1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶማሊያ የቀጠለዉ የአሸባብ ጥቃት

Eshete Bekeleሰኞ፣ ነሐሴ 18 2007

የአሸባብ ታጣቂ ቡድን በሳምንቱ ማገባደጃ በፈጸማቸው ጥቃቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ታጣቂ ቡድኑ በወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ላይ በፈጸመው ጥቃት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ20 በላይ ደርሷል።

https://p.dw.com/p/1GKrx
Somalia Anschlag in Mogadischu
ምስል AFP/Getty Images/M. Abdiwahab

[No title]

የአሸባብ ታጣቂ ቡድን በደቡባዊ ሶማልያ በሚገኝ የወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ በሰነዘረው ጥቃት የሟቾች ቁጥር ከ20 መብለጡን የጀርመን ዜና አገልግሎት ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

በጥቃቱ በአፍሪቃ ሰላም አስከባሪ ስር የሚገኙ ሶስት የኬንያ ወታደራዊ አሰልጣኞችን ጨምሮ ከ45 በላይ መቁሰላቸው ተዘግቧል። የፍተሻ ኬላዎችን ጥሶ ከገባው ቦምብ የጫነ መኪና ውስጥ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ፈጻሚው ረዳት ከፍንዳታው ቀደም ብሎ በመውጣቱ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ መገደሉን ወታደራዊ ምንጮች ለጀርመን ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። የአሸባብ ታጣቂ ቡድን አናዱሉ በተሰኘው የሬዲዮ ጣቢያ አማካኝነት ለጥቃቱ ሃላፊነቱን ሲወስድ በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች 100 ናቸው ሲል አስታውቆ ነበር። ታጣቂ ቡድኑ በሞቅዲሹ ከተማ በፈጸመው ሌላ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 7 ሰዎች ሲገደሉ ስምንት መቁሰላቸውን በሶማሊያ የዶይቼ ቨሌ ተባባሪ ዘጋቢ የሆነው መሐመድ ኦማር ሁሴን ይናገራል።

Kenia Mitglieder der Al-Shabaab Miliz wurden umgebracht
ምስል Reuters/G. Tomasevic

«የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በሞቅዲሹ በፈጸመው ጥቃት ሻይና ቡና በመጠጣት ላይ በነበሩ ንጹሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ነው። በጥቃቱ ሰባት ሰዎች ወዲያውኑ ሲሞቱ ስምንት ደግሞ ቆስለዋል።»

የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ከአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል፤ የሶማልያ መንግስት ወታደሮች፤ የኬንያና ኢትዮጵያ ወታደሮች ትብብር በተከፈተበት ጥቃት ይቆጣጠራቸው የነበሩ ከተሞችን ለመልቀቅ ተገዷል። የአሜሪካን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ጠንካራ በሚባሉት የቀጣናው አገራትና አህጉራዊ ወታደሮች በታጣቂ ቡድኑ ላይ የተወዱት እርምጃዎች በሶማልያ የተረጋጋ ማዕከላዊ መንግስት ለመመስረት ዋስትና አልሆኑም። የጸጥታ ተንታኞች አሸባብ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚገኝባቸውንና የጦር መሳሪያና ታጣቂዎች የሚያስገባባቸውን ከተሞችና ወደቦች በማጣቱ የመዳከም ምልክት ቢያሳይም የጥቃት መንገዱን ወደ ደፈጣ ጥቃት በመቀየሩ አደገኛነቱ እንደሚያይል ያስጠነቅቃሉ። በሞቅዲሹ የሚገኘው መሐመድ ሁሴን ኡመር አሸባብ የሶማልያ መንግስት በስለላ ስራ ደካማ መሆን ለአሸባብ ጥቃት አመቺ ሁኔታ መፍጠሩን ይናገራል።

«በስለላው በኩል የአሸባብታጣቂ ቡድን ከሶማልያ መንግስት የተሻለ ይመስላል። የሶማልያ መንግስት እነዚህን አሰቃቂ ጥቃቶች ለማስቆም የአቅሙን ያህል እየሞከረ ነው። ሰዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎችና በከተማዋ አውራ ጎዳናዎች ቁጥጥርና ፍተሻ ይካሄዳል። ይሁንና አሁንም ጥቃቶች እየተፈጸሙ ነው። ስለዚህ በስለላ ስራው በኩል የሶማልያ መንግስት እጅጉን ደካማ ነው ማለት እንችላለን።»

Karte Kenia Mandera Anschlag

የሶማልያ መንግስት ኃይሎች ታጣቂ ቡድኑ በወታደራዊ ማሰልጠኛ ላይ ለፈጸመው ጥቃት ዛሬ በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ 12 የአሸባብ ታጣቂዎች መገደላቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ጎዳሄ ከተማ ለሶስት ሰዓታት በዘለቀው የተኩስ ልውውጥ ሶስት የመንግስት ወታደሮች መቁሰላቸውን የዜና ወኪሉ ጨምሮ ዘግቧል። ከስድስት አመታት በላይ በአሸባብ ታጣቂ ቡድን ቁጥጥር ስር የቆየችው መንደር ነጻ ወጥታለች ተብሏል።

የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ከሶማልያ ተሻግሮ ኬንያ ድረስ አሰቃቂ የሰርጎ ገብ ጥቃቶችን ፈጽሟል። የታጣቂ ቡድኑን ጥቃቶች ለማስቆም ሶማልያን ለማረጋጋት የሚሰሩት ምዕራባውያንና የቀጣናው አገራት የሚከተሉትን መንገድ ሊቀይሩ እንደሚገባ የጸጥታ ተንታኞች ይናገራሉ። የጎሳ ፖለቲካ በተጫናት ሶማልያ ከአፍሪቃ ሰላም አስከባሪና ጎረቤት አገራት ይልቅ የመንግስት ሃይሎች በአገሪቱ መረጋጋትና የጸጥታ ሁኔታ ከፍ ያለ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚገባ የጸጥታ ተንታኞች ይናገራሉ።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ