በቴይለር ላይ የተላለፈው ብይን
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 18 2004ዘሄግ ኔዘርላንድስ የተሰየመው የሴራልዮን ልዩ ፍርድ ቤት በቀድሞው የላይቤሪያ መሬ ቻርልስ ቴይለር ላይ ዛሬ የጥፋተኝነት ብይን አሳልፏል ። ፍርድ ቤቱ ቴይለር በተመሠረቱባቸው 11 የወንጀል ክሶች ጥፋተኛ መሆናቸውን አሰታወቋል ። ቴይለር በ 1990ዎቹ ሴራልዮን ውስጥ ይንቀሳቀስ ከነበረው የተባበሩት አብዮታዊ ግንባር ጋር በመመሳጠርና በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የሴራልዮን መንግሥት እንዲወጋ በመርዳት ነበር የተከሰሱት ። ተከታዩ የአንድሪ ሌስሊ ዘገባ የቻርልስ ቴይለርን የፍርድ ሂደት ይቃኛል ።
«ተካሳሹ፣ በተረጋገጠ ሁኔታ 11 የወንጀል ዓይነቶችን የሚመለከቱ ክሶች ናቸው የቀረቡባቸው። 5 ቱ በሰብአዊነት ላይ ወንጀል መፈጸማቸውን ነው የሚያወሱት። ይህ ደግሞ ፍርድ ቤቱ በተቋቋመበት ደንብ ፣ አንቀጽ 2 ፤ የሚያስቀጣ ነው። በተለይ ግድያ (በ 2 የክስ ሰነዶች ተወስቷል) አስገድዶ መድፈር (በ 4 የክስ ሰነዶች ተጠቅሷል) የወሲብ ባሪያ ማድረግ የሚለው (5 የክስ ሰነዶች)፤ ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶች (8 የክስ ሰነዶች) ባሪያ ማድረግ ፣ (10 የክስ ሰነዶችን )የያዘ ነው።»
የቀድሞው የላይቤሪያ መሬ ቻርልስ ቴይለር ጥፋተኝ የተባሉባቸውን ወንጀሎች የዘረዘሩት የሄጉ ፍርድ ቤት መሃል ዳኛ ሪቻርድ ሉስያክ እንደዘረዘሩት ። በቴይለር ላይ የጥፋተኝነት ብይን የተሰጠባቸው እነዚህ ወንጀሎች እጎአ ከህዳር 1991 እስከ ጥር 2002 ዓም በተካሄደው የሴራልዮን የርስ በርስ ጦርነት ወቅት የተፈፀሙ ናቸው ። በወቅቱ አማፅያን በሴራልዮን ህዝብ ላይ እጆችና ጣቶችን መቁረጥ ጨምሮ እጅግ ዘግናኝ ወንጀሎች ፈፅመዋል ። ቴይለር በጎረቤት ሴራልዮን እጎአ ከ1991 እስከ 2001 በተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት የሴራልዮኑን አማፂ ቡድን የተባበሩት አብዮታዊ ግንባርን በማስታጠቅ በማሰልጠንና በቁጥጥራቸው ሥር በማድረግ በምትኩ ደግሞ አልማዝ በመውሰድ ነወ የተወነጀሉት ። የቀድሞው አማፂ ቻርልስ ቴይለር እጎአ በ 1997 ነበር ተመርጠው ሥልጣን የያዙት ። በ2 ዓመቱ የላይቤሪያው የርስ በርስ ጦርነት ተቀሰቀሰ ። ቴይለር በ 2003 ወደ ናይጀሪያ ሲኮበልሉ የርስ በረሱ ጦርነተ አከተመ ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ናይጀሪያ ተሰውረው የቆዩት ቴይለር በ2006 ለሴራልዮን ተላልፈው ተሰጡ ። ሆኖም እዚያ መቆየታቸው
አካባቢው እንዳይረጋጋ ያደርጋል ከሚል ፍራቻ ከፍሪታውን ሴራልዮን ወደ ሄግ እንዲዛወሩ ከተደረገ በኋላ የፍርዱ ሂደት ሰኔ 2007 ተጀመረ ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፍርድ ቤት ተጠርተው ቀርበዋል ። Open Society Justice Initiative የተባለው የሰብዓዊ መብት ድርጅት ባልደረባ ሴራልዮናዊ ጠበቃ አልፋ ሴሳይ የፍርዱን ሂደት ታዝበዋል ።
« ምንም እንኳን አቃቤ ህግ አንዳንድ ሰነዶችን በመረጃነት ቢወስድም ውስጥ አዋቂዎች የሰጡትን ምስክርነት ነው በዋነኛነት የተጠቀመው ። ይኽውም የቀድሞውን ምክትል ፕሬዝዳንት ጨምሮ በቴይለር የደህንነት ባለሥልጣን ውስጥ ያገለገሉ ሰዎች ናቸው የመሰከሩባቸው ። »
የፍርዱ ሂደት በተለይ ታዋቂዋ ሞዴል እንግሊዛዊቷ ናኦሚ ካምፕ ቤል በምስክርነት ከቀረበች በኋላ ዐብይ ዜና ሆነ ። ፍርድ ቤቱ ናኦሚን ለምስክርነት የጠራው ያረፈችበት ሆቴል ክፍል ድረስ ከቻርልስ ቴይለር የተበረከቱ አልማዞች ተልኮላታል በመባሉ ነበር ። 3 ቱ ዳኞች የቀረቡትን መረጃዎች ተጨማሪ ጊዜ ወስደው ለማጣራት ና ውሳኔያቸውንም በፅሁፍ ለማቅረብ የፍርዱን ሂደት የዛሪ ዓመት በመጋቢት ወር ለጊዜው አቋረጡት ። ብይን ይጠበቅ የነበረው በታህሳስ አጋማሽ ላይ ቢሆንም ለዚህ ዓመት ለሚያዚያ ተቀጠረ ። ሲሴይ እንደሚሉት በሴራልዮን አማፅያን የተፈፀሙትን ወንጀሎች ማረጋገጡ አያስቸግርም የአቃቤ ህግ ዋነኛው ተግባር ግን እነዚህን ወንጀሎች ከቴይለር ጋራ ማገናኘት ነበር ።
« ሴራልዮን ሄደው አያውቁም ። አንዳንድ አዛዦቻቸው እና የሴራልዮን አማፅያንም ወደ ላይቤሪያ መጓዛቸውና አምፅያኑም ወደ ሴራልዮን መመለሳቸውና እነዚህን ዘመቻዎች ማካሄዳቸው ነው መረጃው ። »
አልፋ ሲሴይ አሁንም ቢሆን የፍርዱ ሂደት ለወደፊት ዓለም ዓቀፍ የወንጀለኞች ጉዳዮች ብርሃን ፈንጣቂ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው ።
« በጣም ተዓማኒ የፍርድ ሂደት ነበር ። ምሳሌም ሆኗል ። ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች በኮሚሽኑ በወንጀል ከተከሰሱ ፣ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ያሳያል ። »
ፍርድ ቤቱ በቴይለር ላይ የመጨረሻውን ቅጣት የሚያስተላልፈው ግንቦት 22 ፣ 2004 ዓም ነው ።
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ