1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ታሪካዊ ቦታ ለኢንቨስትመንት መሰጠቱ ተቃውሞ ቀሰቀሰ

እሑድ፣ መጋቢት 8 2011

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቡለን ወረዳ ታሪካዊ ቦታ ለኢንቨስትመንት በመሰጠቱ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ። በቡለን ወረዳ የሚገኘው ዳሐን ዋሻ በማዕድን ፍለጋ ለተሰማራው ቢ አይካ የተባለ ኩባንያ ተሰጥቶ ነበር። ያገር ሽማግሌዎች ያቀረቡትን ቅሬታ መቀበሉን ያረጋገጠው የክልሉ መንግሥት "ባለሐብቱ ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጠው ዝግጅት ላይ ነን" ብሏል።

https://p.dw.com/p/3FDe5
Asosa, West-Äthiopien und Hauptstadt der Region Benishangul-Gumuz
ምስል privat

ወጣቶች ለባለሐብት የተሰጠው ቦታ ታሪካዊ እና ሊጠበቅ የሚገባው ነው ይላሉ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቡለን ወረዳ ታሪካዊ ቦታ ለኢንቨስትመንት በመሰጠቱ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ። በቡለን ወረዳ የሚገኘው ዳሐን ዋሻ በማዕድን ፍለጋ ለተሰማራው ቢ አይካ የተባለ ኩባንያ ተሰጥቶ ነበር። በአካባቢው ታሪካዊ አልባሳት እና የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች እንደሚገኙበት የሚናገሩ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ቦታው ታሪካዊ በመሆኑ እና "የቅድመ-አያቶቻችን መቃብር ስለሚገኝበት" ውሳኔው ትክክል አይደለም ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

"በሺናሻ ባሕል እርቀ-ሰላም የሚፈጸምበት ቦታ" የሚሉት ነዋሪው "መሰጠቱ ተገቢ አይደለም። ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አልተደረገም" ሲሉ ይወቅሳሉ።

ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ለግል ኩባንያ የተሰጠው ዳሐን ዋሻ አካባቢ "የሺናሻ ማኅበረሰብ ከአስራ አንድ ትውልድ በላይ እዚያው ኖሮ እዚያው ሞቶ እዚያው የተቀበረበት የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው የሺናሻ ማንነት የሚገለፅበት ቦታ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። "ወጣቱ ይቃወማል፤ ያገር ሽማግሌዎቹም ይቃወማሉ" የሚሉት የቡለን ወረዳ ነዋሪ "የእኛን ታሪክ ወደ ጎን በመተው የኢንቨስትመንት ሥራውን ማስቀጠል አንችልም" ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ሐብት ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ይሱፍ አልበሽር ቦታው ታሪካዊ ስለመሆኑ መረጃ እንዳልነበር ተናግረዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ያገር ሽማግሌዎች ያቀረቡትን ቅሬታ መቀበላቸውን ያረጋገጡት ኃላፊው "ባለሐብቱ ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጠው ዝግጅት ላይ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

ነጋሳ ደሳለኝ

እሸቴ በቀለ