1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቱርኩ ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ጀርመናዉያን ተገድለዋል

ማክሰኞ፣ ጥር 3 2008

ቱርክ ኢስታንቡል የአገር ጎብኝዎች በሚያዘወትሩበት ቦታ በደረሰ ፍንዳታ 10 ሰዎች ተገደሉ 15 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸዉ። ከሟቾቹ መካከል ቢያንስ ዘጠኙ ጀርመናዉያን መሆናቸዉን የቱርክ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህሜት ዳቩቱግሉ ለጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/1Hc5V
Türkei Explosion in Istanbul
ምስል Reuters/K. Aslan

ይህ ዜና ይፋ ከመዉጣቱ ቀደም ሲል የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልም ሆኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር በጥቃቱ የተጎዱ ጀርመናዉያን መኖራቸዉን ግን የሞተ እንደማይኖር ገልፀዉ ነበር። ፕሬዚዳንት ሪቺብ ታይብ ኤርዶጋን፤ አጥፍጦ ጠፊ ጥቃቱን ያደረሰዉ ግለሰብ የ 28 ዓመት ሶርያዊ መሆኑን ተናግረዋል። በጥቃቱ ከሞቱት መካከል ቱርካዉያንና የዉጭ አገር ዜጎች እንደሚገኙበት ሲነገር ነበር ያረፈደዉ። ኖርዌ አንድ ዜጋዋ በኢስታንቡሉ ጥቃት መጎዳቱን ያስታወቀች የመጀመርያዋ አገር መሆኗም ተዘግቦ ነበር። የሕክምና ባለሞያዎች ከተጎጂዎቹ መካከል ጀርመናዉያንና አንድ የፔሩ ዜጋ እንደሚገኝበት መግለፃቸዉም ተመልክቶአል።
ጥቃቱ እንደደረሰ የቱርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አህሜት ዳቩቱግሉ የሀገር አስተዳድረ ሚኒስትሩንና የሀገሪቱን የፀጥታ ጥበቃ ዋና ተጠሪ ለአስቸኳይ ዝግ ስብሰባ መጥራታቸዉ ተዘግቦአል። አስቸኳይ ስብሰባዉ ለማንኛዉም ሚዲያ ዝግ መሆኑን የቱርክ ባለሥልጣን መስርያ ቤት አስታዉቋል። አንድ ቦታዉ ላይ የነበሩ የዓይን እማኝ እንደገለፁት

አጥፍቶ ጠፊ የጣለዉ ቦንብ ነዉ ። ጥቃቱ የደረሰበት ቦታ አይቼ ወደ ሆቴሌ ተመልሻለሁ። የጥቃቱ ቦታ እጅግ ምስቅልቅል የበዛበት ነበር። አሁን ፖሊስ አደባባዩን በሙሉ በሙሉ አጥሮ ምንም አይነት ዝዉዉር የለም።
አጥፍቶ ጠፊ ራሱን ያነጎደዉ በኢስታንቡል በቀድሞ ጊዜ በተቆረቆረዉ ሱልታን አህሜት በሚባለዉ የከተማ ክፍል በሚገኘዉ በታዋቂዉ ሰማያዊ መስጊድ ፊት ለፊት እንደሆነ ተገልጾአል። የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ኢስታንቡል ተጓዥዎችም ሆነ ወደሌሎች የቱርክ ከተሞች የሚጓዙ ጀርመናዉያን ሰዉ በብዛት ከተሰበሰበት ቦታ እንዲሁም የአገር ጎብኝዎች ከሚጎበኙት ቦታ ከመገኘት እንዲቆጠቡ ሲል አሳስቦአል።

Türkei Anschlag in Istanbul Aufnahme eines Touristen
ምስል imago/ZUMA Press


አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ