1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሱዳን  1 ሺህ 400 ኢትዮጵያዉያን ከዕስር ተለቀቁ

ዓርብ፣ ግንቦት 3 2010

በሱዳን በተለያዩ ዕስር ቤቶች ታስረዉ ይገኙ የነበሩ ኢትዮጵያዉያን  ታሳሪዎች በትናንትናዉ ዕለት ከዕስር መለቀቃቸዉን በሀገሪቱ የሚገኜዉ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ገለጸ። ኢትዮጵያዉያኑ ከዕስር የተፈቱት የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ለሱዳኑ ፕሬዝዳንት ባቀረቡት የይፈቱ ጥያቄ መሰረት  ነዉ ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2xYmg
Infografik Karte Grand Ethiopian Renaissance Dam ENG

1,400 Ethiopian prisoners released in Sudan. - MP3-Stereo


ካርቱም በሚገኘው በሱዳን የኢትዮጵያ ኢምባሲ ዲፕሎማት አቶ ሂርቆ ጋሪ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት በትንትናዉ ዕለት የተፈቱት ኢትዮጵያዉያን፤ በሱዳን ሀገር በሚገኙ የተለያዩ ዕስር ቤቶች  በተለያየ ወንጀል ተጠርጥረዉ የታሰሩና ክሳቸዉ በሂደት ላይ የነበረ እንዲሁም ተፈርዶባቸዉ  በዕስር ላይ የሚገኙ  ናቸዉ። ኢትዮጵያዉያኑ ከዕስር የተለቀቁት በቅርቡ የኢትዮጵያዉ  ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ  በሱዳን ጉብኝታቸዉ ወቅት ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን  አልበሽር ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት መሆኑን አቶ ሀርቆ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያዉያኑን ታሳሪዎች ጉዳይ በተመለከተ ከዚህ ቀደም ኢምባሲዉ ሲከታተል እንደነበረ የገለፁት አቶ ሀርቆ በተለይ  ተፈርዶባቸዉ የነበሩ 57  ታሳሪዎች  ወደ ኢትዮጵያ  ተመልሰዉ የዕስር ጊዜያቸዉን እንዲጨርሱ ሌሎችም በሂደት ላይ የነበሩ እንዲፈቱ ኢምባሲዉም ሆነ የኢትዮጵያ ዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር በተደጋጋሚ በደብዳቤ  ሲጠይቅ  መቆየቱን አብራርተዋል።  
በትናንትናዉ ዕለት የሱዳን መንግስት ከዕስር የለቀቃቸዉ  ኢትዮጵያዉያን በአብዛኛው የሀገሪቱን ህግ በመተላለፍ ታስረዉ የነበሩ ናቸው።  ከግለሰብ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በፍትሃ ብሄር ህግ የታሰሩና ከሳሽ ያላቸዉ እንዲሁም የሰዉ ነብስ ያጠፉ ታሳሪዎች ግን አለመፈታታቸዉን  ዲፕሎማቱ ተናግረዋል።
ከተፈቱት ኢትዮጵያዉያን  በአብዛኛዉ ታስረዉ የነበሩት ስደተኞች በብዛት በሚገቡበት በሱዳን ምስራቃዊ ክፍል በሚገኙ ግዛቶች  ቢሆንም  በመካከለኛዉ እና በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ከሚገኙ ዕስር ቤቶችም የተፈቱ መኖራቸዉን ነዉ ዲፕሎማቱ የገለፁት።ከነዚህም መካከል በካርቱም ለተፈቱ 64 ኢትዮጵያዉያን  የኢትዮጵያ ኢምባሲ ፣ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በሱዳን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት  ዘንድ አቀባበል መደረጉንም ተናግረዋል።በኢትዮጵያ ኢምባሲም ለተፈችዎቹ የራት ግብዣ መደረጉን ገልፀዋል።
እንደ ዲፕሎማቱ ገለፃ የታሳሪዎቹ መለቀቅ  በዲፕሎማሲዉ መስክ የተገኘ ዉጤት ሲሆን የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት የሚያሻሽልና ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ነዉ።
«ያዉ ትልቅ ነገር ነዉ።የዲፕሎማሲ ዉጤት ነዉ።ከዚህ በፊት ከ ሁለት ዓመት በፊት እዚህ በመጡ ጊዜ ያዩት ስለሆነ ይህን ግንዛቤ በመዉሰድ ኢምባሲዉም የዉጭ ጉዳይ ምንስቴርም በዚህ ጉዳይ ላይ ሲሰራ ስለነበር የሱዳን መንግስት ይህንን ተቀብሎ በመፍታቱ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክርና ወደ ተሻለ ደረጃ እንደደረሰ ይታመናል።በቀጣይም ይህንን የሁለት ሀገሮች ግንኙነት ይበልጥ ለማሻሻልና ወደላቀ ደረጃ እንዲደርስ ይሰራል።»ነዉ ያሉት።
ኤምባሲዉ በቀጣይም ወደ ሀገራቸዉ መመለስ የሚፈልጉ  ኢትዮጵያዉያን  ካሉ በፍላጎታቸዉ መሰረት ወደ ሀገር ቤት ለመመለስና መቆየት ለሚፈልጉት ደግሞ መብታቸዉ ተጠብቆ እንዲኖሩ እንደሚሰራ  አቶ ሀርቆ ተናግረዉ ፤በተለያዩ  ዕስር ቤቶች የቀሩ ኢትዮጵያዉያን ካሉም እነሱን ለማስፈታት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ጥረቱ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

Sudan - Der äthiopischen Botschaft in Khartum
በኻርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምስል Ethiopian Embassy

ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ