1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢራቅ የነዳጅ ዘይት ላይ የሚደርሰው ጥቃት

sdestaረቡዕ፣ ነሐሴ 26 1996

በኢራቅ የሽምቅ ተዋጊዎች በነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያ ቧንቧ ላይ የሚፈፀመው ጥቃት ተደጋጋሚ ተግባር ሆኗል ። ባሳለፍነው የሳምንት መጨረሻም በደቡባዊው ክፍል በሚገኝ የነዳጅ ማከማቻ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ነበር ። ድርጊቱ በአሁኑ ወቅት ለኢራቅ ብቸኛ የገቢ ምንጭ የሆነውን የነዳጅ ገበያ የሚያስተጓጉል ነው ።

https://p.dw.com/p/E0fP

በኢራቅ በነዳጅ ዘይት ማከማቻ እና ማስተላለፊያ ቧንቧ ላይ ጥቃት መፈፀም እንደ ኢራቃውያን ሞት እንደውጭ ዜጎች መታገት ተደጋጋሚ ተግባር ሆኗል ። ቁጥሩ በትክክል ተለይቶ ባይታወቅም ዩናይትድስቴትስ መራሹ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ መቶ ያህል ጥቃቶች በነዳጅ ዘይት ሃብት ላይ ተፈፅሟል ። የነዳጅ ዘይት መስሪያ ቤቶች እና ነዳጅ ጫኝ መኪናዎች የጥቃቱ ዒላማዎች ነበሩ ። ናቸውም ። የሚታለመው እና የሚቀነባበረው ጥቃት ዩናይትድስቴትስን እስከ ደጋፊዎቻ እና የኢራቅ ባለስልጣናትን ዒላማ ቢያደርግም የሃገሪቱን ብቸኛ ገቢ እየጎደ ነው ። ከህዝቡ ሃምሳ በመቶው ሥራ አጥ እንደሆነ ፤ ሃገሪቱም በአንድ መቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ዕዳ ውስጥ እንደተዘፈቀች የመቆየት ዕድሏን የሚያጠናክር ነው ።

አምና የዩናይትድስቴትስ ጦር የኢራቅን በወረረበት የመጀመሪያዎቹ ጊዚያት የሳዳም ሁሴን መንግስት የሰባት የነዳጅ ጉድጓዶችን ሥራ በማስተጓጎል እና እሳት በመለኮስ የወራሪውን ጦር ዒላማ ለማሰናከል ጥሮ ነበር ። ይህን ደግሞ የዩናይትድስቴትስ ባለስልጣናት አስቀድመው ጠብቀውታል ። እንደውም በጊዜው የደረሰው ጉዳት ከሚገመቱት ያነሰ ነበር ። የተዘጋጁበት ይህን ጥቃት ለመከላከል አስቀድሞ የተነደፉ ስልቶች ቢኖሩም ጥቃቱን ለማስቆም አልተቻላቸውም ። ሰባት ሺ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያ ቧንቧን ለማስጠበቅ አሁንም ጥረት ያደርጋል ። በባስራ ፣ በባግዳድ እና ከባግዳድ ሰሜናዊ ምስራቅ በምትገኘው በባዶጂ የሚገኙትን ሶስት ዋና የነዳጅ ጉድጓዶችን አያያዝ ለማሻሻል እድሳቶች ተደርገዋል ። ከነዚህ የነዳጅ ጉድጓዶች የሚገኘው ምርት የሃገር ውስጥ ፍጆታን እየሸፈነ መሆኑን ባለስልጣናት ይናገራሉ ።

አብዛኛው የኢራቅ የነዳጅ ሃብት የሚገኘው በደቡባዊ ክፍለ ነው በተለይም ከባግዳድ ሰሜናዊ ክፍል የምትገኘው የኪርኩክ ከተማ ሶስት እጁን የነዳጅ ሃብት በመያዝ ትታወቃለች ። ሆኖም ከኪርኩክ ወደ ቱርክ የሚሸጋገረው የነዳጅ ዘይት ቧንቧ በየጊዜው የደፈጣ ተዋጊዎች እና አሻጥር ፈጻሚዎች ጥቃት ሲደርስበት አብዛኛውንም ጊዜ ሥራው ቆሟል ። የነዳጅ ቧንቧው የሚያልፈው ደግሞ የሳዳም ሁሴን ደጋፊዎች የሱኒ ጎሳ አባላት ተጠናክረው በሚገኙበት ነው ። ሁለተኛው የኢራቅ ከተማ የባስራ የነዳጅ ቧንቧዎችም የደፈጣ ተዋጊዎቹ ጥቃት ሰለባዎች ናቸው ። እስከአለፈው ሰኔ ድረስ የኢራቅ የነዳጅ ሚኒስትር ሆነው የቆዩት ኢብራሂም ባህሩል ኡሉም እንዳሉት በኪርኩክ እና በባስራ ከአስር እስከ አስራ አንድ የሚደርሱት ጥቃቶች የተፈፀሙት ፀረ መንግስት አቋም ባላቸው የሱኒ ጎሳ አባላት ነው ። የጠቅላይ ሚኒስትር ኢያድ አላዊ መንግስት ከዚህ ጎሳ ጋር የሰላም ድርድር ሙከራዎች ማድረጉንም ኡሉም ገልፀዋል ። እንደሳቸው እምነት ከጎሳ አባላቱ ጋር መደራደር ይቻላል ፤ ሆኖም ዋናው መፍትሄ የሃገሪቱን ፀጥታ ማስከበር ነው ። ኡሉም በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት እንደሚያውቁት የነዳጅ ቧንቧዎች እና ማምረቻዎችን ለማስጠበቅ አስራ አራት ሺ ጠንካራ የፀጥታ አስጠባቂ ሃይል ተሰማርቷል ። ይህንኑ የፀጥታ አስከባሪ ሃይል በእጥፍ ለማሳደግም እቅድ ነበር ።

ኢራቅ አንድ ሺ አምስት መቶ የነዳጅ ማከማቻ ጉድጓዶች እንዳሏት ይገመታል ። እነዚህን ሁሉ የነዳጅ ጉድጓዶች ማስጠበቅ በርግጥ አይቻልም ። መንግስት የፀጥታ ጥበቃውን ከማስከበሩ ጎን የነዳጅ ማከማቻ ጉድጓድ ፣ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ እና የሌሎች ግንባታዎች ጥገና ለማድረግ እቅድ አለው ። የነዳጅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዘንድሮው የአውሮጳውያን ዓመት ከሰባት መቶ እስከ ስምንት መቶ ሚሊዮን ዶላር በጀት አስፈልጎት ነበር ። ሆኖም የጥምሩ ጊዚያዊ መንግስት እስከ አለፈው ሰኔ ድረስ ገቢ ያስገኘው ከገመተው ከግማሽ በታች ነው ። በሌላ በኩል የኢራቅ ባለስልጣናት የነዳጅ ኢንዱስትሪውን ምዋለ ንዋይ ለማስፋፋት ከተለያዩ የነዳጅ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል ። በርግጥ በዘርፉ የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ እየጨመረ ነው ። ምንም እንኳን ከፍተኛ ፍላጎት በኢራቅ ፤ ከኢራቅም በነዳጇ ላይ ቢያሳድሩም ይፈራሉ ። የሃገሪቱ የፀጥታ አስተማማኝነት ስጋታቸውን ያበረታዋል ። የፀጥታ እና የደህንነት ዋስትና ኢራቅን ርቋታል እና ።