1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቤተ ሰማእቲ  በቁፋሮ የተገኘው ጥንታዊ ከተማ

እሑድ፣ ታኅሣሥ 26 2012

ከዓድዋ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ልዩ ስሙ መዝብር ወይ ቤተ ሰማእቲ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት 771 እስከ 612 ዓ.ም ሕዝብ ይኖርበት የነበረ ተብሎ የሚታመን ጥንታዊ ከተማ በኢትዮጵያውያንና አሜሪካውያን የአርኪዮሎጂ ባለሞያዎች መገኘቱ ይፋ ተደርጓል፡፡ 

https://p.dw.com/p/3VYwC
Äthiopien Alte Stadt entdeckt in Bete Semaiti
ምስል DW/M. Hailesilassie

ኢትዮጵያውያንና አሜሪካውያን የቅሪተ-አካል (አርኪዮሎጂ) ባለሞያዎች ለአራት ተከታታይ ዓመታት ካደረጉት ጥናት በኋላ በትግራይ ክልል አሕፈሮም ወረዳ ጥንታዊ ከተማና ቤተ ክርስትያን ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ልዩ ቦታው «ቤተ ሰማእቲ» ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ የተገኘው ይህ ጥንታዊ ከተማ ከክርስቶስ ልደት በፊት 771 እስከ 612 ዓ.ም ህዝብ ይኖርበት ነበረ ተብሎ ይታመናል፡፡ በውስጡም 1700 ያደረገ ቤተ ክርስትያን በቁፋሮ መገኘቱም ተገልፅዋል፡፡ 

ጥንታዊ ከተማና ቤተ እምነቱ በሚገኝበት አካባቢ ተገኝተን እንደተመለከትነው ተቆፍሮ ወጥቶ የነበረው ጥንታዊ ከተማና ቤተ ክርስትያን ዳግም ተቀብሯል፡፡

ብዙዎች ከሚያውቁት ጥንታዊው የአክሱም ስልጣኔ ውጪ ሌሎች የአካባቢው ወይ የከተማ ስልጡን ግዛቶች በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እንደነበሩ የሚያሳዩ ቅሪቶች በየወቅቱ እንደሚገኙ የአርኪዮሎጂ ባለሞያዎች ይገልፃሉ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በትግራይ ክልል ሽረ እንዳስላሰ ከተማ አካባቢ ማይ አድራሻ በተባለ ስፍራ ጥንታዊ ከተማ መገኘቱ አንደ ማሳያ ተደርጎ በባለሞያዎች ይቀርባል፡፡ በቅርቡም በተመሳሳይ ከዓድዋ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ልዩ ስሙ መዝብር ወይ ቤተ ሰማእቲ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት 771 እስከ 612 ዓ.ም ሕዝብ ይኖርበት የነበረ ተብሎ የሚታመን ጥንታዊ ከተማ በኢትዮጵያውያንና አሜሪካውያን የአርኪዮሎጂ ባለሞያዎች መገኘቱ ይፋ ተደርጓል፡፡ 

ቤተ ሰማእቲ ጥንታዊ ከተማን ለማግኘት ለተከታታይ አራት ዓመታት የዘለቀ ጥናት መደረጉ የተገለፀ ሲሆን በሁለት የምርምር ሳይቶች ጥንታዊ ከተማና 1700 ዓመት ያለፈው የክርስትያኖች የአምልኮ ስፍራ መገኘቱ ተነግሯል፡፡ ተማራማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ቤተ ሰማእቲ አካባቢ ቁፋሮ በሚደረግበት ወቅት በጥንታዊ ከተማው ውስጥ የተለያዩ የመቃብር ስፍራዎች፣ ረዣዥም በድንጋይ የተሰሩ አጥር መሰል ህንፃዎች፣ በርካታ የሸክላ ስራዎች፣ ከወርቅና ብር የተሰሩ ጌጣጌጦች እንተገኙ ይገልፃሉ፡፡ 

በቁፋሮው የተገኙ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች በአክሱም በሚገኝ ቤተ-መዝከር (ሙዝየምና) ሌሎች ቦታዎች የተቀመጡ ቢሆንም ቋሚ ቅርሶቹ ቤተ ሰማእቲ ጥንታዊ ከተማና ቤተ እምነቱ ግን ዳግም መቀበራቸው በቦታው ተገኝተን ተመልክተናል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ጥንታዊው ከተማ የተገኘበት ቦታ የአርሶአደሮች ማሳ ሲሆን ገበሬዎች ከተቀበረው ጥንታዊ ከተማ ላይ ያርሳሉ፡፡ የአካባቢው መስተዳድርም ጥንታዊ ከተማና ቤተ ክርስትያን ተቀብሮ በሚገኝበት ስፍራ ላይ ቅርሱን በሚጎዳ ሁኔታ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት አስገንብቶ ተመልክተናል፡፡

በቁፋሮው የተሳተፉ የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የአርኪዮሎጂ ባለሞያ አቶ ግደይ ገብረእግዚአብሔር እንደሚሉት ቋሚ ቅርሱ ዳግም የተቀበረው ቦታው በአሁኑ ወቅት የአርሶአደሮች ማሳ በመሆኑ ካሳ ተከፍሎ እስኪነሱና ቅርሱ ጉዳት እንዳይደርስበት ታስቦ መሆኑ ነግረውናል፡፡

የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቤተ ሰማእቲ ጥንታዊ ከተማ ጥናት ሙሉ በሙሉ በሚጠናቀቅበት ወቅት አካባቢው ለማልማት እቅድ እንዳለው ይገልፃል፡፡ 

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ