1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያን በሱዳን መታሰራቸው

ማክሰኞ፣ የካቲት 14 2009

በሱዳን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኤምባሲ የዳያስፖራ ክፍል ዲፕሎማት አቶ ሙክታር ሞሐመድ ሰልፉ መካሄዱን ከሰልፈኞቹም የታሰሩ እንዳሉ ለዶይቼቬለ ቬለ አረጋግጠዋል ። ሆኖም የሞተ ወይም የተጎዳ ሰው የለም ነው ያሉት ።

https://p.dw.com/p/2Y0NN
Karte Sudan Englisch

Sudan Äthiopien proteste und Verhaftung - MP3-Stereo

 የሱዳን መንግሥት ለመታወቂያ የጠየቃቸውን ከፍተኛ ክፍያ ኤምባሲው ተነጋግሮ እንዲያስቀንስላቸው ለመጠየቅ ሄደው የታሰሩት ኢትዮጵያን ቁጥር ከአንድ ሺህ እንደሚበልጥ ኢትዮጵያውያኑ ይናገራሉ ። ሆኖም በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሞተ ሰው የለም የታሰሩትም ቁጥር 69 ነው ብሏል። ኤምባሲው የኢትዮጵያውያኑ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ከሚመለከታቸው የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑንም ለዶይቼቬለ አስታውቋል ። ኂሩት መለሰ ዝርዝር ዘገባ አላት 
ባለፈው አርብ  በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተካሄደው ሰልፍ ላይ የተካፈሉት ቁጥር ወደ ሁለት ሺህ እንደሚደርስ ነው በሰልፉ ላይ የተገኙ አንድ እማኝ ለዶይቼቬለ የተናገሩት ። ሰልፉ የተካሄደውም ኢትዮጵያውያኑ በቅርቡ ለመታወቂያ ማውጫ የተጠየቁት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሚመለከታቸው  የሱዳን መንግሥት ባለስልጣናት ጋር ተነጋግሮ እንዲያስቀንስላቸው አለያም አማራጭ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ለመጠየቅ ነበር ። 
ይሁንና  የኤምባሲ ሠራተኞች ወጥተው ካነጋገሯቸው በኋላ ውዝግብ ሲነሳ የመጣው ፖሊስ አብዛኛዎቹን አስሮ መውሰዱን በሰልፉ ላይ የተገኙ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል ። በሱዳን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኤምባሲ የዳያስፖራ ክፍል ዲፕሎማት አቶ ሙክታር ሞሐመድ ሰልፉ መካሄዱን ከሰልፈኞቹም የታሰሩ እንዳሉ ለዶይቼቬለ ቬለ አረጋግጠዋል ። ሆኖም የሞተ ወይም የተጎዳ ሰው የለም ነው ያሉት  ። አቶ ሙክታር እንደገለጹት ኤምባሲው አስቀድሞ ለሰልፈኞቹ፣ ለጥያቄአቸው መልስ ለማግኘት እየጣረ መሆኑን እና ሰልፍ ማካሄድ እንደማያስፈልግም ነግሯቸው ነበር  ። አቶ ሙክታር፣ የታሰሩት 69 ገደማ ናቸው ቢሉም ዶይቼቬለ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ኢትዮጵያዊ የታሰሩት ቁጥር ከአንድ ሺህ በላይ መሆኑን ነው ለዶቼቤለ የተናገሩት ። ራድዮ ዳባንጋ ከአምስተርዳም የታሰሩት ቁጥር ከ500 እንደሚበልጥም ዘግቧል ። አቶ ሙክታር ግን ይህን አይቀበሉም ። 
ሱዳን ውስጥ በመታወቂያ ክፍያ መጨመር ምክንያት ችግር ላይ የወደቁት የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በችግሩ ውስጥ እጁ አለበት ሲሉ ይከሳሉ ። ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናትን ነው ።በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን ይህን ያስተባብላል ። ኤምባሲው ችግሩ መፍትሄ እንዲፈለግለት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ነው የሚናገረው ። አሁንም ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ለመፍትሄው ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በንግግር እና በቀጠሮ ላይ መሆኑን በኤምባሲው የዳያስፖራ ክፍል ዲፕሎማት አቶ ሙክታር መሐመድ ዋሬ ለዶቼቬለ ተናግረዋል ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ