለምን ህዝብ የዘረ መል አወቃቀር ስናጠና እንደዚሁ ውክልናቸውን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት አለበለዚያ የሚገኘው ውጤት ለሰው ልጅ በሙሉ ተግባር ላይ ሊውል አይችልም ማለት ነው። በዚህ ምክንያት ይሄ ልዩነት አለ። እስካሁን ግን የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት 96 ከመቶ የሚሆነው  ነጩ ዘር ላይ ሲሆን አራት ከመቶ የሚሆነው ደግሞ በምስራቅ እስያ ላይ ነው ማለት ነው። ስለዚህ በእነዚህ ሁለት አካባቢዎች ብቻ ነው ጥናቱ ያተኮረው። ይህ እስካሁን ያለው ሳይንሳዊ ግኝት የሰውን ዘር በሙሉ የሚወክል አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል” ሲሉ የአስተሳሰብ ለውጡን ይገልጻሉ። 

እንደ ዶ/ር ሰለሞን አባባል ከእንደዚህ አይነት ጥናት ተነስቶ የሚገኝ ሳይንሳዊ ግኝትም ሆነ የህክምና ውጤት ለሌላው የሰው ዘር ጥቅም ላይ ማዋል ያስቸግራል። ከፍትሃዊነት አንጻርም አፍሪካውያን እንዲሁም ሌሎች የሰው ዘሮች በእንደዚህ አይነት ጥናቶች መረሳታቸውን የሚናገሩት ባለሙያው ህመሞቹ ሁሉኑም የሰው ዘር የሚያጠቁ ሆኖ እያለ ትኩረቱ ግን በውስን አካባቢዎች ብቻ መሆኑ ትክክል እንዳያይደለ ስምምነት ላይ ተደርሷል ይላሉ። በዚህም ምክንያት ሁሉኑም የዓለም አካባቢዎች ያካተተ ምርምር መካሄድ አለበት ወደሚል ውሳኔ መመጣቱን ይገልጻሉ። ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረገው በዚህ ምርምር ልትካተት የቻለችው በዚህ አካሄድ እንደሆነ ያስረዳሉ። 

እንደዚህ አይነት ጥናት ለማካሄድ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እና ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ ነዉ። የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ በራሳቸው ይህን መሰል ምርምር ለማካሄድ አቅም እንደሌላቸው ዶ/ር ሰለሞን ያብራራሉ። አሁን የሚደረጉት ጥናቶች ቀደም ካሉት ምርምሮች በተለየ መልኩ የስኪዞፈርኒያ እና ባይፖላር ዲስኦርደር በሽታዎችን መንስኤ ማግኘት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ይናገራሉ። የአሁኑን ምርምር አካሄድ ከዚህ በፊት ከነበረው ጋር በማነጻጸር ደግሞ ተከታዩን ይላሉ።

Symbolbild Grundsatzurteil USA zur Patentierung menschlichen Erbguts
ምስል Fotolia/majcot

“እስካሁን እየሄድንበት ያለው አካሄድ፣ እየተሰጡ ያሉ መድኃኒቶች፣ እየተደረጉ ያሉ ምርምሮች በአንድ መስመር ብቻ የሚሄዱ ናቸው። እሱም ምልክቶችን በመቆጣጠር እና ታማሚው ህመሙ እንዳያገረሽበት መከላከል ላይ ያተኮሩ ናቸው። ይሄኛው መሰረታዊ የአቅጣጫ ለውጥ ያደረገ እና ከስር መንስኤውን ለይቶ ዘላቂ ፈውስ ሊያመጣ የሚችል አቅጣጫ ያሲዛል ተብሎ የሚጠበቅ ጥናት ነው።  ግን ሳምፕል የመሰብሰብ ሂደቱ ራሱ ከአራት እስከ አምስት ዓመት ይፈጃል ነው የምንለው። ከዚያ በኋላ ደግሞ ያ ተጠናክሮ በዘረ መል መዋቅር ውስጥ ያሉ በርካታ ግድፈቶች ይለዩና የትኞቹ ናቸው ዋናዎቹ የሚለው ከተለየ በኋላ እንግዲህ እነሱ በሳይንሱ druggable targets ይሏቸዋል ለመድኃኒት ወይም ደግሞ ዋና አጋላጭ የሆኑ፤ ከመድኃኒትም ደግሞ target የሚሆኑ ብለው ያስቀመጧቸውን ሲያገኙ ለእነሱ የተለየ መድኃኒት ይዘጋጃል ማለት ነው። እና እዚያ ላይ ማስተካከያ  ከተደረገ ፈውስ ያመጣል ተብሎ ነው የሚታመነው። መቼ ነው እዚህ ደረጃ ላይ የሚደረሰው የሚባለው በግልጽ መናገር አይቻልም” ይላሉ ዶ/ር ሰለሞን። 

ጥናቱ አስርም፣ ሃያም፣ ሃምሳ ዓመት ጭምር ሊፈጅ ይችላል የሚሉት ዶ/ር ሰለሞን አሁን ጥናቱ ያለበት ሁኔታ ወደዚያ የሚያስኬድ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያው ጥናት ተሳታፊ የሚሆኑ ስምንት ሺህ ሰዎችን ምልመላ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እንደሚያካሄዱ ይናገራሉ። ከእነዚህ ውስጥ ገሚሶቹ ህመምተኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ በማነጻጸሪያነት የሚያገለግሉ ጤናማ ሰዎች ይሆናሉ።

ጥናቱ የሚካሄደው የተሳታፊዎቹን የምራቅ ናሙና በመሰብሰብ እና የየሰውን ዘረ መል (ዲ ኤን ኤ) በማውጣት እንደሆነ ያስረዳሉ። ለዚህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ የሚገኝ ልዩ ላብራቶሪ ብቁ እንደሆነ ይገልጻሉ። በህመመተኞቹ እና በጤናማዎቹ መካከል ያለውን የዘር አወቃቀር ልዩነት ለመተንተን ግን በዘመኑ ቴክኖሎጂ በቅጡ ወደተደራጀው የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ቤተ ሙከራ ይላካል። ከህመምተኞች የተሰበሰቡት ችግር ያለባቸው የጂን መዋቅሮች ከተመዘገቡ በኋላ ጎልተው የሚወጡት እና ለህመሙ ቁልፍ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ የሚባሉት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ዶ/ር ሰለሞን ይናገራሉ። በእነዚህ ላይ ጥናት ተደርጎ ነው እንግዲህ በስተመጨረሻ ህክምና የሚዘጋጀው። 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ