1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ በርካቶች በጎርፍ ተፈናቀሉ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 19 2008

በኢትዮጵያ እየጣለ ባለዉ ከፍተኛ ዝናብ ወንዞች በመሙላታቸዉ በርካታ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸዉ መፈናቀላቸዉ ተዘገበ። «OCHA» እንዳስታወቀው ከ መጋቢት ወር ጀምሮ 600ሺህ ነዋሪ ተፈናቅሎአል የተፈናቀለዉ በጎርፍ ምክንያት ነዉ።

https://p.dw.com/p/1Jpi0
Somalia Hochwasser Flut 12.11.2013
ምስል picture alliance/AP Photo

[No title]

ኦቻ ተፈናቃዮችን ለመርዳት ከመንግሥት፤ ከአካባቢ ተጠሪዎች፤ ከተመ እና ከርዳታ አጋር ድርጅቶች ጋር እየሰራ እንደሆን ገልጾአል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ርዳታዎች ማስተባበሪያ ቢሮ «OCHA» ትናንት እንዳስታወቀዉ በኢትዮጵያ ካለፈዉ መጋቢት ወር ጀምሮ ከ 600 ሺህ በላይ ነዋሪ ከመኖርያ ቀየዉ ተፈናቅሎአል። አብዛኛዉ ነዋሪ ቤቱን መልቀቅ የተገደደዉ ጎርፍ ባስከተለዉ አደጋ ነዉ። በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ወንዞች የሚገኙት ለም በሆነዉ መሪት አካባቢ በመሆኑና በየዓመቱ በእነዚህ ወንዞች ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ በመከሰቱ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ይፈናቀላሉ፤ ይህ ደግሞ በአብዛኛዉ አዳጊ ሃገራት ዉስጥ የሚከሰት በመሆኑ የሚያስደንቅ ጉዳይ አይደለም ያሉት በኢትዮጵያ ተመ የሰብዓዊ ርዳታዎች ማስተባበሪያ ቢሮ ምክትል ተጠሪ ዴቪድ ዴል ኮንቴ፤ ቢሆንም በአደጋዉ የተፈናቀሉት ነዋሪዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነዉ።

Archivbild, Überschwemmungen in Afrika
ምስል AP

« በያዝነዉ ዓመት ግንቦት ሰኔና ሐምሌ ወንዞች በመሙላታቸዉና ከፍተኛ ጎርፍ በመከሰቱ በርካታ ነዋሪዎች በጊዜያዊነት መኖርያቸዉን ለቀዉ ሸሽተዋል፤ አብዛኞች ደግሞ ዘመዶቻቸዉ ጋር ነዉ የተተጠለሉት። ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ የታወቀ ቢሆንም የተፈናቃዮች ቁጥር በዚህ ዓመት መጨመሩ ያልተለመደ ሁኔታ ሆንዋል። ሁሉም ባይሆኑ ነዋሪዎች በጎርፉ ምክንያት ንብረታቸዉን አጥተዋል። በዚህ ዓመት 600ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸዉ በርግጥም እጅግ ብዙ ነዉ። ስለዚህም ከነዚህ 600 ተፈናቃዮች መካከል ርዳታ የሚያስፈልገዉ ማነዉ በሚለዉ ላይ ከክልላዊና አካባቢያዊ የመንግሥት ተጠሪዎች ከመንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከተመ አጋሮች ጋር እየሰራን ነዉ።»

Infografik Auswirkungen von El Ninho in Afrika

እንደ ድርጅቱ ተጨማሪ መግለጫ ከመጋቢት እስከ ሰኔ ጎርፍ ካፈናቀላቸዉ ወደ 300ሺህ ነዋሪዎች መካከል አብዛኞች ወደ መኖርያ የተመለሱ ሲሆን 10 ሺህ የሚሆኑት ግን አሁንም የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታን የሚሹ ናቸዉ። ከተፈናቃዮች መካከል በጎሳ ግጭት አካባብያቸዉን የለቀቁም ናቸዉ ሲሉ ዴቡድ ዴል ኮንቴ ተናግረዋል፤

« በምዕራብ ኦሮሚያና ሶማልያ አካባቢዎች ነዉ። በኢትዮጵያ ግጭት በሚታይባቸዉ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እንደሚታየዉ፤ ሰዎች ሰላም የማስፈን ጥረት አድርገዉ ይህ ሁኔታ በድጋሚ እንተፈናቃዮች ወደ መኖርያ ቀያቸዉ ደህንነታቸዉ ተጠብቆ እንዲመለሱ ይደረጋል። በዚህ ዓመት ግን በተለያዩ አካባቢዎች ትንሽና የተነጠሉ ግችቶች ታይተዋል። ማኅበረሰቡ የሚያስፈልገዉን ርዳታ ማድረግ ይኖርብናል፤ ይህ ሁኔታ ወደፊት እንዳይከሰትም ከመንግሥትና ከማኅበረሰቡ ጋር ለመስራትም በጥረት ላይ እንገኛለን።

በኢትዮጵያ በብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘዉዴ፤ ኦቻ ያወጣዉን መግለጫ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ፤

እንደ ኦቻ መግለጫ በከባዱ ዝናብ ምክንያት በሶማሌ ክልል በጎርፍ ለተጠቁ 85 ሺህ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ማቀበል አልተቻለም ። ላኒኛ የተባለዉና በየሁለት እስከ ሰባት ዓመት ባለው ጊዜ ድንገትና ያልተለመደ ቅዝቃዜ በሚያስከተለው የአየር ፀባይ ከተለመደዉ ብላይ ከፍተኛ ዝናብ በማስከተሉ፤ ቀደም ሲል በኤሊንዬ በተጠቁ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብ ሊከሰት ይችላል። በተለይ በኦሮምያና ሶማልያ ክልሎች ከሚቀጥለዉ ታህሳስ ወር ድረስ ተጽዕኖ ሊኖረዉ እንደሚችል «OCHA» አስታዉቋል።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ