1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሲዳማ ዞን ኹከት የተጠረጠሩ ሐዋሳ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ሰኞ፣ ነሐሴ 6 2011

የሲዳማ ሚዲያ ኔትወርክ ኃላፊዎችን ጨምሮ በሲዳማ ዞን ተቀስቅሶ በነበረ ኹከት እጃቸው አለበት የተባሉ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

https://p.dw.com/p/3NmCT
Sidama Aktivisten Äthiopien Hawassa
ምስል DW/S. Wegayehu

የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሀዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ሁከቶችን በማስተባበር የተጠረጠሩ የሲዳማ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋናና ምክትል ስራ አስኪያጆችን ጨምሮ የዘጠኝ ተጠርጣሪዎችን ጉዳት ተመለከተ።

በዛሬው ችሎት ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች መካከል የሲዳማ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስኪያጅ ጌታሁን ደጉዬ ፣ ምክትላቸው ታሪኩ ለማና የዚሁ ጣቢያ የቦርድ አባል የሆኑት በላይ ባልጉዳ ይገኙባቸዋል።

መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ በጹሁፍ ባቀረበው ማመልከቻ እንዳለው ግለሰቦቹ የተያዙት በሀዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከሀምሌ  11 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት ተከስተው የነበሩ ሁከቶችን በማስተባበር የክልሉንና የፌደራሉን ህገ መንግስታዊ ስረዓት በአመፅ በማፍረስ ወንጀል በመጠርጠራቸው ነው ብሏል።

Sidama Aktivisten Äthiopien Hawassa
ምስል DW/S. Wegayehu

መርማሪ ፖሊስ እስከአሁን በኹከቱ የሞቱ ሰዎችን ማንነት የመለየት ፣ የዘረፋ ተግባር የተፈጸመባቸው የመንግስትና የግለሰብ ንብረቶችን የማሰባሰብና የመመዝገብ እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ማሰረጃዎችን የማሰባሰብ ስራዎችን ማከናወኑን ለችሎቱ አስረድቷል።

በተጨማሪም እስከ አሁን የሶስት መቶ ሰዎችን የምስክርነት ቃል ከመቀበሉም በላይ የምስል ፣ የድምፅ እና የሰነድ ማሰረጃዎችን ለማሰባሰብ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ጭምሮ ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት ድብዳቤ መፃፉንም ለችሎቱ ገልጿል።

በወንጀል ተጠርጥረው በማረፊያ ቤት በሚገኙ በርካታ ሰዎች ላይ የማጣራት ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የተናገረው መርማሪ ፖሊስ አስከአሁንም በወንጀል ድርጊቱ የጎላ ተሳትፎ እንደሌላቸው የተረጋገጡ 332 ታሳሪዎችን መልቀቁን አስረድቷል። 

ይሁን እንጂ በተጠርጣሪዎች ላይ ለመርማሪ ፖሊስ አባላት የምስክርነት ቃል እየሰጡ በሚገኙ ሰዎች ላይ የተለያዩ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች እየደረሱ ይገኛሉ ሲል መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አመልክቷል።

በዛሬው ችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች የድርጊቱ አስተባባሪዎች በመሆናቸው ፣ የተጠረጠሩበት ወንጀል የዋስትና መብት የሚከለክል በመሆኑና ፣ በዋስ ቢውጡም ማስረጃዎችን ሊያጠፉ ስለሚችሉ ጉዳያቸውን በማረፊያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ይደረግልኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። 

የመርማሪ ፖሊስ በማያያዝም ቀሪ የምስክሮችን ቃል ለመቀበል ፣ የምስል ፣ የድምፅ እና የሰነድ ማሰረጃዎችን ለማሰባሰብ እንዲችል ተጨማሪ የአስራ አራት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠኝ ሲልም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም መርማሪ ፖሊስ ባቀረበው ላይ ተጠርጣሪዎች የተቃውም ሀሳብ ካላቸው እንዲያቀርቡ ጠይቋል።

«ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ይሏት»  በማለት የተቃውሞ ንግግራቸውን በተረት የጀመሩት ሶስተኛ ተጠርጣሪ በላይ ባልጉዳ እሳቸውም ሆኑ አብረዋቸው የሚገኙት ሰዎች በጸጥታ አባላት የታሰሩት በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መሆኑና ዓላማውም በህዝቡ የተነሱ የመብት ጥያቄዎችን ለማፈን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ለፍርድ ቤት አሰምተዋል።

ሌሎች ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው የመርማሪ ፖሊስ እያሰባሰብኩ ነው የሚላቸው የምስል ፣ የድምፅ እና የሰነድ ማሰረጃዎች አብዛኞቹ በመንግስት ተቋማት እጅ የሚገኙና በቀላሉ ሊሰበሰቡ የሚችሉ መሆናቸውን በመጥቀስ «የቀረበው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሆን ብሎ እኛን ለማጉላላት በመሆኑ» ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በአንክሮ እንዲመለከትላቸው አሳስበዋል።

Äthiopien Hawassa | Oberster Gerichtshof
ምስል DW/S. Wegayehu

ማስረጃዎቹ ይገኙባቸዋል በተባሉት የመንግስት ተቋማት ውስጥ አንዳቸውም በተራ ሰራተኝነትም ሆነ በሃላፊነት ስለማይሰሩ ማስረጃ ሊያጠፉ ይችላሉ የሚለው የመርማሪ ፖሊስ ምክንያት አሳማኝ ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን ተጠብቆላቸው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከራከሩም ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በማረፊያ ቤት ግቢ እንዲሁም ወደ ችሎት በሚመጡባቸውና በሚመለሱባቸው ጊዚያት በአንዳንድ የጸጥታ ጥበቃ አባላት ሰብዓዊ ክብራቸውን የሚነካና መብቶቻቸውን የሚጋፉ ድርጊቶች እንደሚፈጸሙባቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል።

ፍርድ ቤቱ በመጨረሻም በተጠርጣሪዎች ላይ ለመርማሪ ፖሊስ አባላት ቃል እየሰጡ በሚገኙ ሰዎች ላይ የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እየደረሱ ይገኛሉ የሚለው ተጠርጣሪዎቹ የተባለውን ማድረግ በማይችሉበት የህግ ጥላ ስር የሚገኙና እነሱን የማይመለከት በመሆኑ ቅሬታው አሳማኝ አለመሆኑን በመግለፅ የተባለውን ድርጊት የሚፈፅሙ ሌሎች ግለሰቦች በውጭ ካሉ በህግ መጠይቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በማረፊያ ቤት ግቢ እንዲሁም ወደ ችሎት በሚመጡባቸውና በሚመለሱባቸው ጊዜያት መሉ ክብራቸውና ሰብዓዊ መብታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ አሳስቧል።

መርማሪ ፖሊስ ቀሩኝ የሚላቸውን ማስረጃዎች በሚቀጥሉት አራት ቀናት ውስጥ በማሰባሰብ አጠናቆ እንዲያቀርብ በማዘዝ ለነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዕለቱን ችሎት አጠናቋል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ