1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢራን የጋዜጠኞች ፈተና

ዓርብ፣ ሚያዝያ 11 2005

ኢራን ዉስጥ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙሃን ላይ መንግስት የሚያደርገዉ ጫና መጠናከሩ እየተነገረ ነዉ። በድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ዘገባ መሠረት በጎርጎሮሳዊዉ 2009ዓ,ም ብቻ 30 የግል ጋዜጦች ኢራን ዉስጥ ታግደዋል።

https://p.dw.com/p/18Jf3
ምስል Loic Venance/AFP/GettyImages
Bildergalerie Iran KW 11
ምስል MEHR
Iran Grafik Inhaftierte iranische Journalisten

 በዚህ ዉጤትም ዛሬ ኢራን ዉስጥ ከሚገኘዉ ፕረስ ከ90 በመቶ የሚልቀዉ በመንግስት ቀጥተኛ ቁጥጥር ስር የሚንቀሳቀስ ነዉ። በቅርቡም ወደሁለት መቶ የሚሆኑ ጋዜጠኞች ከኢራን ተሰደዋል። በሀገሪቱ በመጪዉ ሰኔ ወር በሚካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ምክንያትም መንግስት ተቺ የሚባሉ ጋዜጠኞችና የድረገፅ ጸሀፊዎች ላይ ቁጥጥርና ቅድመ ምርመራዉን ማጠናከሩ እየታየ ነዉ።

ወህኒ በወረደ ምሽት ኤህሳን ማህራቢ ምሽቱ በዋዛ የሚነጋለት አልነበረም። ከቆመበት እንዲቀመጥ አልተፈቀደለትም። መቆሙ ሲበዛበት ብዥ አለበት፤ ሲቆይ ደግሞ ጭራሹን አዞረዉና ራሱን መቆጣጠር አቃተዉ። ወደቀ ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ደረሰበት ግን አሁንም እንዲቆም ተገደደ እንጂ ሸብረክ ብሎ እንኳ ህመሙን እንዲያዳምጥ አልተፈቀደለትም። የከፋዉ ይባስበት እንዲሉ ኢራናዊዉ ጋዜጠኛ ይበልጥ ስነልቦናዬም እንዲታወክ ቤተቦቼንም ጭምር እንደሚያስሩ እኔንም እንደሚገድሉኝ ያስፈራሩኝ ነበር ይላል።
በአንድ ምሽት ሰላይ ሆነ። የስለላ ተቋም ወኪሎች የ37ዓመቱን ጋዜጠኛ ጎረቤቶችና ጓደኞች መኖሪያ ቤት በማንኳኳት ማህራቢ ከዉጭ መንግስታት ጋ ይሠራል ሲሉ ተናገሩ። ምክንያቱም የፓርላማ ጉዳይ ዘጋቢዉ ለብሪታኒያዉ BBC ራዲዮ ፐርሺያ አገልግሎት በጎርጎሮሳዊዉ 2010ዓ,ም ቃለመጠይቅ መስጠቱ ነዉ። «ይህም እኔን ለአንድ አመት ከሶስት ወር ወደወህኒ ለመወርወር በቂ ምክንያት ነበር።»
ኢራን ዉስጥ አንድ ጋዜጠኛ እንዲታሰርም ሆነ ሰቆቃ እንዲፈፀምበት እጅግም ትልቅ ነገር የሚያስፈልግ አይመስልም። ስለኒኩሊየር መርሃግብሩ አንድ ዘገባ፤ ሀገሪቱ ዉስጥ ስለማያባራዉ የዋጋ ግሽበት አለያም ምዕራባዉያን የጣሉትን ማዕቀብ ስለማጥበቃቸዉ መፃፍ በቂ ነዉ። አንዳንዴም ስለእስላማዊዉ አብዮት ክብረበዓል ወይም መንግስትን የደገፉ ሰላማዊ ሰልፎችም መዘገብ መዘዝ ይኖረዋል። ጋዜጠኞች የማይታዩትን ቀይ መስመሮች ላለመጣስ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። «መንግስት ቅድመ ምርመራ ሲል ምንማለቱ እንደሆነ ግልፅ ያደረገበት ሁኔታ የለም።» ይላሉ በኢራን የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ቃል አቀባይ ራዛ ሞይኒ። የጋዜጠኞች መብት ተከላይ ኮሚቴ CPJ በበኩሉ የኢራን ፕረስ ከዓለም ከፍተኛ ቅድመ ምርመራ እንደሚካሄድበት ያመለክታል። ዋና አዘጋጆቹ  ከኢራን ባህል ሚኒስቴር እንዲሁም ከእስላማዊ መሪዎች ትዕዛዝ ይተላለፍላቸዋል። መመሪያዉን እንዴት በስርዓት መከተል እንደሚኖርባቸዉም ያዉቁታል። «አንድ ጋዜጣ ስለአንድ የተቃዉሞ ፖለቲካ መሪ በመዘገቡ ምክንያት በቅርቡ ተዘግቷል።» ይላል ከታገደዉ የኢራን ጋዜጠኞች ኅብረት አሊ ማዝሮይ። ማዝሮይ ለበርካታ ዓመታት ከተለያዩ ጋዜጠኞች ጋ ሰርቷል። እሱ እንደሚለዉም ሁልጊዜም ትችት የሚሰነዝሩ ጋዜጦችና ራዲዮዎች ኢራን ዉስጥ እድሜ የላቸዉም። ይታገዳሉ፤ ይዘጋሉ።

በድንበር የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ዘገባ መሠረት በጎርጎሮሳዊዉ 2009ዓ,ም ብቻ 30 የግል ጋዜጦች ኢራን ዉስጥ ታግደዋል። በዚህ ዉጤትም ዛሬ ኢራን ዉስጥ ከሚገኘዉ ፕረስ ከ90 በመቶ የሚልቀዉ በመንግስት ቀጥተኛ ቁጥጥር ስር የሚንቀሳቀስ ነዉ፤ ስለዚህም ማዝሮይ ዛሬ ብራስል ዉስጥ የስደት ኑሮዉን ይገፋል።
በቅርቡም ወደሁለት መቶ የሚሆኑ ጋዜጠኞች ከኢራን ተሰደዋል። በሀገሪቱ በመጪዉ ሰኔ ወር በሚካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ምክንያትም መንግስት ተቺ የሚባሉ ጋዜጠኞችና የድረገፅ ጸሀፊዎች ላይ ቁጥጥርና ቅድመ ምርመራዉን ማጠናከሩ እየታየ ነዉ። ከጥር ወር መባቻ አንስቶም ወደ24 የሚደርሱ ጋዜጠኞች ታስረዋል፤ ገሚሱ ተለቀዋል የተቀሩት አሁንም ታስረዋል። 46 ጋዜጠኞችና የድረገፅ ፀሀፊዎች ደግሞ ለዓመታት በእስር ላይ ይገኛሉ። በዚያ ላይ ጋዜጠኞች ዋና ከተማ ቴህራንን እንዲለቁ ግፊት ይደረግባቸዋል። ለጋዜጠኞች የሚሟገተዉ ድንበር የለሽ ተቋም የሀገር ዉስጥ ስደት ይለዋል። በዉጭ ሀገር የሚሠሩ ኢራናዉያን ጋዜጠኞች እንደሚጎበኙና ማስፈራሪያም እንደሚደርሳቸዉ ይገልፃሉ። ራሳቸዉን ለመደበቅ ቢሞክሩም ኤምባሲ ስለሚያዉቃቸዉል ለዉጥ እንደማይኖር ያስረዳል ጀርመን የሚገኘዉ ወጣት ኢራናዊ ጋዜጠኛ።
«መንግስት በምርጫዉ ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ እየሞከረ ነዉ።» ይላል ማዝሮይ። የኢራን አገዛዝ የዛሬ አራት ዓመት ከተካሄደዉ ምርጫ ማግስት የተከሰተዉ ዓይነት አመፅ በሀገሪቱ ይነሳል የሚል ስጋት አለዉ። በወቅቱ የተቃዉሞ ሰልፈኞቹ በጭካኔ ተደብድበዋል። ዶቼ ቬለ በርሊን ከሚገኘዉ የኢራን ኤምባሲ አስተያየት በዚህ ላይ ጠይቆ ምላሽ አላገኘም።

Symbolbild Pressefreiheit
ምስል picture-alliance/dpa

ከዚህ የምርጫ ጊዜ አንስቶ ሥራዉ እየከበረ መሄዱንና፤ መንግስት የኢንተርኔቱን መረብ የሚሰልል ሰራዊቱ አሰማርቷል ይላል ማዝሮይ። ተግባሩም የኢሜልና የስካይፕ እንዲሁም የስልክ ግንኙነቶችን መቆጣጠር ነዉ። ማህራቢ በበኩሉ «ምርመራ በሚያካሂዱበት ወቅት የተለዋወጥኳቸዉን ኢሜሎች አቅርበዉልኛል።» ይላል። ከሰላዮቹ ለመሸሽ ሲባል የምስጢር መግባቢያዎችን ለተቃዉሞ ፖለቲከኞች መስጠት፤ ቃለመጠይቅን በስልክ ከማድረግ መቆጠብ እና የመሳሰሉትን ርምጃዎች ጋዜጠኞች ቢወስዱም አንዳንዴ ጥንቃቄዉ ይሰራል አንዳንዴም አይሳካም ይላል ጋዜጠኛዉ። ከባለቤቱ ጋ በስደት በርሊን ዉስጥ ህይወቱን ሲገፋ ሁለት ወራት አስቆጥሯል። ምንም እንኳን እስር ቤት ዉስጥ የሰቆቃ ጊዜ ቢያስልፍ እና ለቤተሰቦቹ ህይወት ስጋት ቢገባዉም፤ እዚያ በቆየበት ወቅት ለ20ዓመታት ያህል እስር ላይ የሚገኙ ወገኖቹን ለማግኘት መቻሉን ከእድል ቆጥሮታል። «ታሪካቸዉን ማንም አያዉቅም፤ እነሱንም ማንም አያዉቃቸዉም» እሱ ከእስር ነፃ ከወጣ በኋላ የእነሱን ታሪክ መግለፅ ችሏል። አደጋ ቢኖርም።

ናኦሚ ኮንራድ

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ