1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በማዕከላዊ ማሊ በዶጎን ጎሳ ላይ የተካሄደ ጥቃት

ቅዳሜ፣ ሰኔ 8 2011

በሞዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ማሌ በዶጎና ፉላኒ ጎሳዎች መካከል ሰሞኑን የተከሰተዉ ግጭት እንዲሁም የአፍሪቃ ህፃናት የጉልበት ብዝበዛ የዛሬዉ የትኩረት ለአፍሪቃ ዝግጅት የሚያጠነጥንባቸዉ ጉዳዮች ናቸዉ ።

https://p.dw.com/p/3KUne
Mali | Soldaten am Flughafen von Mopti
ምስል Getty Images/AFP/M. Cattani

የማሊ ጥቃት እና የአፍሪቃ ሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ

ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ማሊ ከቅርብ ወራት ወዲህ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እያስተናገደች ነዉ። አንዳንዶቹ ጥቃቶች በአክራሪዎች የሚፈፀሙ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ በጎሳዎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች የሚከሰቱ ናቸዉ። ከሰሞኑንም በሀገሪቱ ማዕከላዊ ክፍል ከባድ ጥቃት ተፈፅሟል።ያለፈዉ ዕሁድ በጎርጎሮሳዊዊ ሰኔ 9 ቀን 2019 የዶጎ ጎሳዎች በሚኖሩባት ሶባሚ ዳ  በተባለች መንደር በተፈፀመ ጥቃት 100 የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል።

ለጥቃቱ  እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም ነገር ግን ዉጥረቱ እያየለ የመጣዉ «ኦጎሳጎ» በተባለች መንደር ከሦስት ወራት በፊት 160 የፉላኒ ጎሳ አባላት ከተገደሉ ወዲህ ነዉ።በዚህ ግድያ «ዳን  ና አምባሳጉ» በተባለ የዶጎን ሚሊሻ ቡድን ተጠያቂ ተደርጎ የነበረ ሲሆን በወቅቱም አንዳንድ የፉላኒ የጎሳ መሪዎች አጸፋ ለመመለስ ዝተዉ ነበር። እናም የዕሁድ ዕለቱ ጥቃት የፉላኒ ጎሳዎች የበቀል እርምጃ ሳይሆን እንዳልቀረ  እየተነገረ ነዉ።ጥቃቱ በተፈፀመባት ሳባሚ ዳ መንደር አቅራቢያ የሚትገኜዉ የሳንጋ ከተማ ከንቲባ አሊ ዶሎ የጥቃቱን  ሁኔታ እንዲህ ነበር የገለፁት።

«ከሕዝቡ በሰበሰብነዉ  መረጃ መሰረት ከባድ መሣሪያ  የያዙ ታጣቂዎች  በ20 የሞተር ብስክሌት ተጭነዉ ነዉ ወደ መንደሩ የገቡት።  ከዚያም ተኩስ ጀመሩ።የመንደሩ ነዋሪዎችም  በወራሪዎችቹ በተቃጠሉት  ቤቶች ውስጥ  መደበቅ ጀመሩ። እነዚህ ቤቶች በአብዛኛው  ጣሪያቸዉ የሳር ክዳን ስለነበር ተቃጥለዋል።ለማምለጥ የሞከሩ ሰዎችም  በቅርብ ርቀት ተኩስ ተገለዋል። 95 የተቃጠሉ አስከሬኖችን  አይተናል። በመንደሩ  300 ሰዎች ይኖሩ የነበረ ሲሆን  50 ሰዎች ብቻ ለጥሪው ምላሽ ሰጥተዋል።»

Mali 2013 Konflikt | Christliche Kirche in Diabaly
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

በአካባቢዉ ምንም አይነት የመንግስት አካል አለመኖሩም ለጥቃቱ መባባስ ዋና ምክንያት ተደርጎ እየተወሰ።ደ ነዉ።በዚህም በአብዛኛዉ የህብረተሰብ ክፍል ጥቃት ይደርስብናል የሚለዉ ስጋት እየጨመረ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ያለዉ አመኔታ ደግሞ እየተሸረሸረ መጥቷል። በሰሞኑ የዶጎ ጎሳዎች ጥቃትም የመንደሪቱ ነዋሪዎች  ጥቃቱ ከመፈፀሙ አስቀድመዉ ለባለስልጣናት ቢያሳዉቁም ከመንግስት በኩል  አፋጣን ምላሽ ባለመሰጠቱ ጥቃቱ ተባብሷል በሚል የሀገሪቱ መንግስት እየተወቀሰ ነዉ። የዶጎ ጎሳዎችን ባህል የሚጠብቀዉና የሚያስተዋዎቀዉ «ጊኒ ዶጎን» የተባለዉ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት  ሃሚዱ ኦንጎባ የማሌን የመንግስት ባለስልጣናት ከሚተቹ አካላት መካከል አንዱ ናቸዉ።

«ከሁለትና  ከሶስት ቀናት ቀደም ብሎ የታጠቁ ሰዎች  ከብቶችን ለመስረቅ  መጥተዉ ስለነበር።  የመንደሩ  ነዋሪዎች  ጥቃት ይፈጸምብናል በሚል ድንጋጤ ዉስጥ ነበሩ። ይህ የማስጠንቀቂያ ምልክት ነዉ ብለዉ በማሰብም ምላሽ ላልሰጧቸዉ ባለሥልጣናት ጉዳዩን  አሳዉቀዉ ነበር ። እሁድ  ሰኔ 2 ቀን  ከምሽቱ 11  ስዓት አካባቢ  ጥቃት ፈፃሚዎቹ  ቦታዉ ደረሱና ግድያ ጀመሩ። ግድያዉ  እስከሚቀጥለዉ ቀን ቀጥሎ ነበር።ሰወችን ለመርዳት የደረሰ አካል ግን የለም።የማሊ የመከላከያና የፀጥታ ሀይሎች የደረሱት ሰኞ ጠዋት ነዉ።እናም  ለመጠፍጨፍ ፣ለማቃጠልና ሁሉንም ነገር ለማጥፋት ጊዜ ነበራቸዉ።»

በሀገሪቱ የተከሰተዉን ቀዉስ ለማስቆምና የንፁሃንን ህይወት ለመታደግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ሀይል ከ2013 ጀምሮ ተሰማርቶ ይገኛል። ጀርመንም 750 ወታደሮቿን በማሊ አሰማርታለች።ያም ሆኖ ግን ግጭቱ አሁንም ድረስ መቋጫ አላገኔም። «Welthungerhilfe» ከተባለዉ የዕርዳታ ድርጅት በርንት ሽቬንክ እንደሚሉት ግጭቱን ለመቆጣጠር በሀገሪቱ የሰፈረዉ የሰላም አስከባሪ ሀይልም ቢሆን ብዙ እያገዘ አይደለም።

«እነሱ በሀገሪቱ  ዉስጥ ይገኛሉ።ነገር ግን ካምፕ ዉስጥ ነዉ የሚቀመጡት።ይህ ደግሞ ሰዎችን አይረዳም።ከሁሉም በላይ ሁኔታዎችንና ነገሮችን ተዘዋዉረዉ የመቆጣጠር ግዴታ አለባቸዉ።»

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ካሰማራቸዉ የሰላም አስከባሪ ሀይል አንዱ የሆኑት ብርጋዴር ጀነራል ፒተር ሚረዉ ግን እኛ እዚህ ባንሆን ኖሮ ሁኔታዉ የከፋ ነበር ባይ ናቸዉ። «እዚህ መሆናችን ጥሩ ነገር ነዉ። እኛ እዚህ ባንሆን ችግሮች ይባባሱ ነበር። በሌላ በኩል ሰዎችን ለመርዳትም እየሞከርን ነዉ። በእርግጥ  የምንሰራዉ በተባበሩት መንግስታት ድንጋጌና ማዕቀፍ  ዉስጥ ነዉ። ያ ማለት የተወሰኑ እጥረቶችና  ዕድሎች  ይኖራሉ»

Sudan Unruhen Proteste in Khartum
ምስል Reuters

በማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል በእርሻ ስራ በሚተዳደሩት ዶጎ ጎሳዎችና ከፊል አርብቶ አደር በሆኑትና ኑሮአቸዉን ከቦታ ቦታ በመዘዋወር በሚገፉት የፉላኒ ጎሳዎች መካከል የሚታየዉ ግጭት የቆየ ሲሆን የዉዝግቡ መነሻም የተፈጥሮ ሀብት ማለትም የግጦሽ መሬት ነዉ።በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ያለዉ ግጭት ከጎርጎሮሳዊዉ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በማሌ ሰሜናዊ ክፍል ከሚደረገዉ የእስላማዊ ሚሊሻዎች እንእስቃሴ ጋር ተያይዞ እየተካረረ መምጣቱም ይነገራል። የዶጎ ጎሳ አባላት፤ ከታላቋ ስሃራ ዕስላማዊ መንግስት ታጣቂዎች ጋር በመሆን ጥቃት እየፈፀሙብን ነዉ በሚል በአብዛኛዉ የዕስልምና ዕመነት ተከታዮች በሆኑት የፉላኒ ጎሳ አባላት ላይ ወቀሳ ይሰነዝራሉ። የፉላኒ ጎሳዎች በበኩላቸዉ « ዳን ና አምባሳጎዉ» በሚል መጠሪያ የዶጎ ጎሳ አባላት የመሰረቱት ራስን የመከላከል ማህበርን ለፉላኒ ጎሳ አባላት ጥቃት ተጠያቂ ያደርጉታል።

በሌላ በኩል በቀጠናዉ በአየር ንብረት ለዉጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ እንደ ዉኃና መሬት በመሳሰሉት የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የሚደረገዉ ግጭት እንዲጨምር አድርጓል። በዓመት  ሦስት ወር ብቻ ዝናብ የሚያገኔዉ ይህ አካባቢእየጨመረ ከመጣዉ  የህዝብ ብዛት ጋር ተዳምሮ ሁኔታዉን አስቸጋሪና የማይተነበይ አድርጎታል። የተፈጥሮ ሀብት እያሽቆለቆለ መምጣትና  በእነሱ ላይ ጥገኛ የሆኑት የአርብቶ አደርና የአርሶ አደር ቁጥር መጨመር ችግሩን የበለጠ እንዳባባሰዉ  መቀመጫዉን ለንደን ያደረገዉ «ቻታም ሃዉስ» ከተባለዉ ጥናትና ምርምር ተቋም ፓዉል ሚሌ ገልፀዋል።በዚህ የተነሳ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጎሳዎቹ መካከል እየታዬ ያለዉ ግጭት ከምንጊዜዉም የከፋ ነዉ ይላሉ ፓዎል ሚሌ።ምክንያቱም ድህነት ሁለቱ ተፋላሚ ጎሳዎች ተዋጊዎችን በቀላሉ እንዲመለምሉ ረድቷቸዋል።የአካባቢዉ ወጣቶች በተለይም ወንዶች ብዙ ስራና ተስፋ ስለሌላቸዉም በቀላሉ ለዚህ ይጋለጣሉ።.

በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል በሚንቀሳቀሱት የተዋሬግ አማፅያንን የመሳሰሉ በጎሳና በሀይማኖት የተደራጁ ቡድኖች ግጭቱ የፖለቲካና የሀይማኖት መልክ እንዲኖረዉ እያደረጉት መጥተዋል።የፖለቲካ አለመረጋጋቱም በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሳቢያ ወደ ደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል በመዛመት ላይ ነዉ።

በ2013 ዋና ከተማዋን ባማኮን ጨምሮ በሰሜናዊ የሀገሪቱን ክፍል ለመገንጠል በሚንቀሳቀሰዉ የተዋሬግ አማፂ ቡድን ቁጥጥር ስር ዉሎ የነበረ ሲሆን የቀድሞ የሀገሪቱ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ ወታደሮቿን በመላክ ግዛቶቹ በየሀገሪቱ መንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ አድርጋለች። ማሌ ከፈረንሳይ ነፃነቷን ያገኔችዉ በጎርጎሮሳዊዉ 1961 ዓ.ም ነበር።

 

የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ በአፍሪቃ

ዓለም ዓቀፍ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ይቁም ቀን ያለፈዉ ረቡዕ ሰኔ 5 ቀን« ህፃናት በእርሻ ማሳዎች ሳይሆን በወደፊት ህልሞቻቸዉ ላይ መስራት አለባቸዉ» በሚል መርህ ተከብሯል።በዚህ ዕለት ዓለም አቀፉ የህጻናት ድርጅት ባወጣዉ መረጃ መሰረት በዓለም ላይ 151 ሚሊዮን ህፃናት ዕድሚያቸዉና አቅማቸዉ በማይፈቅደዉ እንዲሁም ለአካላዊና ስነልቡናዊ ችግር በሚዳርጉ ስራዎች እንዲሰማሩ ይገደዳሉ። የጉልበት ብዝበዛ ከሚፈፀምባቸዉ ከነዚህ ህፃናት ዉስጥ 72 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ህፃናት በአፍሪቃ የሚገኙ ሲሆን በርካቶቹ ከ12 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ናቸዉ።እነዚህ ህፃናት 31 ነጥብ 5 በመቶ በአደገኛ ስራ ላይ የሚሰማሩ ናቸዉ።

Kinder in einem Flüchtlingslager in Äthiopien nahe der Grenze zum Südsudan
ምስል DW/Fanny Facsar

የልጆች የጉልበት ብዝበዛ የተለያዩ መልኮች ያሉት ሲሆን አደገኛና አካላዊ እንዲሁም ስነ-ልቡናዊ ችግር ሊያደርስ ይችላል ይላሉ ከዓለም አቀፉ የህፃናት ድርጅት ነኒያ ቻርቦኒ ።

«በእርግጥ  የግዳጅ ስራ፣ የዝሙት አዳሪነትና  በወርቅ ማዕድን ማዉጫዎች ማሰማራትን የመሳሰሉ አደገኛ ለልጆች በጣም አድካሚ የሆኑና ጉልበትን የሚበዘብዙ ስራዎች በተለያዩ ደረጃዎች አሉ።»

እንደ ዓለም አቀፉ የህፃናት ድርጅት አፍሪቃ ችግሩን ለመቅረፍ ብዙ ርቀት አልሄደችም።ስለሆነም የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ በጎርጎሮሳዊዉ ከ2012 እሰከ 2016 ባሉት አመታት በዓለም ላይ የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም በአፍሪቃ በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት እየጨመረነዉ የመጣዉ ።ድህነት፤ግጭት የወለደዉ መፈናቀልና የሀገራት የፖሊሲ አተገባበር ለችግር በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

በዚህ የተነሳ በአፍሪቃ ከአምስት ህፃናት ዉስጥ ለአካላዊና ስነልቡናዊ ችግር በሚዳርጉ ስራዎች እንዲሰማሩ ይገደዳሉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጎርጎሮሳዊዉ 2025 በዓለም ላይ የልጆችን የጉልበት ብዝበዛ የማቆም ግብ አለዉ።ነገር ግን ይህንን ግብ ለማሳካት በሚያስችል መልኩ ሀገራት  እየተጓዙ አለመሆኑን ነዉ የሚገለፀዉ። መመሪያንና ፖሊስን በማዉጣት ለዉጥ ማምጣት አይቻልም የሚሉት ነኒያ ቻርቦኖይ የወላጆችን የገቢ መጠን የሚያሳድጉ የስራ ፈጠራ ዕድሎችን መጨመር ፣የማህበራዊ  ደህንነት ዋስትናን ማረጋገጥና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ማስፈን ለችግሩ መፍትሄ መሆኑን ይጠቁማሉ።ያ ሲሆን ልጆች አካላቸዉና ዕድሜያቸዉ በማይፈቅደዉ ስራ ሳይሆን በነፃነት በትምህርት ቤቶች እንዲዉሉ ማድረግ ይቻላል።ለዚህም የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል።በተለይም በአብዛኛዉ የልጆች የጉልበት ብዝበዛ በሚደረግበት የግብርና ስራ ላይ።

Kamerun Kinder beim Koranunterricht mit Notebook
ምስል picture-alliance/imageBROKER/M. Katz

"ከግብርና እና በገጠር ልማት ጋር ተያያዥነት ያላቸዉ  የሚኒስቴር መ/ቤቶችና  መንግስታት በግብርና ስራ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመቅረፍ  ተግባራዊ እርምጃዎችን መዉሰድ አለባቸዉ።ችግሩ በአንድ ወገን ጣልቃ ገብነት ወይም በመንግስታት በጎ ፈቃድ ብቻ ችግሩን መፍታት አይቻልም። የህፃናትን የጉልበት ብዝበዛ ለመግታት የተቀናጀ ጥረትና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት  ያስፈልጋል።»

 

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ