1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8 ተከሳሾች በነጻ እንዲሰናበቱ በይኗል

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 30 2010

የኢትዮጵያ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤትን በማቃጠል ወንጀል በተከሰሱ 38 ተጠርጣሪዎች ላይ ዛሬ ብይን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከተከሳሾቹ ውስጥ የተወሰኑት በነጻ እንዲለቀቁ የወሰነ ሲሆን በቀሪዎቹ ላይ የቀረበባቸው የሽብር ክስ ውድቅ ሆኖ በመደበኛ ወንጀሎች ራሳቸውን እንዲከላከሉ በይኗል፡፡

https://p.dw.com/p/2xNji
Äthiopien Journalisten Martin Schibbye und Johan Persson
ምስል AP

ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንት ተከሳሾች በነጻ እንዲሰናበቱ በይኗል

የቂሊንጦ ማረሚያ ቤትን በማቃጠል የሽብር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ የ38 ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው የችሎት ውሎው በነጻ እንዲለቀቁ የበየነላቸው ስምንት ተከሳሾችን ነው፡፡ የልብ ህክምና ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ እና የአየር ኃይል አብራሪው መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ ቀሪዎቹ 30 ተከሳሾች ደግሞ በመጀመሪያ የቀረበባቸው የሽብር ክስ በመደበኛ ወንጀሎች ተቀይሮ እንዲከላከሉ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አማካኝነት ባለፈው ዓመት ህዳር ወር የተከፈተው ክስ ሰላሳ ስምንቱ ተከሳሾች ከጥር ወር 2008 ዓ.ም ጀምሮ ከማረሚያ ቤት አምልጠው ለመውጣት የሽብር ቡድን ማቋቋማቸውን እና እቅዳቸውን ለማስፈጸምም የእሳት ቃጠሎ ማስነሳታቸውን ይወነጅላል፡፡ በዚህ የእሳት ቃጠሎም 23 የሚሆኑ ታራሚዎች በከባድ ሁኔታ ተደብድበው እንዲቃጠሉ እና ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርገዋል በሚል በሽብር ወንጀል መከሰሳቸውን ያትታል፡፡

ክሱን ሲመለከት የቆየው ችሎት ለዛሬ በዋነኛነት ቀጠሮ ይዞ የነበረው ተከሳሾች «ይከላከሉ ወይስ አይከላከሉ» በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት እንደነበር የአብዛኞቹ ተከሳሾች ጠበቃ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ሽፋ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ጠበቃው ብይን ሊሰጥባቸው የነበሩ ጉዳዮችን ዘርዝረዋል፡፡

ሁለት ሰዓት ያህል ዘግይቶ የተጀመረው የዛሬው የብይን ማሰማት ሂደት አስቀድሞ የተመለከተው በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኩል የቀረበውን የምርመራ ውጤት ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ኮሚሽኑ ያቀረበውን የምርመራ ዘገባ ሙሉ በሙሉ በመቀበል 16 ተከሳሾች በግዳጅ ሰጥተውታል የተባለውን የእምነት ክህደት ቃል ውድቅ ማድረጉን ጠበቃው ተናግረዋል፡፡ ዳኞች በእያንዳንዱ ተከሳሽ ላይ የቀረበባቸውን ክስ እና የተመሰከረባቸውን ዝርዝር ለማቅረብ ሲሞክሩ ተከሳሾች እና ጠበቆች ተቃውሞ በማሰማታቸው በቀጥታ ወደ ብይን ንባብ መሻገራቸውን ያስረዳሉ፡፡

Symbolbild Deutschland Justiz
ምስል picture-alliance/dpa/U. Deck

የዛሬው ችሎት ከወትሮው በተለየ በርካታ ቤተሰቦች፣ ታዛቢዎች እና ዲፕሎማቶች የተከታተሉት እንደሆነ ከታዳሚያኑ መካከል አንዱ የነበሩት ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ይናገራሉ፡፡ ዳኞች ብይናቸውን አሰምተው እንደጨረሱ በችሎቱ ግርግር ተፈጥሮ እንደነበርም ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡

ጠበቃ ሙስጠፋ “ክርክር የፍርድ ሂደቱ አንድ አካል እንደመሆኑ ተከሳሾቹ ሊደመጡ ይገባ ነበር” ባይ ናቸው፡፡ በግርግሩን ራሳቸውን የሳቱ ሰዎች እንደተመለከቱ የሚናገሩት ጠበቃው ቆየት ብሎ መረጋጋት መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ የተሰየሙት ዳኞች ግርግር መነሳቱን እንደተመለከቱ ችሎቱን በቶሎ ለቅቀው በመውጣታቸው የዋስትና መብት ማግኘት የነበረባቸው ተከሳሾች ሳይጠየቅላቸው መቅረቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተከላከሉ የተባሉ ተከሳሾች ቀጣይ ቀጠሮ መቼ አንደሆነ እንኳ ሳይነገራቸው ችሎቱ መበተኑን አስረድተዋል፡፡ ከሌሎች ጠበቆች ጋር በመሆን ቀጣይ ሂደቶችን በፍርድ ቤቱ ጽህፈት ቤት በኩል ለማስፈጸም ማሰባቸውንም አክለዋል፡፡ 

በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ስር በሚገኘው የቂሊንጦ እስር ቤት በነሐሴ 2008 ዓ.ም በደረሰው የእሳት ቃጠሎ 23 ሰዎች መሞታቸውን የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቆ ነበር፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና አራማጆች (አክቲቪስቶች) ግን የሟቾቹ ቁጥር በመንግስት ከተጠቀሰው በእጥፍ የላቀ እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ፕሮጀክት የተሰኘው ተቋም ከቃጠሎው ጋር በተያያዘ 67 ሰዎች መሞታቸውን በምርመራ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡ በቂሊንጦ ቃጠሎ በማረሚያ ቤቱ ላይ 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት መድረሱ በአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ዝርዝር ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ