1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ዓመታዊ ዘገባ በኢትዮጵያ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ይፋ አደረገ  

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 13 2010

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ የዘፈቀደ ግድያ እና ስቅየትን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አስታወቀ፡፡ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ይህን የገለጸው ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ 200 በሚጠጉ ሀገራት የነበረውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በገመገመበት እና ዛሬ ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ዘገባው ነው  

https://p.dw.com/p/2wROx
Symbolbild USA Außenministerium Logo Siegel
ምስል AP

ዘገባው በኢትዮጵያ ያሉ ዋንኛ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ሲል ከዘረዘራቸው ውስጥ በጸጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ የዘፈቀደ እስሮች እንደዚሁም ጭካኔ የተሞላባቸው፣ ኢ-ሰብዓዊ እና ክብረ-ነክ አያያዞች ይገኙበታል፡፡ በእስር ቤቶች ያለው ሁኔታም አስቸጋሪ እና ለህይወት አስጊ ነው ብሏል፡፡ የሚታሰሩ ሰዎች ፍትሃዊ ዳኝነት እንደማያገኙም አትቷል፡፡ በመናገር ነጻነት፣ በመገናኛ ብዙሃን እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ላይ ገደቦች ተጥለው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው በመሰብሰብ፣ በመደራጀት እና እንደ ልብ ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር ላይ ተመሳሳይ እቀባዎች መስተዋላቸውን ተንትኗል፡፡ 

የኢትዮጵያ መንግስት በጥቅሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙትን ባለስልጣናት ለመቅጣትም ሆነ ለፍርድ ለማቅረብ እርምጃዎችን አልወሰደም ሲልም ተችቷል፡፡ የተጠያቂነት አለመኖርን በችግርነት ያነሳው ዘገባው በዓመቱ ውስጥ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ለፍርድ የቀረቡ የጸጥታ ኃይሎች እና ባለስልጣናት ቁጥር በጣም ውስን መሆኑን በማሳያነት ጠቅሷል፡፡    

መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ ዓመታዊ ዘገባውን አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ “ሪፖርቱ ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ህዝቦች መሰረታዊ መብቶቻቸውን ለመጠቀም ብርቱ ተግዳሮቶች ገጥመዋቸው እንደነበር ያንጸባረቀ ነው” ብሏል፡፡ “የቀጣዩ ዓመት ግን ዘገባ ግን ከአሁኑ የተለየ ሊሆን እንደሚችል እምነት አለን” ሲል አክሏል፡፡ 

ኤምባሲው ተቃውሞውን በተደጋጋሚ የገለጸበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባይነሳም በዚህ ዓመት በሺህዎች የሚቆጠሩ እስረኞች መለቀቃቸውን እንደ አዎንታዊ እርምጃ ጠቅሶታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የማሻሻያዎችን አስፈላጊነት ጠንከር አድርገው በመልዕክቶቻቸው በግልጽ ማሳወቃቸው አበረታች ነው ብሎታል፡፡ እነዚህ ማሻሻያዎች የኢትዮጵያውያንን መብቶች የሚያረጋግጡ እንደዚሁም ሁሉን አካታች በሆነ የፖለቲካ አውድ እንዲሳተፉ የሚያስችሏቸው ይሆናሉ ብሎ እንደሚጠብቅም ገልጿል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫዎች ወደ ተግባር እንዲለወጡ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ኤምባሲው ጠቁሟል፡፡   

ተስፋለም ወልደየስ

እሸቴ በቀለ